የአሰልጣኞች ገጽ | አብርሀም ተክለሃይማኖት (ክፍል ሁለት)

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው “የአሰልጣኞች ገፅ” አሰልጣኝ አብርሀም ተክለሃይማኖትን በተከታታይ እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። ከ30 ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት ሙያ ያሳለፉት እና በአሁኑ ወቅት የህፃናት ማሰልጠኛ ማዕከል በመመስረት የታዳጊዎች ስልጠና ላይ የተሰማሩት አሰልጣኝ አብርሀም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ዘለግ ያለ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቆይታ አድርገዋል። በዛሬው የክፍል ሁለት ዝግጅታችንም አሰልጣኙ ያሳለፉትን የአሰልጣኝነት ህይወት እና ተያያዥ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ እናደርጋለን።


በአሰልጣኝነት ሥራ ላይ የማትገኘው የክለብ ሥራ አጥተህ ወይስ ስላልፈለግህ ነው?

★ የራሴን ሥራ መስራት ፈልጌ ነው፡፡ በእርግጥ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሌላ ሥራ መሥራት ጀምሬ ነበር፡፡ ገንዘብ ይገኝበታል፤ ነገርግን እርካታ ላገኝበት አልቻልኩም፡፡ ከዚያ ተውኩት፡፡ የክለብ አሰልጣኝነትም አላጣሁም፤ ነገርግን ለሃገር የሚጠቅምና ራሴንም በምፈልገው መስክ ለማሰማራት ወስኜ ነው የጀመርኩት፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ለታላቅነት አብቅቼዋለሁ፤ በርካታ ችግሮችን ተጋፍጬም ቡድኑን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ እንዲሆን አድርጌዋለሁ፡፡ያልክለት ጉና ክለብ ከአንተ ዘመን በኋላ መጨረሻው መፍረስ ሆኗል፡፡ ክለቡን ምን ገጠመው

★ እንግዲህ ለማንም ተናግሬ የማላውቀውን ዛሬ ልናገረው! በጉና ንግድ የስፖርት ክለቡ ሃላፊና ዋና አሰልጣኝ ሆኜ ነበር የተቀጠርኩት፡፡ ቀጣሪዎቼ አሁንም አሉ፤ ይህ ጽሁፍ ሲወጣ አሳያቸዋለሁ፡፡ አንደኛው የእንደርታ ተጫዋች የነበረውና ኋላ ላይ ታጋይ የሆነው ግርማይ ዳቦ ነው፡፡ የጉና ድርጅት መስራች ሲሆን በትራንስ ኢትዮጵያም በምክትል ሥራ አስኪያጅነት አገልግሏል፡፡ ከትግል ሜዳ ሲመለስ እኔ እግርኳስ ውስጥ ሆኜ ጠበቅሁት፤ “በመቀሌ ጉና የሚባል ቡድን ስለምንመሰርት እዚያ ሂድ፡፡” አለኝ፡፡ ያን ጊዜ እኔ በምድር ባቡር ውስጥ ነበር የምሰራው፤ እግርኳስ ከመውደዴ የተነሳ በማታው ክፍለ ጊዜ በዲግሪ መርኃግብር አምስተኛ ዓመት የደረስኩበትን የጂኦግራፊ ትምህርቴንና የተለያዩ ጥቅማ-ጥቅሞቼን ትቼ በቀጥታ ወደ መቐለ አመራሁ፡፡ በክለቡ ቤቴን ያህል እየተሰማኝ በታማኝነት ለአስር ዓመታት ያህል ሰራሁ፡፡ በጣም ጉጉ ከመሆን በመነጨ እርስ-በርሳችን ባለመስማማት የተወሰኑ ችግሮች ቢገጥሙንም ከዓመት-ዓመት ለውጦችን እያመጣን ዘለቅን፡፡ ቀስ በቀስ ከስፖርት ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር “የእኔ ነው ትክክል- አይደለም- የእኔ ነው ትክክል!” በሚል የሐሳብ ልዩነቶች አላስፈላጊ ደረጃ ላይ ተዳረስን፤ እዚህ ያሉት አለቆችም እኛን ለመቅጣት ማሳደድ ያዙ፡፡ በእርግጥ ያኔ እኔም ‘አልተሳሳትኩም፡፡’ አልልም፡፡ ወጣትነቴ፣ የራስ መተማመኔ፣ የግል ዕምነቴና ሌሎችም ባህሪዮቼ ግትር አድርገውኝ ነበር፡፡ በተለይ በራስ የመተማመን መንፈሴን በፍጹም መሸርሸር አልፈልግም፤ በዚህ የማሳየው አቋም ዝንፍ የማይል ስለነበር በራሴ እምነት ጸናሁ፡፡ ክለቡ በጥሩ ጎዳና እየተጓዘ፣ አመራሮች በአግባቡ እየደገፉን ብዙ ቆየን፡፡

በእውነቱ ያን ጊዜ ጥሩ-ጥሩ መሪዎች ነበሩን- አቶ ግርማይ ነበር፤ ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ዘርዓያዕቆብ-ኤርትራዊ ስለነበር ወደዚያ ሄዷል፤ አቶ ኃይሉ ጉና የተባሉ ኃላፊም ነበሩን፡፡ እነዚህ ሰዎች ከበታቾቻቸው ጋር እንድ ሆነው በመሥራት ወደር አልነበራቸውም፡፡  በዚህም ምክንያት ክለቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ ቻለ፡፡ ኋላ ላይም አቶ ሰይፉ አምባዬ- የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤት ስራ አስፈጻሚ- የክለባችን ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ፡፡ በእርሳቸውም ሥር ከፍተኛ ድጋፍ ይደረግልኛል፤ ሙሉ ዕምነት ተጥሎብኝም በመልካም ሁኔታ እሰራለሁ፤ የፈለግሁትን የመወሰን መብትም ስለነበረኝ ፈጣን እድገት አመጣን፡፡ ይህን ሁሉ እያደረግንም ደጋፊ አልነበረንም፤ ቡድኑ ህዝብ ልብ ውስጥ መግባት ተሳነው፡፡ ጉና ምንድን ነው? እንግዲህ ጉና በአማራ ክልል የሚገኝ የኢህአዴግ ጦር በርካታ ውጊያዎችን ያካሄደበት ተራራ ነው፡፡ ድርጅቱ በዚያ ቦታ ስም ተጠራ፤ ክለቡም በዚሁ ተሰየመ፡፡ ነገርግን በአካባቢው ሰው ድጋፍ አላገኘም፡፡ ስለዚህ እኔ ‘የክለቡን መጠሪያ ለምን መቐለ አንለውም?’ የሚል ሐሳብ አነሳሁ፡፡ ከዚያ “ይሄ መንደርተኝነት ነው፡፡” ተብሎ ተቃውሞ ገጠመን፤ በጥያቄው ሊገፋበት የወደደ ሰው ስላልነበረም በዚሁ ቀረ፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም “ይሄ የመቐለን ልጆች ለማሰባሰብ የታለመ ነው፡፡” ብለው ለመክሰስ ሞከሩ፡፡ ስለዚህ ሐሳቡ ገና ከእንጭጩ ተቀጨ፡፡ ኋላ ድርጅቱም ክለቡን ማስተዳደር ከአቅሙ በላይ እየሆነበት ሄደ፤ እኔም ማደግ ፈለግሁ፡፡ አስር ዓመት ሙሉ ስሰራ በስፖርት አመራሩ በኩል የአመለካከት ለውጥ ማየት አልቻልኩም፡ ሰለቸኝ፡፡

እንዳጋጣሚ ሆኖ እኔና ገብረመድህን አንድ ላይ ወጣን፤ እሱ ባንኮችን-እኔ ቡናን ያዝን፡፡ ታዲያ ሁለታችንም ክለብ ካገኘን በኋላ ነው የተነጋገርነው፡፡ በመጀመሪያ “እንውጣ!” ተባብለን አልተመካከርንም፤ እኔ እንደዚያ አላስብም፤ እሱም ፍጹም ሊያስብ አይችልም፡፡ በወቅቱ ሁኔታውን ስናይ ስም ማጥፋት፣ ጭቅጭቅና ክስ በዛ፡፡ እኔ ያጠፋሁት ጥፋት፣ ያለአግባብ የበላሁት ወይም የሰረቅሁት ነገር አልነበረም፤ አመራሩ በጣም ያምነኝ ነበር- ቼክ እስከ መፈረም የደረሰ ሥልጣን ነበረኝ፡፡ ታማኝነቴን አልፌ ለግሌ ያደረግሁት ነገር የለኝም፡፡ በ1996 መጨረሻ እኔ ከጉና-ወደ-ቡና፣ ገብሬ ከትራንስ-ወደ-ባንኮች ተዘዋወርን፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት የነበረውና አሁን አሜሪካ ያለው አቶ ብዙዓየሁ ዮሐንስና አቶ ተስፋዬ ካህሳይ ሊያነጋግሩኝ ሲቀጥሩኝ የመጨረሻ ጨዋታችንን ከቡና ጋር ከማድረጋችን ቀደም ብለው ነበር፡፡ እንጦጦ ላይ የጉናን ተጫዋቾች ልምምድ እያሰራሁ ሳለ ደውለውልኝ “እንፈልግሃለን፤ ስትመለስ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንጠብቅሃለን፡፡” አሉኝ፡፡ እኔም ልምምዱ እንደጨረስኩ ወዳረፍንበት ገነት ሆቴል አመራሁ፤ ትጥቄን አወላልቄ ተጣጠብኩ፤ ትንሽ አረፍኩና ምሳ በልቼ ወደ ቀጠሮዬ አቀናሁ፡፡ እዚያ ስደርስ ሁለቱም ሰዎች በቦታው ጠበቁኝ፡፡ ከዚያ በፊት አቶ ብዙአየሁን አውቀዋለሁ፤ አቶ ተስፋዬን ግን አላውቀውም ነበር፡፡ ቁጭ ካልኩ በኋላ ‘ነገ ተጋጣሚያቸው ሆኜ እንዴት ክለቡን እንድይዝ ይጠይቁኛል? ምንድን ነው ነገሩ?’ ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ እንግዲህ ይሄ የራሴ ጥያቄ ነው፡፡ በዚያ ላይ ቡድናቸው እስከ መጨረሻው ድረስ ለዋንጫ የሚፎካከርበት ዓመት ነበር፡፡ ከንቱ ተጠራጣሪነት እንጂ ያሰብኩት ትክክል አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ ‘እሺ ላስብበት፡፡’ አልኳቸው፤ በቀጣዩ ቀን ጨዋታውን አከናወንንና 3-1 ተሸነፍን፤ ያኔውኑ ማታ ሲጠሩኝ ‘ እነዚህ ሰዎች እውነታቸውን ነው፡፡’ አልኩና ሄጄ አወራኋቸው፤ በቃል ተስማማን፡ ለቤተሰቤም ሄጄ ዜናውን አበሰርኩ፡፡ መቐለ በጣም የምወዳቸው ጓደኞች አሉኝ፤ ከእነርሱ ጋር ተሰብስበን ስንመካከር ግማሾቹ ” አትሄድም፤ ትጠፋለህ፡፡” ሲሉኝ ሌሎች ደግሞ ” መሄድ ይኖርብሃል፡፡” አሉኝ፡፡ በመጨረሻም የእኔ ምላሽ ምን እንደሆነ ጠየቁኝ፤ እኔ ደግሞ “ገና ጎጆ መቀለሴ ነው- ጉናም በጀቱ እየቀነሰ ሄዷል፤ ስለዚህ መሄድ አለብኝ፤ ራሴን መፈተሽ እፈልጋለሁ፡፡” አልኳቸው፡፡ ከዚያ ስለ ውሳኔዬ ላማክረው ገብሬን ጠርቼ ሳወራው ” እንዴ እኔም’ኮ ወደ ባንኮች መሄዴ ነው፡፡” አለኝ፡፡ በእርግጥ ክልሉ አፍርቶናል፤ ከልጅነታችን ጀምሮም የነበርንበት ደረጃ ላይ አድርሶናል፤ ይህንን አንክድም፤ ግን ደግሞ ራሳችንን ማሳደግ ነበረብን፡፡ ብዙ መሃንዲሶችና ዶክተሮች ከዚያ ወጥተው ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል፤ ስለዚህ  ” እኛም እዚያው ተገድበን መቅረት የለብንም፤ ሙያችንን ማዳበር ይኖርብናል፡፡” ከሚል አመለካከት ተነስተን ወሰንን፡፡ ከዚያ በኋላ እንደገመትኩት ክለቦቹ በሒደት ተንኮታኮቱ፤ እንደሚፈርሱ አውቅ ነበር፡፡ ክለቦቹን ማስተዳደር ከድርጅቶቹ  አቅም በላይ ሆነ፡፡ የክልሉ ወጣቶችን የማፍራት ሒደቱ እስካሁንም ቀጥሏል፤ አሁንም ድንቅ-ድንቅ ተጫዋቾች ከክልሉ እየወጡ ነው፡፡ ከጉና ጋር የነበረኝ ጊዜ በዚህ መልኩ ነው የተጠናቀቀው፡፡

ክለቦቹ እንዳይወርዱ፣ ከወረዱም እንዳይፈርሱ እና ህልውናቸው ዘላቂ እንዲሆን ጠንካራ መሰረት ጥሎ የማለፍ ጥረት አልተደረገም?

★ እንደ አሰልጣኝ ተተኪ ወጣቶችን በማዘጋጀት ረገድ ያን ማድረግ ተችሏል፤ ወጣት አሰልጣኞችም ቢሆን ወደ ሙያው እንዲገቡ ተደርጓል፤ እነ የማነና ዳንኤል ጸሃዬን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ድርጅቱ ግን መቀጠል አልፈለገም፤ ስለዚህ ክለቡን አፈረሰው፡፡ ሙገር እያሰለጠንኩ ሳለ አንድ ጊዜ ሄጄ ሥራ አስኪያጁን አናግሬዋለሁ፤ ‘ ክለቡ ለምን ይፈርሳል?’ ብዬ ጠይቄአለሁ፡፡ በቀጥታ ባያገባኝም የክልሉ እግርኳስ ስለሚመለከተኝ ለትራንስ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅም ጥያቄ አቅርቤያለሁ፡፡ በወቅቱ ኃላፊዎቹ ” ተተኪዎች ማፍራት ነው የምንፈልገው፤ ስለዚህ አካዳሚ እንከፍታለን፡፡” የሚል ምላሽ ቢሰጡኝም ይኸው እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አላደረጉትም፡፡ ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ እቅድ ነበር ያወጡት ግን አልሆነም፡፡ እኔ አሁንም ክትትሌን አላቆምኩም፤ የእኔ አካዳሚም ታዳጊዎችን የማውጣት ሐሳብ ፍሬ ነውና፡፡

የመጀመሪያ የአሰልጣኝነት ኮርስን 1977 በምድር ባቡር ክለብ በሰራተኞች ጉዳይ አስፈጻሚ ቢሮ እየሰራህና በተጫዋችነት እያገለገልክ እንደወሰድክ መጽሃፍህ ላይ ገልጸሃል፡፡ የወቅቱ የምድር ባቡር ክለብ ዋና አሰልጣኝ እገዛን እናውሳ

★ በምድር ባቡር ጠዋት-ጠዋት በአስተዳደር ቢሮ- በፐርሶኔልነት፥ ከሰዓት ደግሞ በተጫዋችነት እሰራ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ማህበር ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ተፈራ ዋሲሁንም በድርጅቱ ይገኙ ነበር፡፡ ቀደም ሲል የኦሜድላና የብሄራዊ ቡድናችን ተጫዋች የነበረው ኃይሉ ጎሹ ደግሞ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት መርቶታል፤ በተጫዋችነት በርካታ አለምዓቀፍ ተመክሮዎች የያዘው ኃይሉ በጣም ጎበዝ አሰልጣኝም ነበር፡፡  ነገርግን የአሰልጣኝነት ላይሰንስ አልነበረውም፡፡በምድር ባቡር ድርጅት ድጋፍ በጃንሜዳ የስድስት ወር የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስጄ <Licenced Coach> ሆንኩ፤ ቡድኑም በእኔ የአሰልጣኝነት ሰርተፊኬት እንዲጫወት ተደረገ፡፡ በጊዜው እየተጫወትኩ ለአሰልጣኞቼ ሐሳብ እሰጥና አንዳንዴ እከራከር ስለነበር ለአንድ ሰው የመማር እድል ሲመጣ ሁሉም እኔን መርጠው ላኩኝ፡፡ ተማርኩ፤ የ<B-ቡድን> ተሰጠኝ፤ ዮናስ፣ አባይ ሰለሞን/ሪኔ (ዝነኛ የቡና ተጫዋች የነበረና አሜሪካን ሃገር በመኪና አደጋ የሞተ)፣ ፍሬዘር ቶማስ፣ አሰፋ ሲማ፣ ያሬድ ኮምቦሮ፣… የመሳሰሉት በእኔ ሥር የ<B-ቡድኑ> አስገራሚ ችሎታ የያዙ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ቀጠልኩና በዋናው ቡድን የኃይሉ ጎሹ ምክትል ሆኜ ተሾምኩ፤ ቡድናችንም ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አለፈ፡፡ ልክ 1983 የመንግስት ለውጥ ሲደረግ እኔ በ1984 ከድርጅቱ ለቀቅሁ፡፡ ለአንድ ዓመትና የተወሰኑ ወራት በአሰልጣኝነት ሳልሰራ ቆየሁና በ1986 ወደ ጉና ሄድኩ፡፡

አንተን ጨምሮ ብዙ የሃገሪቱ አሰልጣኞች የሙገር ክለብ ቆይታቸውን የሚያስታውሱት ከሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦች በተለየ በመልካም ጎኑ ነው፡፡ ካሳሁን ተካ፣ ሰውነት ቢሻው፣ አዳነ ገብረየስ፣ ግርማ ሃብተዮሃንስና የመሳሰሉት በዚህ በድን ምቾት ተሰምቷቸው እንደሰሩ በተለያዩ ጊዜያት መስክረዋል፡፡ ምክንያቱ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ከነበሩት ኢንጂነር ግዛው ተክለማርያም ጋር የሚያያዝ ይሆን

★ የጥሩ አመራር ውጤት ነው፡፡ በሙገር ለአሰልጣኞች ምቹ የሆነ ከባቢ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ኢንጅነር ግዛውም በክለቡ የእግርኳስና አትሌቲክስ ቡድኖች አያያዝ ደማቅ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ ቀደም ሲል ትልልቆቹ ክለቦች ያላደረጉትን ሙገር ሲሚንቶ ግን የወጣቶች ማሰልጠኛ ማዕከል አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ኃላፊዎቹ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎች ከየክልሉ ተመርጠው በዚህ ማዕከል ውስጥ እየሰለጠኑና እየተማሩ የሚዘልቁበትን ሒደት አመቻቹ፡፡ ሁላችንም በዚህ ሁኔታ ስለሰራን ጠንካራ ቡድን ልናቀርብ ችለናል፡፡ እኔ በሙገር ጥሩ ስብስብ ነበረኝ፤ የሌሎቹን ባላስታውስም የሰውነትና የካሳሁንም እንዲሁ ምርጥ ቡድኖች ነበሩ፡፡ በእርግጥ እኔ ክለቡን የተረከብኩት ኢንጅነር ከለቀቁ በኋላ ቢሆንም በእርሳቸው ሥር የነበረው የተሻለ የስፖርት አመራር ባህል ቀጥሎ ነው የጠበቀኝ፡፡ በመረብኳስና አትሌቲክስም በሃገሪቱ ቶፕ ደረጃ ደርሶ ነበር፡፡ የሙገር እግርኳስ ቡድን ልምምዱን አዲስ አበባ ላይ እየሰራ ለጨዋታ አምቦ ይሄድ ነበር፡፡ በዚህም ዋናው ፋብሪካ ያለበት አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ጨዋታ እንዲያይ፣ እንዲዝናና እና ድጋፍ እንዲሰጥ በማድረግ ስፖርቱ አሳታፊ መድረክ እንዲሆን ተጥሯል፡፡ ይሄ ትልቅ ስፖርትን የማስተዳደር ችሎታን ማሳያ ነው፡፡

አንተም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነህ ስትመረጥ የሙገር ውልህን ሳታቋርጥ በቀጥታ ነው ኃላፊነቱን የተረከብከው? የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት አጓጊ ይሆን?

★ትክክል ነው የሙገር ውሌን ሳላቋርጥ ኃላፊነቱን ተረክቤያለሁ፤ ነገርግን ጓጉቼ አልነበረም፡፡ የቅጥር ፈተና ተሰጠ፤ በጥሩ ውጤት አለፍኩ፡፡ ሙገር ክለብ ደግሞ የማንኛውም ሰራተኛውን እድገት ይፈልግ ስለነበር ተባበረኝ፡፡ ስለዚህ ውሌን ማቋረጥ አልተጠበቀብኝም፡፡ እኔ እስካሁንም እንደ ሙገር አይነት መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ክለብ አይቼ አላውቅም፡፡ ሙገር እኮ የምትፈልገውን በአግባቡ ሰርተህ ጥሩ እንቅልፍ የምትተኛበት ክለብ ነው፡፡ ሌላ ቦታ ጠንክረህ ሰርተህም ተንኮል፣ ክፋት፣ ምቀኝነት፣… ይገጥምሃል፡፡ ሙገር እንዲህ አይነት አሉታዊ ነገሮች የሉም፡፡ ከእኔ ጋር ተባብረው የሚሰሩ በጣም ጥሩ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጥሩ ሥራ አስኪያጅ ነበረን፡፡ የድርጅቱ ሰራተኞች በሙሉ ቅን አሳቢዎች ነበሩ፡፡ እንደ ሙገርማ የሚሆን ቦታ አልነበረም፡፡ በክለብ አሰልጣኝነት ስራዬ ጉና እና ሙገር ናቸው ለእኔ የተመቹኝ፡፡ መተሃራም በተመሳሳይ ጥሩ ጊዜ አሳልፌያለሁ፤ እንዲያውም እነርሱ ውል አፍርሼባቸው አስቀጥተውኛል፡፡ ፌዴሬሽኑ የውል ማፍረሻ ቅጣት እንድከፍል አድርጎኝ ነው የወጣሁት፡፡ ሙቀቱ ከበደኝ፤ ከትንንሽ ልጆቼ ራቅሁኝ፤ የኑሮ ሁኔታዬ አልተመቻቸም፤ ስለዚህ መልቀቅ ነበረብኝ፡፡

በወቅቱ ብሄራዊ ቡድኑ ሲቀጣ ለሁለት ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ ያህል በቴክኒክ ኮሚቴ አባልነት ነው ስትሰራ የከረምከው?

★ እኔ በብሄራዊ ቡድኑ የሁለት ዓመት ኮንትራት ፈረምኩ፤ ብዙም ሳንጓዝ ገና ከጅምሩ ተቀጣን፡፡ በሁለት ሳምንት ዝግጅት ካዛብላንካ ሄደን በሞሮኮ 3-0 ተረታን፤ እዚህ በሩዋንዳ ተሸነፍን፤ ሶስተኛውን ጨዋታ ለማካሄድ ሞሪታኒያ ሄደን 1-0 አሸነፍን፡፡ በሞሪታኒያው የመልስ ጨዋታ በአዲስ አበባ 6-1 ድል አደረግን፡፡ ከዚያ የሞሮኮውን የመልስ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ሳናደርግ የፊፋ ቅጣት መጣ፡፡ በሜዳችን በሩዋንዳ የተሸነፍንበት ጨዋታ አሳማኝ አልነበረም፤ እነ ደጉና ሙሉጌታን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ያካተተ ጥሩ ቡድን ነበረን፡፡ እነ ሳላዲንም ከሙገር ወጥተው የጎመሩበት ዘመን ነበር፡፡ ጥሩ ወጣቶችን ያሰባሰበና ብዙ ብሰራበት ኖሮ ደህና ደረጃ እንደርስ ነበር፡፡ ሶስትና አራት ወራት ብቻ ሰርቼ ቅጣቱ ከተፍ አለ፡፡ በነገራችን ላይ ያ ቡድን ነው በሒደት መጠነኛ ማሻሻያዎች ተደርጎበት ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው፡፡ ከዚያ ወደ ቴክኒክ ክፍል ተዛውሬ በቴክኒክ ኃላፊነት መስራት ጀመርኩ፡፡

በጊዜው የደመወዝህ ጉዳይ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ሰባት ሺህ ብር ወርሃዊ ደመወዝና የሁለት ዓመት ኮንትራት ለብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የተለመደ አልነበረም፡፡ ከዚያ በፊት የሃገሪቱ ዋና ብሄራዊ ቡድን ውድድሮች ሲኖሩ በሚመረጡ አሰልጣኞች እንጂ የሙሉ ጊዜ አሰልጣኝ (Full-Time Coach) አግኝቶ አያውቅም፡፡ ይህ ያልተለመደ ሹመት ብዙዎችን ከቴክኒካል ጉዳዮች ይሎቅ ኮንትራትህና ክፍያህ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉ ምን ያህል ተጽዕኖ ፈጠረብህ? 

ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ከቅጥሩ ጀምሮ አዲስ አሰራር ታይቷል፤ በፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆንኩት እኔ ነኝ፡፡ በጊዜው ይህኛውን አሰራር ያልተቀበሉት ሰዎች ገጥመውኛል፤ በአደባባይ በተሰጠ ፈተና እንጂ በሰው አልተሾምኩም ደመወዙን በተመለከተም ሰባት ሺህ ብር ብዙ ነበር- እውነት ነው፤ መነጋገሪያም ሆኗል፡፡ እስካሁን የሚያስገርመኝ ጉዳይ ግን እያንዳንዱ ጋዜጠኛ በራሱ መንገድ ይጠይቃል፡፡ ለሁሉም መልስ መስጠት ደግሞ ሥራ ያስፈታል፡፡ “እምቢ!” ካልክ የሚጠብቅህ ስድብ ነው፡፡ እንዳሁኑ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ሞሮኮ የሄድኩ ጊዜ ነው ስለ ጋዜጣዊ መግለጫ ያወቅሁት፡፡ በወቅቱ የፌዴረሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ አህመድ ያሲን ጋዜጣዊ መግለጫ መሥጠትን አስጀምረውልን ነበር፡፡ አሁን ጥሩ ይመስለኛል፤ ሥርዓት ይዟል፡፡

1997 በኢትዮጵያ ቡና በተዘረጋው አዲስ አወቃቀር የክለቡ ዋና አሰልጣኝ እና የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነህ ተሾምክ፡፡ ይህም ድርብ ኃላፊነት ለአንተ አዲስ እና የመጀመሪያህ ነበር?

እውነት ነው አዲስ ሹመት ግን ደግሞ ከባድ ኃላፊነትም ጭምር ነበር፡፡ የክለቡ ሐሳብ ዘመናዊ አሰራርን ለመከተል ያለመ ቢሆንም በውስጡ ሰፊ የሥራ ድርሻዎች ተካተዋል፡፡ የ<B> ቡድን፣ የወጣት ቡድን፣ በአስሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ታዳጊ ቡድኖችም ነበሩ፡፡ ነገርግ ኢትዮጵያ ቡናን በሚያክል ቡድን ውስጥ አሰልጣኝም ቴክኒክ ዳይሬክተርም መሆን አዳጋች ነው፡፡ ያኔ እኔም እንደከበደኝ አውቄዋለሁ፡፡ በእርግጥ መቐለ ሆኜ ከቡና በደረጃ ዝቅ ባለ ክለብ ስለነበርኩ ሚናውን በአግባቡ ተወጥቼዋለሁ፡፡ ቡና ስመጣ ግን አስቸጋሪ ሆነብኝ፤ ቴክኒካል ዳይሬክተርነት እጅግ ከባድ ሥራ መሆኑንም የተገነዘብኩት ያኔ ነው፡፡

ከአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ጋር አብሮ የመሥራት እድል አግኝተሃል? 

★ አላገኘሁም፤ አብሬውም አልሰራሁም፡፡ እርሱ ሲወጣ እኔ ገባሁ፤ እኔ ስወጣ ደግሞ ሥዩም ተመለሰ መሰለኝ፡፡

በምክትልነት ያገለገልካቸው አንጋፋ አሰልጣኞች የሉም?

★ አንደኛው የእኔ አመጣጥ ችግር የሚመስለኝ በምክትልነት ሰርቼ አለማወቄ ነው፡፡ በምድር ባቡር እያለሁ በኃይሉ ጎሹ ሥር ለአንድ ዓመት ያህል ሰርቼ በርካታ ትምህርቶችን ተምሬያለሁ፤ ኃይሉ ቅን ሰው ነበር፡፡ ያን ጊዜ እኔ ገና ወጣት ስለሆንኩ “ነይ አንቺ!” እያለ ያስተምረኝ፣ ያሰለጥነኝና ኃላፊነት ይሰጠኝ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አብዛኛውን ጊዜ ከራሴ ስማር ነው የኖርኩት፡፡ የሆነ ጊዜም በትግራይ ምርጥ ቡድን ከገብረመድህን ኃይሌ ጋር በምክትልነት ሰርቻለሁ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲሁ ለአንድ በሩዋንዳ የሚካሄድ የደርሶ መልስ ጨዋታ አሰልጣኝ አብርሃም መብራህቱ “ምክትሌ ሁን፡፡” ብሎ ሲጠይቀኝ ምክትል ሆኜለታለሁ፤ እንዲያውም የተወሰኑ ሰዎች “አንተ <ሲኒየር> ሆነህ እንዴት ለአብርሃም ምክትል ትሆናለህ?” በማለት ተቆጥተውኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ‘ይህ ሥራ ነው፤ ሙያ ነው፤ እማርበታለሁ፡፡’ ብዬ ሰርቻለሁ፡፡ ከእነዚህ ውጪ በረዳትነት የሰራሁበትን ዘመን አላስታውስም፤ የለኝምም፡፡ ይሁን እንጂ ረዘም ላሉ ጊዜያት ምክትል አሰልጣኝ ሆኜ ባለመሥራቴ ይቆጨኛል፤ ይህ አመጣጤ ከአንጋፎቹ የመማር እድል ነፍጎኛል፡፡

1990ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት የጉና ጠንካራ ጎን ምንድን ነበር?

★ Discipline! ብዙ ተጫዋቾች ጉና ሲመጡ ሀ-ብለው ስለ ስነ-ምግባር ይማራሉ፡፡ ነፍሱን ይማረውና እስራኤል መኮንን የሚባል የሐረር ልጅ ነበረኝ፡፡ መቐለ መጥቶ በአንደኛው ዙር አስራ ሁለት ጎሎች አስቆጥሮ ከኮብ ግብ አግቢነቱን ይመራ ነበር፡፡ በርካታ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ቦታዎች እየመጣ ለእውቅና እንዲበቁ የሚያደርግበት ዋነኛ መሳሪያው ስነ-ምግባር ነው፡፡ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ-ምናልባት ከአስራት ኃይሌ ቀጥሎ ዲሲፕሊን በማስከበር እኔ እጠቀሳለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በተጫዋቾች ሥነ-ምግባር ላይ ጠንካራ አቋም ነው ያለኝ፡፡ ጉናም ተጫዋቾችን በስነምግባር የሚያንጽና በሥራ የሚያምን ክለብ ነበር፡፡

ጉና ለእንግዳ ቡድን የሚያደርገው አቀባበል ልዩ እንደነበር ይነገራል፡፡ 

★ ጉና በዚህ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓታችን በእግርኳሱ ከባቢ ላይ ትልቅ ለውጥ ፈጥሯል፡፡ከመብራት ሃይል ሰዎች ብዙ ትምህርት ወስጃለሁ፤ የክለቡ አመራሮች እነ አቶ አርአያ፣ ጋሽ ክፍሌ፣ አቶ ቤተማርያምና የመሳሰሉት ከእኛ አለቆችም ሆነ ከእኔ ጋር የጓደኛ ያህል እንቀራረብ ነበር፡፡ ልክ ለሁሉ ቡድኖች እንደምናደርገው ሁሉ ወደ መቐለ ሲመጡም ጥሩ አቀባበልና አሪፍ ግብዣ እናደርግላቸዋለን፡፡ ከጨዋታ በኋላ ተሸንፈን እንኳ ተገባብዘን ነበር የምንሸኛቸው፡፡ አንዳንዴ የሙዚቃ ባንድ ሳይቀር አስመጥተን የደስታና መዝናናት ሥሜት እንፈጥር ነበር፡፡  አስታውሳለሁ-አንድ ጊዜ ቡና መቐለ መጥቶ አሸነፈን፤ ማታ ጥሩ ግብዣ አደርግንላቸው፤ ስዩም አባተ በጣም ገርሞት ” እንዴ! አትናደዱም እንዴ!” አለኝ፡፡ ” ለምን እንናደዳለን? እግርኳስ’ኮ ነው፤ ከእናንተ ለመማር እየጣርን ነው፡፡ እኛ ገና አዳጊዎች ነን፤ ጭራሹኑ እግርኳስ ጠፍቶ የነበረበት ክልል ነው፡፡ ስለዚህ አንናደድም፡፡” አልኩት፡፡

ከጊዮርጊስ ጋርም እንዲሁ ልዩ ወዳጅነት ፈጥረናል፡፡ በፈረስና በሞተር ሳይክል አጅበን ነው ከአየር ማረፊያ ወደ ከተማው ያስገባናቸው፡፡ እኛ እዚህ ስንመጣም በ1991 በአጋጣሚ እኔ ብራዚል ሄጄ ስለነበር ግብዣው ላይ ባልታደምም ከደጋፊዎች ወደ አርባ ሺህ ብር ተዋጥቶ የሸራተን ባስ ለአንድ ሳምንት ተፈቅዶልንና ለአሰልጣኛችን መርሴዴስ መኪና ተመድቦለት ነው የተጋበዝነው፡፡ ያኔ እንግዲህ ይህን መሳይ መንፈስ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ያንን ሰላማዊ ድባብ ስለማውቅ ነው ” አሁን ሊግ ለምን ይፈርሳል?” የምለው፡፡ ያ ሁሉ መስርተነው የነበረው ወዳጅነታችን የት ገባ? አሁንም የያኔዎቹ የጊዮርጊስ ኃላፊዎች አሉ፤ ያኔ በኢምፔሪያል ሆቴል የተደረገውን ደማቅ ግብዣ የሚያሳዩ ፎቶዎች የተሰባሰቡበት አልበምም እስካሁን ተቀምጧል፤ የመቐለውም እንደዚያው፡፡ የእግርኳስ ሊግን በዚህ መንፈስ መስርተን አሁን የሚያጣላን ምንድን ነው? የማያስማማንን ባዕድ ነገር እናውጣው፡፡ ከኳስ ውጪ የሆነውን ጉዳይ እናስወግደው፡፡ የኢትዮጵያን እግርኳስም ወደ ጥሩ መስመር እንምራው፡፡

በሰበታ ብዙ አልሰነበትክም፡፡ ምን ችግር ገጠመህ?

★ እኔ የሰበታ ቆይታዬ አልተመቸኝም፤ ስብስቡ ብዙ ስላላሳመነኝ እንጂ ክለቡ ምንም አድርጎኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ ታህሳስ 21-2003- ለቅቄ ወጣሁ፤ እነርሱም ምንም አላሉኝም፡፡ የያኔው ከንቲባ ሽመልስ ሐሰን በጣም መልካም ሰው ሲሆን ብዙ ድሆችን ባለጸጋ ያደረገ ጥሩ መሪ ነው፡፡ በሰበታ ከተማሜ በጣም ተወዳጅ ከንቲባ ነበር፡፡ እኔንም መጀመሪያ “ና! ሰበታን አሰልጥን!” ብሎ የወሰደኝም ሽመልስ ነበር፡፡ እናም እርሱ ከለቀቀ በኋላ ሁኔታዎች ተቀያየሩ፤ አንዳንዶች እጃቸውን ማስረዘም ጀመሩ፤ የተጫዋቾቹን ስብስብ ስታይ የበርካታ ክለቦች አሻራ ያረፈባቸው ነበሩ፡፡ እነዚህን ተጫዋቾች ወደ አንድ ለማምጣት ረጅም ጊዜ ይጠይቃል፡፡ እኔ በሒደት ችግሮቹን ለማስተካከል አቀድኩኝ፤ እነርሱ ግን በአጭር ጊዜ ውጤት ፈለጉ፤ አልተግባባንም፤ ትቼ ወጣሁ፡፡ በእርግጥ ሙሉአለም ረጋሳን የመሰለ ጥሩ ባህሪና ችሎታ የያዘ ረዳት ነበረኝ፤ እስከ አርባ ዓመት መጫወት መቻልም የዚህ ስብዕና ውጤት ነው፡፡

የሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የቅጥር ጥሪው ያልጠበቅኸው ነበር?

★ በወቅቱ ፌዴሬሽኑ ችግር ላይ ይገኝ የነበረ ይመሥለኛል፡፡ ከሰበታ በለቀቅሁበት ምሽት ቤቴ ቁጭ ብዬ ስልክ ተደወለልኝ፡፡ አቶ አሸናፊ እጅጉ ነበር፡፡ ‘ምነው- ከመሸ ምን ገጠመህ?’ አልኩት፡፡ “ፌዴሬሽኑ የወሰነው ነገር ስላለ ነገ ቢሮ እንጠብቅሃለን-ና!” አለኝ፡፡ በማግስቱ ለመነጋገር ሄጄ እዚያው አስፈረሙኝ፡፡ ከሰዓታት በኋላ ወንድሜ ጀነራል አበበ ደወለልኝና ” ቴሌቪዥን ያለበት አካባቢ ነህ?” ሲለኝ ‘ አይ-አይደለሁም፤ ከጓደኞቼ ጋር ስታዲየም አካባቢ ምሳ እየተመገብኩ ነኝ፤ ምነው?’ አልኩት፡፡ ” ‘አብርሐም ተክለሃይማኖት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ፡፡’ የሚል ዜና በኢቲቪ እየታየ ነው፡፡” አለኝ፡፡ “ስምንት ሰዓት ላይ ተገኝ፡፡” ተባልኩ፤ ሄድኩ፤ ጨረስኩ፡፡

እንግዲህ ነገሩ እዚህ ከደረሰ ወደኋላ ማለት የለብኝም፡፡  ነገርግን በሴቶች እግርኳስ ምንም ልምድ አልነበረኝም፤ ሥልጠናውን እንደ ወንዶች ነበር የማየው፡፡ ልጆቹ ተሰባስበው ጠበቁኝ-እኔም ወዲያው ልምምድ ጀመርኩ፡፡ ከዚያ ብሄራዊ ቡድኑ እየተመቸኝ ሄደ፤ እኔ፣ከሥሬ የነበሩት ባለሙያዎችና ልጆቹ ጥሩ ሥራ እየሰራን ዘለቅን፡፡ በተፈጥሮዬ ቂም በቀል አልወድም፤ የሚያጠፉትን ልጆችም እያስተካከልኩ ወደፊት መጓዜን ቀጠልኩ፡፡ ውስጤ የነበረው ተስፋ የበለጠ እያበረታታኝ ስሜን የመትከል እቅድም ገፋፋኝ፡፡ ተጫዋቾቹ ስልጠናውን በአግባቡ ይቀበላሉ፤ ፌዴሬሽኑ ሙሉ እምነት ጥሎብን ነጻ ኃላፊነት ስለሰጠኝ እኔም ተነቃቃሁ፡፡ ደቡብ አፍሪካን ብናሸንፍ ኖሮ በዚያ ቡድን ብቃት ኦሎምፒክ እንሳተፍ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ደቡብ አፍሪካውያን የተደራጁ፣ ልምድ ያላቸውና ትልልቅ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ነው፡፡ ለሴቶች እግርኳስም ልዩ ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እኛ ውድድር ሲኖር ነው የምንሰበስባቸው፤ እነርሱ ግን በርካታ ክለቦች አሏቸው፤ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ድጋፍ ያደርጉላቸዋል፤ ተጫዋቾቹ ነጻ የትምህርት ዕድል ያገኛሉ፡፡ ልክ እንደ ምዕራባውያኑ ናቸው፡፡

ለዓለም ዋንጫው የማለፍ ህልማችን በደቡብ አፍሪካ ሲገታ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች መጡ፡፡ ግብጽን፤ ጋናን እና ታንዛኒያን በቅደም ተከተላቸው እያለፍን ወደ ውድድሩ ተቀላቀልን፡፡ ገና ከጅምሩ በምድብ ድልድሉ የገጠሙንን ሃገራት ሳይ እንደሚከብደን አውቄ ነበር- ግን ደግሞ “ይከብዱናል!” ተብሎ አይነገርም፡፡ ሃገራቱ በአካል ብቃት የላቁ ናቸው፤ ጥሩ አደረጃጀት አላቸው፡፡ የእኛዎቹ ደግሞ ችሎታ ቢኖራቸውም ብዙ የውድድር ልምድ አልነበራቸውም፡፡ እነዚህን ልዩነቶች እያስተዋለ “ለምን አላሸነፋችሁም?” የሚል አካል ካለ ስህተት ነው፡፡ “በውድድሩ ከዚህ በላይ መጓዝ አንችልም፡፡” ብዬ በወቅቱ ተናግሬያለሁ፤ ያኔ ሉሲዎች የሄዱበትን ርቀት ማክበር አለብን፡፡ በነገራችን ላይ ከውድድሩ በኋላ የሰማኋቸው ነገሮች አሳዘኝ ነበሩ፡፡ ፍጹም እኔን የማይገልጹና ለትዝብት የሚዳርጉ ናቸው፡፡ ያው በኢትዮጵያ እግርኳስ ውጤታማ ስትሆን ንጉስ ትደረጋለህ፤ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ታች ትወርዳለህ፡፡

እግርኳስን በማሰልጠንህ እስከ ጠላትነት የመተያየት ደረጃ መድረስ በጣም አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ በጊዜው የነበሩት አመራሮች በማያውቁት ጉዳይ ከሼህ አላሙዲን የተሰጠኝን የሽልማት ገንዘብ እስከ መቀነስ ደርሰዋል፡፡ በአሉባልታና ማስረጃ በሌላቸው ወሬዎች ምንም ሳያመዛዝኑ የሰውን ስም ማጥፋት እኮ በህግም ያስጠይቃል፡፡ ከዓመታት በኋላ አንዳንዶቹን አነጋግሬያለሁ፤ ” ያኔ ያደረጋችሁት በህግ እንደሚያስጠይቃችሁ ግን አላወቃችሁም?” ብዬ ስጠይቃቸው ” አይ- እኛ እንዲህ… እንዲህ… ተብለን ነው፡፡” የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡ በእግርኳስ ስም ከምታውደለድል አንድ የፌዴሬሽን አባል መረጃ ተቀበልን ተብሎ የስም ማጥፋት ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ ራሴን የማውቅ ሰው ነኝ፤ ጥሩ ቤተሰብ አለኝ፤ የልጆች አባት ነኝ፤ ጥሩ ወንድሞችና እህቶች አሉኝ፤ የሰውን ክብር እጠብቃለሁ፡፡ በባህሪዬ ኃይለኛ ነኝ፤ አሁን እንደምትሰሙኝ ሁሉንም ነገር ፊትለፊት እናገራለሁ፡፡ እናንተም እንደኔ የሚናገር አለ ወይ ተብላችሁ ብትጠየቁ ምላሻችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ የመሰለኝን እናገራለሁ፤ ‘ነገ ሰው እንዲህ… ያደርገኛል፡፡’ ብዬ አላስብም፡፡

የመጀመሪያ እምነቴ ‘ለሃገር ይጠቅማል? አይጠቅምም?’ የሚል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የተቀየሙኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ ቡድኑን ሞጆ ወስጄ ሳሰለጥን አንድም የፌዴሬሽን አባል መጥቶ አይቶን አያውቅም፤ ወደ ዉጪ ልንሄድ ስንል ግን ብዙዎች ሰልፍ ያዙ፡፡ ቡድን መሪዋ እንኳ አሜሪካ ቆይታ ከመጣች በኋላ ነው ከእኛ ጋር ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ የሄደችው፤ ስለ ቡድኑ ምንም አይነት ግንዛቤ አልነበራትም፡፡ ሽንፈት ሲመጣ ስም ማጥፋት ሆነ፡፡ ናይጄሪያንና ካሜሮንን ያኔም፣ አሁንም፣ በእንዲህ አይነቱ አካሄድ ገና አስር ዓመት ሰርተንም አንችላቸውም፡፡ በትክክለኛው አሰራር በደንብ አድርገን እናሸንፋለን፡፡ ተጫዋቾቻችን እኮ ተነሳሽነት፣ ችሎታ፣ ሞራል፣… ህልም ያላቸው ነበሩ፡፡ መሃላቸው ደግሞ ያው….. ሁሌም ያለ ነው፤ ጥሩ ሲኖር አብሮ መጥፎ አይጠፋም፡፡ መጥፎ ሰው በድክመትህ ገብቶ ሊያጠቃህ ይሞክራል፡፡ በአጠቃላይ በሴቶች ብሄራዊ ቡድን ቆይታዬ ለአፍሪካ ዋንጬ ባለፈው ቡድን እኮራለሁ፤ በህዝባችን ግን አዝኛለሁ፡፡ እንዲያውም “ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው፡፡” ሲባል እገረማለሁ፡፡ ቢሆንማ ኖሮ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፉት ሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች ነበሩ- የወንዶቹም፥ የሴቶቹም፡፡ ነገርግን የወንዶቹ ላይ ተሰቀለ፤ ብዙ ተባለለት፡፡  እነዚያ ሴቶች ግን ያን ሁሉ ታሪክ ሰርተው አንድም አይወራላቸውም፡፡ የወንዶቹማ እካሁንም ድረስ “ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ…” እየተባለ ሲወደስ እንሰማለን፡፡ የሴቶቹ ግን አይነሳም፤ ለምን? እነርሱም እኮ ከአስር ዓመት በኋላ በአፍሪካ ነው ለአፍሪካ ዋንጫ የተሰተፉት፡፡ እንዲያውም የሴቶቹ ገድል ነው በደንብ ሊገን የሚገባው፡፡ ለዚህ ደግሞ የስፖርት መሪዎች፣ ፌዴሬሽን አካባቢ ያሉ ሰዎች እና ጋዜጠኞች መወቀስ አለባቸው፡፡

ያ ቡድን ለአፍሪካ ውድድር ካለፈ ከሰባት በላይ ዓመታት ተቆጠሩ፤ ምንም አይነት መሻሻል ሳናሳይ- ጭራሽ የነበረንን ደረጃም እያጣን መጥተናል፡፡ ይህ ሁኔታ በጣም ያሳዝነኛል፤ እንደገና ሰላሳ ዓመታት ልንጠብቅ ነው? ልክ እንደ <ሱናሚ> ዝም ብሎ የሚመጣ ጉድ ሊሆን ነው ማለት ነው? ዘላቂ ስኬታማነት የያዘ የእግርኳስ ሥራ ሰርተን ማደግ እንድንችል የሚያደርግ አጠቃላይ የእግርኳስ ሥርዓትና አመራር ያስፈልገናል፡፡ በነገራችን ላይ ሎዛ አበራ የ<ፕሮፌሽናልነት> እድል እንድታገኝ ከመሰረቱ ያመጣኋት እኔ ነኝ፤ ማንም ግን አይጠቅሰውም፡፡ የ<ሉሲ ማቀጣጠያ!> ብለን እኔና አቶ ዘሪሁን ከደቡብ ክልል ሰባ ልጆችን ሰብስበን በሐዋሳ ስልጠና እንዲያገኙ ስናደርግ ሎዛ አንደኛዋ ነበረች፡፡ እኔ፣ አቶ ዘሪሁንና ወ/ሪት መስከረም ሆነን ገንዘብ ከእነ ዶ/ር እሌኒ እና ከሌሎችም አካላት እየዞርን ሰብስበን ወደ አራት መቶ ሺህ ብር አገኘን፡፡ ለአንድ ወር አቶ ዘሪሁን ሆቴል ውስጥ እንዲቆዩ ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ ሎዛ አበራ፣ ዙሌይካና ሌሎች ወጣቶችን አስመረጥን፡፡ እንዲያውም ዙሌይካን የዚያኔ ባንክ ጥሩ ቡድን ስለነበር በእንክብካቤ ልታድግ ትችላለች በሚል ከክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር ተነጋግሬ እዚያ እንድትገባ አድርጌያለሁ፡፡ ብዙ ግን አይነገርም፡፡

ደደቢትም አልቆየህም፤ ምን ተከሰተ?

★ ከኮሎኔል ዐወል ጋር ገና በሴቶች በብሄራዊ ቡድን ሳለሁ ከታንዛኒያ ጋር ከመጫወታችን በፊት ዳሬሠላም ድረስ መጥቶ፣ ከእኛ ጋር ሰንብቶ ነው በዚያው ያነጋገረኝ፡፡ የዚያን ጊዜ “ውድድሩን ስጨርስ ደደቢት እገባለሁ፡፡” ብዬ ወሰንኩ፡፡ ስመጣ ደደቢትን ተቀላቀልኩ፡፡ ነገርግን በክለቡ ብዙም አልቆየሁም፤ በማያቸው ነገሮች እየተሰላቸሁ ሄድኩ፡፡ ለመልቀቅ ወሰንኩ፤ወጣሁ፡፡

ያለፉት ሠላሳ ዓመታት የእግርኳስ አሰልጣኝነት ህይወትህ ሁለት ገጽታዎች ያሉት ይመሥላል፡፡ እምብዛም ጫና ባልነበረባቸው ጉና፣ ሙገር፣ በጣም ጥሩ ቡድን በነበረው መተሃራ እና በሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነትህ ውጤታማ ነበርክ፡፡ በተቃራኒው ከፍተኛ ጫና ባለበት ቡና ብዙ አልቆየህም፤ በወንዶቹ ብሄራዊ ቡድንም አጭር ጊዜ ነው የቆየኸው፤ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡት ሰበታና ደደቢትንም በጊዜ ተሰናብተሃል፤ ከዚህ አንጻር አብርሃም ተክለሃይማኖት በጫና ውስጥ ሆኖ መሥራት ይከብደዋል

★ ይህንን እኔ ራሱ የማስበው ጉዳይ ነው፡፡ ቡድን መርጬ ገብቼ አላውቅም፡፡ ለቅጥር መጀመሪያ ጥያቄ ያቀረበልኝን ክለብ “እሺ!” እላለሁ፡፡ ቡናን እንኳ ከሥዩም አባተ ውጪ የትኛው አሰልጣኝ ነው የተሳካለት? ውበቱ አባተ-በቃ! ሥዩም ከክለቡ ምስረታ ጀምሮ አብሮ የነበረ ስለሆነ ብዙ ስኬቶች አምጥቷል፡፡ እኔ መብቴን ማስነካት አልወድም፤ ስድብን መቀበል አልችልም፡፡ የመጀመሪያውን ሲቲ-ካፕ ቡና ወስዷል፤ ሊጉ ተጀምሮም ጊዮርጊስን የሰባት ነጥብ ብልጫ ነበረን፡፡ ከዚያ ውስጥ ሰላም ጠፋ፡፡ በጥባጮቹ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ብጥብጡ የአድማ መልክ ያዘ፤ እኔን የማይፈልግ ቡድን ተፈጠረ፡፡ በዚህ ምክንያት ቡድኑ ከሚጎዳ ብዬ እኔ ለቀቅሁ፡፡

ከዚያ በመተሃራ የሚገርም ቡድን ሰራሁ፤ በሜዳችን ጊዮርጊስ ብቻ ነው ያሸነፈን፤ ቡናንም ሆነ መብራት ሃይልን አሸንፈናል፤ ጠንካራና ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን ገንብቻለሁ፡፡ ነገርግን የሙቀት መጠኑ እስከ 40 ዲግረ ሴንቲግሬድ በሚደርስበት ቦታና ከቤተሰብ ያን ያህል ርቄ መስራት አልቻልኩም፤ ቢያንስ ወንጂ ቢሆን እየተመላለስኩ እስራ ነበር፡፡ ትንሽ ሞከርኩ-ፍጹም አልተስማማኝም፤ ምግብም አልነበረም፤ ትንሽ መሸት ካለ ዝም ብለህ ገብተህ መተኛት ነው፡፡ እኔ አኗኗሩን አልቻልኩም እንጂ እጅግ በጣም በእንክብካቤ የተያዝኩበት ክለብ ነበር፡ በመቀጠል ሙገር ነው የገባሁት፤ መገርንም ተወዳዳሪ ክለብ አድርጌዋለሁ፡፡

በብሄራዊ ቡድን ደግሞ ብዙም ሳልጓዝ ነው የፊፋ ቅጣት የመጣው፡፡ ከዚያ በኋላ አልተወዳደርኩም፤ እድሉንም አላገኘሁም፡፡ የሴቶቹን ካየንም ጫና አለው፡፡ ያኔ በእኛ ሃገር እግርኳስ በክለብ ደረጃ በፈታኝ ከባቢ (Challenging Environment) ውስጥ ለመሥራት ቅዱስ ጊዮርጊስን አልያም ኢትዮጵያ ቡናን ማሰልጠን አለብህ፤ እኔ አንዱን የመምራት አጋጣሚውን አግኝቻለሁ፡፡ በራሴ አስተሳሰብ ሳቢያ እሱን ልጠቀምበት አልፈለኩም፤ ተጫዋች ካደመብህ ደግሞ ነገሮች አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ ከአሰልጣኝ በላይ ደጋፊ የሚታመንበት ቦታ ለመሥራት ደግሞ ያለኝ ሙያዊ ሥነ ምግባር አይፈቅድልኝም፡፡ በስልክ ተደውሎ ” እነ እገሌን አሰልፍ፤ እነ እገሌን አስወጣ!” የሚባልበት ሁኔታዎችን መቋቋም አልፈልግም፤ አሁን ስናገረው እንደ ምክንያት ሊታይብኝ ይችል ይሆናል፡፡ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡

ደደቢትና ሰበታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንደመጡ በርካታ ገንዘብ ያወጡ ነበር፡፡ ሰበታ እንዲያውም መሬትም እስከ መስጠት ደርሶ ነበር፡፡ ከመጠን ያለፈ ጉጉት እና ከአቅም በላይ የሆነ እቅድ ያላቸውን ክለቦች መምራት ምን ያህል አስቸጋሪ ነው?

★ ብዙ ጊዜ በሌለ አቅም <Over Ambituous> የሆነ አካሄድ መከተል የአመራሩ ችግር ነው፡፡ የሚያወጡትን ገንዘብ በውጤት ለመመለስ ማሰብ በየትኛውም ዓለም የተለመደ ነው፡፡ በሰበታ እኔ እግርኳሱ እንዲሄድ ሳስብ የነበረው ሌላ፥ በተግባር ሲሆን የነበረው ደግሞ ሌላ ነው፡፡ በወጣቶች አምናለሁ፤ በዚያ መልኩ የማያስብ ክለብ ስገባ እረባበሻለሁ፡፡ አንዳንዴ ጥዬ የምወጣውም ለዚያ ይመስለኛል፡፡ ለቀጣይ ህይወቴ የሚጠቅም ገንዘብ ሳላዘጋጅ እስከ መልቀቅ እደርሳለሁ፤ ያን ያህል ጨካኝ ነኝ፡፡ መሥራት የማልችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ትቼ እወጣለሁ፡፡ ይህ ባህሪዬ ፍርሃት ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ ፈሪ ነኝ ብዬ ግን አላስብም፤ ምክንያቱም ስጋት ቢኖርብኝ ኖሮ አልናገርም፤ አድርባይና <Opportunistic> እሆን ነበር፡፡ አንድ ክለብ ውስጥ ተጫዋች ለፕሬዘዳንቱ ደውሎ ስለ አሰልጣኙ ወሬ ሲያቀብል ገጥሞኛል፤ ይህን ፈጽሞ አልቀበልም፡፡ ተጫዋቹ የትም አምሽቶ ተቀያሪ ወንበር ላይ ሳስቀምጠው ” እንዴት እገሌ ተቀያሪ ይሆናል?” በማለት ከሚናገረኝ አመራር ጋር መሥራት አይሆንልኝም፡፡ በመጨረሻ እንዲያውም “የኢትዮጵያ እግርኳስ በዚህ መንገድ የትም አይደርስም፡፡ ብዬ ነው የደመደምኩት፡፡ ተጫዋች የሚያዝበትን ሥርዓት ልቀበል አልችልም፡፡ አሰልጣኝም ሆነ ተጫዋች ለ<Discipline> ተገዢ መሆን አለበት፡፡ በባርሴሎና በነበረኝ ጉብኝት ቡድኑ በኑካምፕ የልምምድ ፕሮግራም ላይ ፍራንክ ራይካርድ የወቅቱን የአለም ኮከብ ሮናልዲንሆን ጠርቶ ሲያነጋግረው ያ ዓለምን ያስደነቀው ጥበበኛ ተጫዋች እጆቹን ወደኋላ አድርጎ አሰልጣኙን ሲያዳምጥ አይቻለሁ፡፡ ሮናልዲንሆን የሚያክል ታላቅ ተጫዋች አሰልጣኙን የሚያከብርበት ሁኔታ የተጫዋቾች <Professional Ethics> የት ደረጃ እንደደረሰ ያመላክታል፡፡ የእግርኳስ እድገት መሰረቱ ከዚያ ይጀምራልና እኔም በዚያ መልኩ አስብ ነበር፡፡ አልፎአልፎ ‘እንደ ጉዱ ካሳ ሆንኩ እንዴ?’ እላለሁ፡፡ ነጠቅ ብሎ መውጣትና በሌለ ሜዳ መውተርተር አስቸጋሪ ይሆናል፤ እንደ እብድ ትታያለህ፡፡

ከባቢዎቹ ከተስተካከሉ ወይም በራስህ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተመስርተህ ወደ አሰልጣኝነቱ ልትመለስ ትችላለህ

★ እንደ አሰልጣኝ ሙሉ መብት ከተሰጠኝ እና ኃላፊነቱ በእጄ ከሆነ አድራጊ ፈጣሪ እኔ እሆናለሁ፡፡ ያኔ ተጠያቂም ተወዳሽም መሆን እችላለሁ፡፡ ሌላ ሰው እጁን አያስገባም፤ ተጫዋቾችም ለኔ ሥርዓት ተገዥ ይሆናሉ፡፡ የሌላ አካል ጣልቃ ገብነት አያሻም፡፡ ሌላ እገዛ በሚያስፈልገው ቦታ ይደረጋል፡፡ በዚህ መልኩ ሆኖ አሰልጣኙ በሚስማማባቸው ጉዳዮች እየሰራ፥ በማይስማማቸው ደግሞ ጥያቄ እያቀረበና በአግባቡ እየተመለሱለት የሚያሰራ ከባቢ ከተፈጠረ መስራት እችላለሁ፡፡ በሰከነ መንፈስ ማሰልጠን በምችልበት ጊዜዬ ነው የተውኩት፤ ‘ገንዘብ አገኛለሁ፤ ኑሮዬን እገፋበታለሁ፤…” ብዬ ፍጹም በማልወደው አድርባይነት ራሴን ማሳተፍ አልፈልግም፡፡ ‘በአጭር ጊዜ የኢትዮጰያ እግርኳስ ይሻሻላል፡፡’ ብዬም ስለማላስብ ከዚያ በኋላም ቢሆን ችግሩ እየገፋ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡

ይቀጥላል…


ክፍል አንድን ለማግኘት ይህን ይጫኑ :point_right: ክፍል 1