የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ይህን ብለዋል።
“ለኛ ትልቅ ድል ነው” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ
ስለጨዋታው
ጨዋታው በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር። እነሱ 13 ተከታታይ ጨዋታ አልተሸነፉም ነበር፤ የሊጉ መሪም ናቸው። ከኛ ጋር የነበራቸው የነጥብ ልዩነት ወደ 10 ነጥብ ነበር። እናም ያንን ስትመለከት ጠንካራ ቡድን ነው። የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈን በዋንጫ ፉክክር ዉስጥ ለመቆየት የነበረን ጉጉት ቢያንስ ልዩነቱን ለማጥበብ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን። ሜዳም ላይ የነበረዉ ያ ነው። በርካታ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረናል። ተሳክቶልን አንድ ግብ አስቆጥረናል። ለኛ ትልቅ ድል ነው።
የድሉ ምክንያት የተጫዋች ቅያሪ ወይስ ቀይ ካርድ?
እውነት ለመናገር ከመጀመሪያው ጀምሮ ብልጫ ነበረን። በመጀመሪያ አስር አስራ አምስት ደቂቃ ሽመክት ያመከናቸው አጋጣሚዎች እንኳን ግልፅ የግብ እድሎች ነበሩ። የተጫዋቾቹ መውጣት ተገቢ ነው። ሁለተኛ ቢጫ ነው ያየው፤ የቀይ ካርዱ ተገቢነዉ። ዓለምብርሀን ታዳጊ ተጫዋች ነው። ዘንድሮ ነው ያሳደግነው ተስፋ ሰጭ ልጅ ነው። በሱ ግብ ማሸነፋችን ቢያስደስተኝም ያሸነፍነው እንደ አጠቃላይ ጥሩ ስለ ነበርን ነው።
በሜዳቸሁ ያለመሸነፍ ጉዞ…
እውነት ለመናገር እኛ ከተቻለ በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችንም ውጭ ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው። አጥቅተን ነው ምንጫወተዉ ። እግርኳስ ሁለቱም ነገር ቢኖረዉም ከማሸነፍ ጋር የተያያዘ ነገር ነው ምንሞክረው። ዋናው ቡድኑ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀናጀ መሄዱ ነው። እኛ እስከ መጨረሻው የራሳችን የቤት ስራ እንሰራለን ።
” ፋሲል የተሻለ ሆኖ አሸንፏል” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ
ስለጨዋታው
እኛ እዚህ ስንመጣ የምናገኝውን አጋጣሚ ተጠቅመን መሪነታችን አስጠብቀን ለመሄድ ነበር። ማለት ማሸነፍ ወይ አቻ መውጣት ነበር። ቢሆንም ግን ተሸንፈናል። የተሸነፍንበት የራሳችን የሆኑ ጥቃቅን ስህተቶች አሉ። የቀይ ካርዱ በተደጋጋሚ ጥፋት ስለሰራ ነው። እኛም በተደጋጋሚ ነግረነው ነበር። ያ ደግሞ ጫና እንዲበዛብን አድርጓል። እነዚህ በዘጠና ደቂቃ የታዩ ክፍተቶች አልፎ አልፎ የሚደረጉ ውሳኔዎች ችግሮች አሉባቸው። ግን የጎላ ችግር አለ ብዬ አላስብም። የጎንደር ህዝብም ቡድኑን ዘጠና ደቂቃ መደገፉ ጥሩ ነው። እናም ምንም አይነት ቅራኔም አልነበረንም ስለዚህ ተቀብለነዋል ።
ስለ ዳኝነት
ስለዳኝነት አላወራም፤ ቀለል ባለ መልኩ ተናግሬአለሁ። ፋሲል ጥሩ ነበር፤ የሜዳው እና የደጋፊ ኃይልም ተጠቅሟል። የተሻለ ሆኖ አሸንፏል። እኛ በታክቲክ ደረጃ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ የሳትናቸዉ ኳሶች እና የተጫዋቹ ቀይ ካርድ ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን እንጅ የኛ ተጫዋቾች በጨዋነት እንዲጫወቱ እና መሪነታችን ለማስጠበቅ ነበር የመጣነው።
ካለፉት 3 ጨዋታዎች አንድ ብቻ ማሸነፉ
ያጋጥማል። አንድን ቡድን ጥሩ ነው ጥሩ አይደለም የምትለው በጠቅላላ ድምር ውጤት ነው እንጅ በአንድ ጨዋታ ደካማ ነው ወይም ደካማ አይደለም ማለት አይቻልም። ስናሸንፍ እንዴት እንደመጣን እናውቀዋለን። እናም እኛ ስንሸነፍ አንገታችንን አናቀረቅርም። ስናሸንፍም ቡራ ከረዩ አንልም።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡