ባህር ዳር ከተማ የቀድሞ ተጫዋቹን ሦስተኛ ፈራሚው አድርጓል

በተከታታይ ቀናት አንድ አንድ ተጨዋች እያስፈረሙ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች የቀድሞ ተጨዋቻቸውን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል።

ሳሙኤል ተስፋዬን እና ኤፍሬም ዓለሙን (መጠርያ ስሙን ወደ ፍፁም ዓለሙ ቀይሯል) በማስፈረም ወደ ዝውውር ገበያው የገቡት ባህር ዳር ከተማዎች ዛሬ ከሰዓት ሚኪያስ ግርማን ማስፈረማቸው ታውቋል። ከዚህ ቀደም ለአደድ ዓመት ከግማሽ በባህር ዳር መጫወት የቻለው ሚኪያስ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ወደ ምስራቁ የሃገራችን ክፍል ድሬዳዋ በማምራት ግልጋሎት ሰጥቷል። ከሁለቱ ክለቦች ቀደም ብሎ በቅዱስ ጊዮርጊስ የምናቀው ይህ የመስመር ተጨዋች ብዙም የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ማሳለፉ ይታወሳል።

ዛሴ ከሰዓት በተሰማ ዜና ይህ የመስመር ተከላካይ እና የመስመር አማካይ ቦታ ላይ መሰለፍ የሚችለው ተጨዋች ውሃ ሰማያዊ ለባሾቹን ባህር ዳሮች ለሁለት ዓመት ለማገልገል ተስማምቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እያለ ከአሁኑ የባህር ዳር አሰልጣኝ ስር የሰለጠነው ሚኪያስ ከዚህ ቀደም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው ቃለ ምልልስ እንደ አርዓያ እንደሚመለከተው የገለፀው ፋሲል ተካልኝን ተከትሎ ወደ ባህር ዳር አምርቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡