የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን የመጨረሻ ትኩረት የፋሲል እና መቐለ ጨዋታ ይሆናል።
የጎንደሩ አፄ ፋሲለደስ ስታድየም ነገ በ09፡00 ተጠባቂውን የፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታን ጨዋታ ያስተናግዳል። ፋሲል ከነማ ከሚገኝበት መልካም አቋም አንፃር የሊጉን መሪዎች መፈተን የሚያስችል ጊዜ ላይ እንደሚገኝ መናገር ይቻላል። ሁለተኛው ዙር ከገባ በሁለት ጨዋታዎች በጠንካሮቹ ሀዋሳ እና ሲዳማ ላይ አራት ግቦችን ማስቆጠር የቻሉት አፄዎቹ አራት ነጥቦችንም መሰብሰብ ችለዋል። ከተከላካይነት የሚና ለውጥ አድርጎ በፊት መስመር ተሰላፊነት በመጫወት ላይ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ የሚያሳየው ንቁ ተሳትፎ እና ግቦችን በፍጥነት ማስቆጠር መጀመሩም ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን የነገ ፍልሚያ ትልቅ ጠንካራ ጎን ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጠው ፋሲል የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥንቃቄን ሊመርጥ በሚችለው ተጋጣሚው የኋላ ክፍል ክፍተቶችን ለማግኘት መፈተኑ የሚቀር ባይመስልም እንደ ሱራፌል ዳኛቸው አይነት የርቀት ሙከራዎችም ሌላ አማራጮቹ ሊሆኑ ይችላሉ። በጨዋታው ፋሲሎች መጣባቸው ሙሉ ፣ ናትናኤል ወርቁ እና አብዱራህማን ሙባረክን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀሙ ሲሆን ሱራፌልን ከኦሉምፒክ ቡድኑ ጥሪ መልስ ያገኛሉ።
ሊጉን በርቀት እየመሩ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች የአስር ተከታታይ ጨዋታዎች ባለድልነታቸው ጉዞ በወልዋሎ ቢደናቀፍም አሁንም ከስድስተኛው ሳምንት በኋላ ሽንፈት ሳይደርስባቸው ቀጥለዋል። ነገም በጎንደር ከበድ ያለ ፈተና እንደሚጠብቃቸው የሚታሰብ ሲሆን ለቻምፒዮንነት እንደሚጫወት ቡድን ነጥብ ይዞ የመመለስ ብሩቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የአሰልጠኝ ገብረመድህን ኃይሌው መቐለ በጨዋታው በአንዳንድ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ላይ ሲያደርገው እንደሚስተዋለው በሦስት የመሀል ተከላካዮች የሚጠቀም እና በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የተቃኘ ቡድን ይዞ እንደሚቀርብ ይገመታል። በዚህም ቡድኑ ፊት ላይ የአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደን ስኬታማ ጥምረት በመጠቀም የአፄዎቹን የተከላካይ ክፍል መፈተኑ አይቀርም። መቐለዎች ከጉዳታቸው በሚገባ ያላገገሙት ስዩም ተስፋዬ እና ሳሙኤል ሳሊሶን ይዘው ያልተጓዙ ሲሆን ቁልፍ ተጫዋቻቸው አማኑኤል ከኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ መልስ ግብ ጠባቂው ፊሊፖ ኦቬኖም በተመሳሳይ ከብሔራዊ በድን ጥሪ በኋላ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– አምና የሁለቱም ዙር ጨዋታዎች በገለልተኛው አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የተደረጉት ሲሆን ሁለቱም ጨዋታዎች ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ፡፡ በመጀመሪያው ዙር የተገናኙበት የዘንድሮው ጨዋታ ደግሞ በመቐለ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
– ፋሲል ከነማ ሜዳው ላይ ስምንት ጨዋታዎች አድርጎ አምስት ድሎች እና ሦስት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል። እስካሁን ጎንደር ላይ ሽንፈት ያላገኘው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት የሜዳው ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረበትም።
– ከየካቲት መግቢያ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትግራይ ስታድየም ውጪ ጨዋታውን የሚያደርገው መቐለ ስድስት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ሲያከናውን በመጀመሪያ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ቢያገኘውም ቀጥሎ አቻ በመውጣት ከዚያምሦስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቧል።
ዳኛ
– ጨዋታው ሁለቱን ቡድኖች በተናጠል ሁለት ሁለት ጊዜ ያጫወተው ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይመራዋል። አርቢትሩ በእስካሁኖቹ ስምንት ጨዋታዎች 38 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲያሳይ አንድ ጊዜ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ሁለት ተጫዋቾችን ለሜዳ አሰናብቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-3-3)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሁሴን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ሠለሞን ሐብቴ – ኤፍሬም ዓለሙ – ሱራፌል ዳኛቸው
ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ
መቐለ 70 እንደርታ (3-5-2)
ፍፊሊፔ ኦቮኖ
ቢያድግልኝ ኤልያስ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ
አንተነህ ገብረክርስቶስ –ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ያሬድ ሀሰን
ሐይደር ሸረፋ
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ያሬድ ከበደ