ያለፉትን ሁለት ወራት ለ”ሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ” ውድድር በዝግጅት ላይ የሚገኘው የኤርትራ ከ20 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ትላንት ከሩስያ ክለብ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል።
በአሰልጣኝ ዓለምሰገድ ኤፍሬም እየተመሩ ዝግጅት ጀምረው ላለፉት ወራት በርካታ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያደረጉት “የቀይ ባሕር ግመሎች” በትላንትናው ዕለት ከሩስያው ክለብ ኡራል ጋር ተጫውተው 4-1 ማሸነፍ ችለዋል። የኤርትራው ስፖርት ሚኒስትር ሰመረ ተክለ እና የሩስያው አምባሳደር አዜብራ ኬሞዶቭ ባስጀመሩት ጨዋታ ለኤርትራ ሳዶር የማነ፣ ዴቨን ግብጻዊ እና ዓሊ ሱሌይማን (ሁለት ግቦች) ጎሎች ሲያስቆጥሩ ለክለብ ኡራል ግሪቦሪ ሞሮቢቢ ብቸኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
በጨዋታው ጥሩ በመንቀሳቀስ በመጀመርያው አጋማሽ አራት ግቦች ማስቆጠር የቻሉት ኤርትራዎች ባሳለፍነው ወር ደቡብ ሱዳንን ሶስት ለባዶ እንዲሁም የሃገሪቱ መከላከያ እግር ኳስ ቡድንም በተመሳሳይ በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸው ይታወሳል።
በ2007 በሩማንያዊው አሰልጣኝ ዶሪያን ማሪን እየተመሩ ዛምቢያን በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፈው በቶጎው የ2007 የወጣቶች አፍሪካ ዋንጫ ከተሳተፉ በኃላ ላለፉት ዓመታት በወጣቶች እግር ኳስ ተዳክመው የቆዩት ኤርትራዎች እግር ኳሳቸው ከሌላው ግዜ በተሻለ በመነቃቃት ይገኛል።
በአስመራ የሚከናወነው የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ በሚያዝያ ወር እንደሚካሄድ ሲጠበቅ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ይሳተፉበታል። የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድንም በቀጣይ ሳምንት ዝግጅት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡