በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ተሰተካካይ ጫዋታዋች ዛሬ ላይ ተከናውኖ ስልጤ ወራቤ እና ጅማ አባ ቡና ሶስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።
ጅማ ላይ ጅማ አባቡና ከ ቡታጅራ ከተማ ያደረጉት በባለሜዳው 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። አባ ቡናዎች ለእንግዳው ቡድን ባበረከቱት ስጦታ በተጀመረው ጨዋታ ቡታጅራዎች በ29 ኛው ደቂቃ ላይ በአገኘው ሊኬሳ ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ከእረፍት መልስ ግዙፏ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው በ50ኛው እና በ75ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታግዘው አባ ቡናዎች 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።
ወደ ቦንጋ ያመራው ስልጤ ወራቤ ካፋ ቡናን 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድል አሳክቷል። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ አማካዩ መሐመድ ከድር ለስልጤ ወራቤ ብቸኛዋን የማሸነፍያ ጎል አስቆጥሯል።
ቢሾፍቱ ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከቤንች ማጂ ቡና 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። 3ኛው ደቂቃ ላይ ቱፋ ተሺቲ ለቤንች ማጂ ቡና ግብ አስቆጥሮ ረዘም ላለ ደቂቃ መምራት ቢችሉም የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከመሸነፍ የዳነበትን ግብ ወንድማገኝ አብሬ አስቆጥሯል።
የምድብ ሐ ቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች በቀጣይ ማክሸኞ ከተካሄዱ በኋላ መጋቢት አንድ የ11ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ተከናውኖ አንደኛው ዙር የሚጠናቀቅ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡