የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ነገ ወደ ማሊ ያመራል

በሜዳው ከማሊ ጋር አንድ አቻ የተለያየው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች (ኦሊምፒክ) ቡድን ነገ ማለዳ 18 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ ፈተና ይዞ ወደ ስፍራው የሚያቀና ይሆናል።

በቶኩዮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2020 የኦሊምፒክ ውድድር እንደ ማጣርያነት ለሚያገለግለው የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ለማለፍ የማጣርያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ 23 ዓመት በታች (የኦሊምፒክ) ቡድን የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ትላንት በአዲስ አበባ ስቴዲየም አከናውኖ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መለያየቱ ይታወቃል።

የመልሱን ጨዋታ በቀጣይ ማክሰኞ ባማኮ ላይ የሚያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ ነገ ማለዳ 01:00 ወደ ስፍራው የሚያቀና ሲሆን ዛሬ ማምሻውን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከአዳማ ከተማ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሰርቷል።

በልምምዱ ወቅት በትናንትናው ዕለት የጨዋታው መጨረሻ ደቂቃዎች ከጉዳቱ ጋር እየታገለ ያጠናቀቀው አጥቂው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ልምምድ ያልሰራ ቢሆንም ነገ ከቡድኑ ጋር አብሮ እንደሚጓዝ ተነግሯል።

የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ዐወል አብዱራሂም፣ ዮሴፍ ተስፋዬ እና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በምሽቱ ልምምድ ላይ በመገኘት የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል።

ወደ ማሊ ባማኮ የሚያቀኑት 18 ተጫዋቾች ስም ዝርዝር

ምንተስኖት አሎ፣ ተክለማርያም ሻንቆ፣ ደስታ ደሙ፣ ወንድሜነህ ደረጄ፣ጌቱ ኃይለማርያም፣ ደስታ ዮሐንስ፣ኢብራሂም ሁሴን፣ ዳዊት ወርቁ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ፣ አፈወርቅ ኃይሉ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ከነዓን ማርክነህ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ሐብታሙ ገዛኸኝ፣ አቡበከር ናስር፣ እስራኤል እሸቱ እና ፍቃዱ ዓለሙ

በማክሰኞው ጨዋታ በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን በቀጣዩ የማጣርያ ዙር ካሜሩንን የሚገጥም ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *