አንደኛ ሊግ | የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የመጀመሪያው ዙር ግምገማ በሦስት ከተሞች ተከናውኗል

58 ክለቦችን በስድስት ምድብ ተከፍሎ ሲደረግ የቆየው የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የመጀመሪያው ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ ግምገማ እና ውይይት ትላንት እና ዛሬ አዲስ አበባ፣ ሀዋሳ እና ባህር ዳር ላይ ተከናውኗል፡፡

ሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ላይ የምድብ ሶስት እና ስድስት ተካፋይ ክለቦችን ያሳተፈው ግምገማ ማክሰኞ ከማለዳው 3:00 ጀምሮ ሲካሄድ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ፣ ከአንደኛ ሊግ ኮሚቴ አቶ በልሁ ወልደማርያም ዳኞች ኮሚቴ ኮሚሽነር ዓለማየሁ እሸቴ እና እንዲሁም የሁለቱም ምድቦች ተሳታፊዎች በተገኙበት ውይይቱ ተደርጓል፡፡ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ በመክፍቻ ንግግር ባስጀመሩት በዚህ ፕሮግራም የ2011 የአንደኛ ሊግ የመጀመሪያው ዙር የውድድር አፈፃፀም ግምገማን የያዘው ሰነድ በዓለማየሁ እሸቴ የቀረበ ሲሆን በዋናነት ውድድሩ ከተያዘለት ጊዜ ሊዘገይ የቻለበትን ምክንያትን ገልፀው ክለቦች በተባለው ጊዜ ክፍያን ባለመፈፀማቸው ምክንያት ዘግይቶ ለመጀመር እንደተገደዱ በሪፖርቱ አቅርበዋል፡፡ ከቀረበው ሪፖርት በኋላ ጥያቄዎች ተነስተውም ምላሽን ተሰቷቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ትላንት በአዲስ አበባ የምድብ 1 ፣ 4 እና 5 ክለቦች ግምገማ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚድያ ክፍል የተከናወነ ሲሆን ከውድድር እና ስነ-ስርዓት አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ ፣ ከአንደኛ ሊግ ኮሚቴ አቶ ኤፍሬም እንዲሁም ከዳኞች ኮሚቴ ሲያምረኝ ዳኜ ተገኝተዋል። የውድድሩ ሪፖርት በአቶ ኤፍሬም የቀረበ ሲሆን እንደ ሀዋሳው ሁሉ የውድድሩ አፈፃፀም ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ቀርበዋል።

ዛሬ በባህር ዳር ቤልማስ ሆቴል በተከናወነው ግምገማ የምድብ 2 ተሳታፊ ክለቦችን ያቀፈ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወሮ ሶፊያ አልማሙን፣ ከአንደኛ ሊግ ኮሚቴ አቶ የሺዋስ እንዲሁም ከዳኞች ኮሚቴ አቶ ፍቃዱ ተገኝተዋል።

በሦስቱም ቦታዎች ከቀረበው ሪፖርት መካከል በአጠቃላይ በውድድሩ 255 ጨዋታዎች መደረጋቸው ሲገለፅ 531 ጎሎች ተቆጥረው 900 ቢጫ እና 34 ቀይ ካርዶች ተመዝግበዋል። ሊጀመር ከታሰበበት ጊዜ በክለቦች ጥያቄ መሰረት ለ25 ቀናት ዘግይቶ ህዳር 30 ሲጀመር በምድብ 1 እና 5 የሚገኙ ቡድኖች የነበረባቸውን ችግር ባማከለ መልኩ ተጨማሪ ቀናት ተራዝመው ታህሳስ 8 እንደተጀመሩም ተገልጿል።

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopia

በውድድሩ ሒደት የታዩ ጠንካራ ጎኖች ከተባሉት መካከል ለሚከሰቱ ችግሮች አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃ መወሰዱ፣ የእረፍት ጊዜ በመስጠት መርሐ ግብሮች እንዲያጠናቅቁ መደረጉ፣ ኮሚኒኬ በወቅቱ እንዲደርስ መደረጉ እና የመሳሰሉት ሲጠቀሱ ዓመታዊ ክፍያ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቁ፣ የፀጥታ አጠባበቅ ችግሮች፣ የቡድን አመራሮች ውሳኔን በፀጋ ያለመቀበል በደካማ ጎንነት ከተጠቀሱት መካከል ናቸው።

ከሪፖርቶቹ በኋላ የክለብ ተወካዮች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን እንደ ክለብ በተናጠል የደረሰባቸውን ችግር ከመግለፅ ባሻገር የተለያዩ አስተያየቶች ተነስተዋል፡-

– የዳኛ እና የኮሚሽነር ሪፖርት ጨዋታውን የማይገልፅ ነው። ጥፋት በሜዳ ላይ እየተፈፀመ ጨዋታው በሰላም ተጠናቀቀ በማለት ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡

– አጥር በሌለው ሜዳ ውስጥ ከደጋፊዎች ጋር እየተቀላቀለ ነው ዳኛ የሚያጫውተው። ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ፌዴሬሽኑ ሜዳ ይገመግማል ይባላል ያን ነገር ግን በተግባር እያየን አይደለም፡፡

– ዋና ዳኛ ከረዳት ዳኞች ጋር በመግባባት መስራት አልቻሉም።

– ዳኞች ጫና ውስጥ ሆነው ስለሚያጫውቱ ለባለሜዳው ክለብ ያደላሉ፡፡

– የቡድን አመራሮች ውጤት ለማስቀየር ጥረቶችን ሲያደርጉ ይስተዋላል።

– አምና ይህ ግምገማ አልተደረገም። ዘንድሮ መደረጉ ግን አምና ካየናቸው ፈተናዎች አንፃር ሊፈቱ የሚችሉ በመሆናቸው የሚበረታታ ነው፡፡

– ይህ መድረክ በየአካባቢው መደረጉ በመልካምነቱ እንወስደዋለን፡፡

– አንድ ቡድን በተከታታይ ከሶስት በላይ ጨዋታዎች በሜዳው እየተጫወተ ይገኛል።

– አስቀድሞ የወጣው ድልድል ተፋልሶ ጨዋታዎች በተዘበራረቀ ሁኔታ እየተካሄዱ ነው።

– መልክዓ ምድርን ያማከለ ተብሎ የወጣው ድልድል አንዳንድ ክለቦችን ወጪ እየተፈታተነ ነው።

– ኮሚኒኬ እንደከዚህ ቀደሙ ከወረቀት ይልቅ በኢሜይል መሆኑ ተደራሽነቱ ላይ ችግር አስከትሏል።

– ከውል ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽኑ ያስቀመጠው ደንብ ክለቦችን ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ ነው።

– ዳኖች ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ አንድን ቡድን በተደጋጋሚ ያጫውታሉ።

– በእድሜ የገፉ ኮሚሽነሮች ውድድሮችን በአግባቡ ለመታዘብ ሲቸገሩ እናስተውላለን።

ከአስተያየቶቹ በኋላ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ የሰጡ ሲሆን በመድረኮቹ የተሰጡት አስተያየቶች በሁለተኛው ዙር ለሚደረገው ውድድር እንደ ግብዓት እንደሚወሰድ ተገልጿል። መጋቢት 15 ሊጀመር የነበረው ውድድርም በአብዛኛዎቹ ክለቦች ጥያቄ መሠረት ወደ መጋቢት 22 መራዘሙ ዛሬ የተገለፀ ሲሆን የሚያልቅበት ቀን ግን ለውጥ ሳይደረግበት ግንቦት 15 እንዲሆን ተወስኖ ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *