ሠላም ዘርዓይ የኢትዮጵያ ሴቶች የኦሊምፒክ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሾመች

የቅዱስ ጊዮርጊስ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ የሆነችሁ ሠላም ዘርዓይ የኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት እንድትመራ ተመርጣለች፡፡

ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ቅድመ ማጣርያ ከዩጋንዳ ጋር ጨዋታ ለሚጠብቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመቅጠር መስፈርት አውጥቶ ያወዳደረው የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ በቅድሚያ ከአምስት አሰልጣኞች በቅጥር ማስታወቂያው መሠረት አራት አሰልጣኞችን ለመጨረሻ ፈተና ካቀረበ በኋላ አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይን የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በማድረግ ቀጥሯል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ የሴት ቡድኑን ረዘም ላለ ጊዜ በመምራት የምትታወቀው አሰልጣኟ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት በማጣሪያ እና በሴካፋ ውድድር ላይ የመራች ሲሆን አሁን ደግሞ የኦሊምፒክ ቡድኑን ለመምራት ተመራጭ ሆናለች፡፡ ሹመቱን ከሰማች በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን ያደረገችው አሰልጣኝ ሠላም “ከዚህ በፊት በመጀመሪያው የብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ በጣም ደስ የሚል ቆይታ ነበረኝ። አሁን ግን የበለጠ ኃላፊነት ነው የሚሰማኝ፤ ምክንያቱም ምን እንደሚጠብቀኝ ካለፈው የአሰልጣኝነት ቆይታዬ ተምሬያለሁ። ስለዚህ የተሻለ ዝግጅት እና ሀሳብ ይኖረኛል ብዬ አስባለሁ። በብሔራዊ ቡድን ወደ ሰባት እና ስምንት የጨዋታ ልምድ ኖሮኛል። እሱኔ ተጠቅሜ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት ሀሳቧን ተናግራለች፡፡

ማክሰኞ ለቃል ፈተና ጥሪ የቀረበላቸው አራቱ የመጨረሻ ተመራጭ አሰልጣኞች ሌላ ጊዜ እንጠራችዋለን ተብለው ይህን ተለዋጭ ቀን እየጠበቁ ባለበት ሰዓት አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ መሆኗ ከአሁኑ ቅሬታን ማስተናገድ የጀመረ ሲሆን መሠረት ማኔ እና ሰርካለም ምርጫው አግባብ አይደለም በሚል ደስተኛ አለመሆናቸው ተሰምቷል። ስለ አሰልጣኟ ሹመት በቀጣይ ዝርዝር ጉዳዮችን የምንጠብቅ ቢሆንም ፈተና ሊፈተኑ ቀነ ቀጠሮ እየጠበቁ ሹመቱ መፈፀሙ ቅሬታዎችን አበራክቷል፡፡ አንድ አሰልጣኝ ከፈተናው አስቀድማ ራሷን ከውድድሩ ማግሏም ይታወሳል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *