በነገው ዕለት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የሚጀምሩት ምዓም አናብስት ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለመቀላቀል ተስማምተዋል።
ከሌሎች ቡድኖች ቀድመው ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚገቡት እና አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም በሰፊው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የሊግ ቻምፒዮኖቹ ከአርባምንጭ ከተማ ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ እና አማካዩ አለልኝ አዘነን ለማስፈረም ከስምምነት ሲደርሱ ካሉሻ አልሃሰንም ቡድኑን ለመቀላቀል ከስምምነት ደርሰዋል።
ባሳለፍነው ወር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በስምምነት የተለያየው የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የድሪምስ ጋናዊ አማካይ መቐለ 70 እንደርታ በኢትዮጵያ ቆይታው ሦስተኛ ክለቡ ይሆናል። በተለያዩ የአማካይ ክፍል ሚናዎች የሚጫወተው አል ሀሰን ካሉሻ ለመቐለ የማጥቃት አማራጭ አንደሚያሰፋ ይጠበቃል።
ሌሎች ክለቡን ለመቀላቀል የተስማሙት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአርባምንጭ ቆይታ ያደረጉት ተስፈኛ ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ እና አማካዩ አለልኝ አዘነ ናቸው። ከአርባምንጭ ታዳጊ ቡድን የተገኘው ፅዮን መርዕድ ባለፈው ዓመት የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው ግብጠባቂዎችን በልጦ የቋሚነት ዕድል ካገኘ በኋላ የቡድኑን ግብ በቋሚነት መጠበቅ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪም ለዋናው እና ለታዳጊ ብሄራዊ ቡድን መመረጥ ችሏል። አለልኝ አዘነ ሲሆን እሱም እንደ ፅዮን መርዕድ ሁሉ ከአርባምንጭ ታዳጊ ቡድን ወጥቶ ዋናውን ቡድን በቋሚነት ሲያገለግል የቆየ ተጫዋች ሲሆን በመሐል አማካይ እና ተከላካይ አማካይነት ይጫወታል።
ከሦስቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ኤፍሬም አሻሞን ለመቀላቀል የተስማማው መቐለ የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት በይፋ ያስፈርማቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡