የእለቱ ዜናዎች | ረቡዕ ህዳር 27 ቀን 2010

ወልዲያ

በክለቡ አስተዳደራዊ ችግር ምክንያት ባለፈው አርብ በድንገት ከወልድያ ተለይተው የሄዱት ምክትል አሰልጣኙ ኃይማኖት ግርማ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ ባደረጉት ጥሪ እሁድ ከቡድኑ ጋር የተቀላቀሉ መሆናቸውን ሰምተናል። ወልዲያ በስድስተኛ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ላለበት ጨዋታ አሁን በአአ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል የሚገኝ ሲሆን ነገ ወደ ሀዋሳ የሚያቀና ይሆናል። ወልዲያ በቅርቡ አሉበት የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት የክለቡ የበላይ አካላት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።


ወልዋሎ

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በመጀመርያ አመት ተሳትፎው ጥሩ አጀማመር ያደረገው ወልዋሎ ሜዳውን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የክለቡ አመራሮች ጥረት ማድረግ መጀመራቸውን ሰምተናል። እንደ ክለቡ አመራሮች ሀሳብ ከሆነ የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሜዳን ሁለተኛ ሜዳ እንዲሆን በፌዴሬሽኑ አስመዝግበው ቡድኑ ለሁለት ወራት ያህል በዩኒቨርስቲው ሜዳ እንዲጫወት በማድረግ አሁን እየተጠቀመመበት ያለውን ሜዳ በሁለት ወር ውስጥ ሊጠናቀቅ በሚችል መልኩ የሜዳውን አጠቃለይ ሁኔታ (ሳር የማልበስ እና የስታድየሙን ጥላ ፎቅ ግንባታ የማጠናቀቅ) እንደታሰበ ታውቋል። የወልዋሎ ሜዳ በአመቺነቱ ዙርያ በተጋጣሚዎች ቅሬታ ባይቀርብበትም ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች መሀል የመጫወቻ ሜዳው ሳር ያልለበሰ ብቸኛ ሜዳ መሆኑ ይታወቃል።


አስመራጭ ኮሚቴ 

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተሰየመው 13 አባላት ያሉት አሰመራጭ ኮሚቴ የተመራጭ እጩ ተወካዮችን ሰነድ ተረክበው በማስቀመጥ የጀመሩት መደበኛ ስብሰባቸውን ባለፈው ቅዳሜ ቀጥለው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፈዋል። ሰኞ እለት ስብሰባቸውን አጠቃለው የጨረሱ ሲሆን ከውሳኔዎቻቸው መካከል አንዱ 5  የፕሬዝደንት እና 16 የስራ አስፈፃሚ እጩ አባላት ይፋ የተደረጉበት ሲሆን ሌላው ደግሞ ሁለት እጩ ተወካዮችን ውድቅ ያደረገ ነበር።

ይሁን እንጂ ከዚህ ውሳኔ ጀርባ በርካታ ልዩነቶች ፣ በድምፅ ብልጫ የተወሰኑ አስገራዊ ውሳኔዎች ፣ በአስመራጭ ኮሚቴው ፕሬዝደንት እና ምክትሉ መከካከል የተፈጠሩ ሰጣገባዎች እንደነበሩ የተሰማ ሲሆን በእስካሁኑ ሒደት ላይ ነገ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ታስቦ የነበረ ቢሆንም መቅረቱን አረጋግጠናል። በሚቀጥለው ሳምንት በአጠቃላይ አስመራጭ ኮሚቴው ስለሰራው ስራ እና ስላለበት ሁኔታ ሁሉም የኮሚቴ አባለት በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ የሰማን ሲሆን ኮሚቴው በሚጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አንዳንድ አባላት ልዩነታቸውን ለህዝቡ እና ለሚዲያው ይፋ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።


የሴቶች ፕሪምየር ሊግ – ሁለተኛ ዲቪዚዮን 

ሦስተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረው የሁለተኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ባለፈው እሁድ ጀምሮ ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፍፃሜውን አግኝቷል ። በሁለቱ ሳምንት ከተመዘገቡት ጎሎች አንፃር በሦስተኛው ሳምንት የጎሎች መጠን በርከት ያለ ሲሆን በሰባት ጨዋታዎች 29 ጎሎች ተቆጥረዋል። ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ ጥረት ኮርፖሬት እና ጥሩነሽ ዲባባ  ስፖርት አካዳሚ ሦስቱንም ጨዋታ በማሸነፍ መልካም የውድድር ጊዜ እያሳለፉ ይገኛሉ።


በሦስተኛ ሳምንት የተመዘገቡ ውጤቶች 

ጥሩነሽ ዲባባ  3 – 0 ሻሸመኔ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ 3 – 0 ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ

ጥረት ኮፕሬት 6 – 0 ፋሲል ከነማ

ኢትዮ ቡና 3 – 2 ቦሌ ክ/ ከተማ

ቅ/ማርያም 0 – 4 አአ ከተማ

ልደታ ክ/ ከተማ 2 – 0 አቃቂ ክ/ከተማ

ቂርቆስ ክ/ከተማ 0 – 6 ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ


ጥቆማ

ነገ ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በኢትዮዽያ ሆቴል የኢትዮዽያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት አመራሮች ፣ ደጋፊዎች በተገኙበት እሁድ በሚደረገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ዙርያ ውይይት ይደረጋል። ጨዋታው በፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ በታሰበው የውይይት መድረክ በርካታ ጠቃሚ ሀሳቦች ይነሱበታል ተብሎ ይጠበቃል።


የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን

የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 10:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ ኢትዮ ኤሌትሪክ ያገናኛል። በሁለተኛ ሳምንት መደረግ የነበረበት ይህ ጨዋታ ከ17 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ምክንያት ያልተካሄደ ሲሆን ከሦስተኛ ሳምንት ጀምሮ ያለው ጨዋታ መርሐ ግብር  ከታህሳስ 14 ጀምሮ እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።


የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ነገ 08:00 ላይ ከቡሩንዲ ጋር ያደርጋል።

ዝርዝሩን እዚህ ያንብቡ | ኢትዮጵያ ከ ቡሩንዲ


ሸገር ደርቢ 

እሁድ የሚደረገው የሸገር ደርቢ ጨዋታን አስመልክቶ የሚኖረውን ረጃጅም ሰልፍ እና አድካሚ ውሎን ለማስቀረት በማሰብ የመግቢያ ትኬት ከአርብ ጀምሮ ለሽያጭ ለማቅረብ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማርኬቲንግ ክፍል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ትኬቱ እንዴት እና የት ይሸጣል የሚለውን ለስፖርት ቤተሰቡ በቀጣይ እንደሚያሳውቁም ሰምተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *