ክለቡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን 13 ነጥቦችን ብቻ የሰበሰበ ሲሆን በ13ኛ ደረጃ ከሚገኘው ስሑል ሽረ የ13 ነጥቦች ልዩነት ያለው በመሆኑ ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ከመርሐ ግብር ማሟያ የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም።
በክረምቱ የዝውውር ወቅት ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር በመለያየት በወጣቶች እና ዝቅተኛ ክፍያ በሚያገኙ ተጫዋቾች ቡድኑን ያዋቀረው ደደቢት በተለይ በመጀመርያው ዙር እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን በሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ለውጦችን አድርጎ በመቅረብ መነቃቃት ቢያሳይም ብዙም ሳይዘልቅ ቀርቶ አራት ጨዋታ እየቀረው ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል።
በ1989 የተመሰረተው ደደቢት በ2002 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት ጊዜ ጀምሮ በጠንካራ የፋይናንስ አቅም በርካታ ተጫዋቾችን በማሰባሰብ ተፎካካሪ ሆኖ በመቅረብ በ2005 የሊጉ አሸናፊ መሆን ችሎ ነበር። ሆኖም ከቻምፒዮንነቱ በኋላ ባሉት ዓመታት የቡድኑ ተፎካካሪነትም ሆነ የገንዘብ አቅም ቀስ በቀስ እየተዳከመ መጥቶ ዘንድሮ ለተጫዋቾች ደሞዝ ለመክፈል እና በውድድሩ ለመቀጠል እስከመቸገር ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡