አአ ከተማ ዋንጫ | ወልዋሎ ድል አድርጓል

በሁለተኛ ቀን የአዲስአበባ ከተማ ጨዋታ 8 ሰዓት ላይ ወልዋሎ ዓ/ዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1ለ0 በመርታት ውድድሩን በድል ጀምሯል፡፡

የወልዋሎዎች የበላይነት በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ቢጫ ለባሾቹ ከግብጠባቂው ኬይታ ውጭ ከዐምናው ቡድን ፍፁም የተለየ የቡድን ስብስብን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በጨዋታውም በተለይ በቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራ ከድሬዳዋ ከተማ ክለቡን የተቀላቀለው ገናናው ረጋሳ ባጋደለ መልኩ ወልዋሎዎች በተደጋጋሚ ወደ ኤሌክትሪኮች አደጋ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡

ወደ መሀል ሜዳ ተጠግተው ለመከላከል ካሰቡት የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ጀርባ በርካታ አጋጣሚዎች የወልዋሎ ተጫዋቾች ቢገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ33ኛው ደቂቃ ጂሊያስ ናንጁቢ የግሉን ጥረት ተጠቅሞ ያገኛትን ኳስ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ወልዋሎን ቀዳሚ ማረግ ችሏል፡፡

ኤሌክትሪኮች ደካማ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ ኳስን በተለይ በራሳቸው ሜዳ ክፍል መቀባበል ቢችሉም ኳሳቸው ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል ሲደርስ በቀላሉ ሲበላሽ ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች በእንቅስቃሴ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ በነበሩት በሁለተኛው አጋማሽ የጠሩ የግብ እድል በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ በተለይም በሁለት አጋጣሚ ኢታሙና ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከናቸው አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ የኤሌክትሪኩ ግብጠባቂ ታምራት ዳኘው ከግብ ክልል ውጭ ኳስ በእጅ በመንካቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡


ጨዋታው በወልዋሎ የ1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተክሎ የጨዋታው ብቸኛ ግብ ባለቤት ጂሉያስ ናንጁቢ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ