ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበውበታል። አቃቂ ቃሊቲ ሽንፈት ቢያስተናግድም መቐለ አቻ በመውጣቱ መሪነቱን አስጠብቋል።
08:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማን 3-2 አሸንፏል። ቂርቆሶች የተሻለ በተንቀሳቀሱበት በዚህ ጨዋታ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች እምብዛም አልታዩም። በ34ኛው ደቂቃ ባንቺ ይርጋ ተስፋዬ ከመጨረሻ ተከላካይ ኳስ ቀምታ ጥሩ የግብ ዕድል ብታገኝም ሳትጠቀምበት የቀረችው ቂርቆስን መሪ ልታደርግ የምትችልና በዚህ አጋማሽ የታየች ብቸኛ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበረች።
የተሻለ ፉክክር በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ 50ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ከሔማ አቡሼ ጋር በግሩም ቅብብል ወደ ሳጥን በመግባት ቀዳሚውን ጎል ለቂርቆስ አስቆጥራለች። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ የተነቃቁት ልደታዎች አቻ ለመሆን ብዙ ደቂቃ አልፈጀባቸውም፤ በ55ኛው ደቂቃ እማዋይሽ ይመር ባስቆጠረችው ጎል።
ከሁለቱ ጎሎች በኋላ መልሶ የተቀዛቀዘው ጨዋታ ተቀይራ በገባችው እየሩሳሌም ብርሀኑ የ77ኛው ደቂቃ ጎል መነቃቃት አሳይቷል። እየሩሳሌም በ90ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ በጥሩ አጨራረስ ሦስተኛውን የቂርቆስ ጎል ስታስቆጥር የዳኛ የመጨረሻ ፊሽካ ሲጠበቅ አስናቀች ቲቤሶ ከርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት አስቆጥራ ጨዋታው በቂርቆስ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በ9፡00 ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ የተካሄደው የፋሲል ከነማ እና የሻሸመኔ ከተማ ጨዋታ በፋሲል 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ፋሲል በድሉ በመታገዝ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ማደግ ባይችልም ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁን አረጋግጧል።
10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በቦሌ ክ/ከተማ 2-1 ተሸንፏል። በጨዋታው ጠንክረው የቀረቡት ቦሌዎች ለሊጉ መሪ ከባድ ፈተና ሆነው ታይተዋል። ከመስመር በሚነሱ እና በረጃጅም ኳሶች የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት ያረጉት ሲሆን በ9ኛው ደቂቃ መሪ ሊሆኑ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ምስጋና ግርማ ከሳጥን ውስጥ የመታችው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት ቦሌዎች በ22ኛው ደቂቃ ያገኙትን ቅጣት ምት መዓዛ አብደላ ወደ ጎልነት ቀይራ መሪ መሆን ችለዋል። ከጎሉ በኋላ አቃቂዎች የተሻለ ኳስ ቁጥጥር ቢያሳዩም ቦሌዎች ክፍተት ባለመስጠት እና ቅብብሎችን በማቋረጥ ተሳክቶላቸው የመጀመርያው አጋማሽን በመሪነት አገባደዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ቦሌ በጥብቅ መከላከል፤ አቃቂ ጎል በመፈለግ ተጠምደው ተመልካቹን ያዝናና ፉክክር አሳይተዋል። አቃቂዎች በተጋጣሚያቸው የሜዳ አጋማሽ በማመዘን ተጭነው መጫወት ቢችሉም ሰብረው ወደ ሳጥን ለመግባት ተቸግረው ታይተዋል። በዚህም ግልፅ የጎል እድል መፍጠር ተስኗቸው ለረጅም ደቂቃዎች ቆይተዋል።
በ84ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ሳጥን አቅራቢያ የተገኘውን ቅጣት ምት ዙፋን ደፈርሻ በቀጥታ መትታ በማስቆጠር አቃቂን አቻ ማድረግ ብትችልም ቀጣይ ደቂቃዎችን የድል ጎል ለማግኘት ሙሉ ለሙሉ ለማጥቃት መሞከራቸው በመጨረሻ ዋጋ አስከፍሏቸው ለመሸነፍ ተገደዋል። በጨዋታው በግሏ ጥረት ስታደርግ የነበረችው ህድዓት ካሱ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የማሸነፍያ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በቦሌ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጨዋታው ከመርሐ ግብር ማሟያነት የዘለለ ትርጉም ባይኖረውም ቦሌዎች እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለሊጉ ዋንጫ እየተፎካከሩ የሚገኙት አቃቂዎችን እስከመጨረሻው ፈትነው ሦስት ነጥብ ማስመዝገባቸው በሌሎች የሀገሪቱ ክለቦችም ሊለመድ የሚገባው ነው።
በተመሳሳይ 10፡00 መቐለ 70 እንደርታ በሜዳው ንፋስ ስልክን አስተናግዶ 2-2 በመለያየት ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ማደጉን አረጋግጧል። እጅግ ማራኪ የጨዋታ ፍሰት እና ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ጎል ያስተናገደው ገና እንደተጀመረ ነበር፤ በ2ኛው ደቂቃ ዮርዳኖስ ምዑዝ በግል ጥረቷ ገብታ በግሩም አጨራረስ ግብ በማስቆጠር ቡድኗን መሪ ማድረግ ስትችል በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ የነበራቸው ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በ6ኛው ደቂቃ ላይ በፍረወይኒ ገብረዮሐንስ ግብ በማስቆጠር መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። አማካይዋ ከቅጣት ምት የተመታውን ኳስ ግብጠባቂዋ ዮርዳኖስ ኃይሌ ስትጨርፈው በግንባር በመምታት ነበር ያስቆጠረችው።
ዘግይተው ወደ ጨዋታው የገቡት ንፋስ ስልኮች በሄለን ገበየሁ የቅጣት ምት ሙከራ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በ39ኛው ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ባደረገቸው የአጥቂ ክፍል ተሰላፊ ሜሮን ገነሞ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር ወደ ጨዋታው መመለስ ችለዋል። ከግቡ በኃላም ጥሩ የተንቀሳቀሱት ንፋስ ስልኮች በትዕግስት ሽኩር አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። አማካይዋ በመቐለ ተጫዋቾች ትኩረት ማጣት ያገኘችው ንፁህ የግብ ዕድል ነበር ያልተጠቀመችበት።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጥሩ ፉክክር በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ባይታይበትም ጥሩ ጨዋታ የታየበት ነበር። ሄለን ገብረፃድቃን ከመዓዘን አሻምታው አበባ ገብረመድኅን በግንባርዋ ገጭታ ባደረገችው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት መቐለዎች በሙከራ ረገድ ከተጋጣምያቸው የተሻሉ ነበሩ። በዚህም በርሻን ብርሃኑ እና በዮርዳኖስ ምዑዝ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር በተለይም የዮርዳኖው ሙከራ የቡድኑ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች። በጨዋታው ከጥሩ ጨዋታ አልፈው ወደ ግብ ያልቀረቡት እንግዶቹ በ55ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። ግቧም ግብ ጠባቂዋ ሸዊት አብርሃ እና ተከላካይዋ ፍፁም ኪሮስ ባለመናበባቸው በፍፁም ኪሮስ በራስ ላይ የተቆጠረች ነበረች። ጨዋታው በዚ መጠናቀቁ ተከትሎ መቐለዎች በመጀመርያ ዓመት ተሳትፏቸው በአሰልጣኝ ህይወት አረፋይነ እየተመሩ ወደ ፕሪምየርሊግ ማለፋቸው አረጋግጠዋል። ጨዋታውን አሸንፈው ቢሆን ደግሞ መሪነቱን ከአቃቂ ቃሊቲ መረከብ ይችሉ ነበር። (በማቲያስ ኃይለማርያም)
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡