ከፍተኛ ሊግ | ወደ ፕሪምየር ሊግ ላደጉት ክለቦች ሽልማት ተበርክቷል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2011የውድድር ዘመን በየምድባቸው በቀዳሚነት በማጠናቀቅ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉት ወልቂጤ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ለቡድኖቻቸው ሽልማት አበርክተዋል።

በ46 ነጥቦች ምድብ ለን በመሪነትን ያጠናቀቀው ወልቂጤ ከተማ ትላንት ምሽት በለቡድኑ ተጫዋቾች እና ለአሰልጣኝ ክፍል ኃላፊዎች የማበረታቻ ሽልማት የመስጠት እና የምስጋና ዝግጅት ተከኗውኗል። ከ12 ሰዓት ጀምሮ በተከናወነው ዝግጅት የዞኑ አስተዳዳሪ፤ የከተማው ከንቲባን ጨምሮ የክለቡ አመራሮች፣ ተጨዋቾች፣ ደጋፊዎች እና እንግዶች በቦታው የተገኙ ሲሆን የእራት ግብዣ እና የሽልማት አሰጣት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል። ዝግጅቱን በንግግር የከፈቱት የዞኑ አስተዳደር መሐመድ ጀማል፣ የክልሉ ከንቲባ ግሩም ወልደሰንበት እና የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበባው ሰለሞን በክለቡ ስኬት መደሰታቸውን በመግለፅ ለተጫዋቾቹ እና ለአሰልጣኝ ክፍል ኃላፊዎች ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ደጋፊዎችንም ለድንቅ ድጋፋቸው ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባ ገልፀዋል።


”ወልቂጤዎች ድንቅ ደጋፊዎች ያሉት ክለብ ነው። ይህንን ደግሞ እንደ በጎ መጠቀም አለብን። ቡድኑን እንደ 12ኛ ተጨዋች በመሆን ሁልግዜ መደገፍ እና ማበረታታት አለብን።” ያሉት አቶ አበባው ጨምረው ቡድኑ በፋይናንስ ደረጃ እንዲጠናከር በከተማው ያሉ ባለሀብቶች በአቅማቸው ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጥሪ አስተላልፈዋል። በመቀጠል የሽልማት ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን ለቡድኑ የከተማው አስተዳደር ለእያንዳዱ 158 ካሬ ሜትር እንዲሁም የ500,000 ሺ ብር ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን ዞኑ 3.5 ሚሊየን ብር ሽልማት አበርክተዎል።

ሀዲያ ሆሳዕና በዘንድሮ ውድድር ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን በማስመልከት ለተጫዋቹቹ እና ለአሰልጣኞቹ የሽልማት ስነ-ስርዓት አከናውኗል። ሀዲያ ሆሳዕና የ1.5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የመሬት ሽልማት ተበርክቷል። የመሬት ሽልማቱ በሆሳዕና ከተማ ላይ ከ100-150 ካሬ ሜትር ያካተተ ሲሆን ለአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ከሆሳዕና ስፖርት በዓመቱ ለገነባው ስብስብ እና ለመጣው ስኬት የቦርድ አመራሮች፣ የቡድኑ ተጫዋቾች፣ የደጋፊ ማኅበር ተወካዮች እና የክለቡ ደጋፊዎች ፊርማ ያረፈበት ስጦታ ተበርክቶለታል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ እንደገለፁት ” በሚቀጥለው ዓመት የተሻለ የውድድር ጊዜ ማሳለፍ እንችል ዘንድ ቀዳሚ ስራ እየሰራን ሲሆን የሜዳ ግንባታ እና የስፖርታዊ ጨዋነትን ጉዳይ ላይ እንሰራለን።” በማለት ከሶከር ኢትዮጵያ በነበቸው ቆይታ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡