3ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትላንትና ከትላንት በስቲያ በተካሄዱ 8 ጨዋታዎች ቀጥሎ ውሏል። በዚህም መሠረት ወልዋሎ ሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታውን ድል ሲያደርግ፤ ወልቂጤ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል አሳክተዋል፤ እኛም የሳምንቱን ዓበይት ጉዳዮች በተከታዩ መልክ ቃኝተነዋል።
1. የወልቂጤ የመጀመሪያ ሙሉ ሦስት ነጥብ
ዐምና ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደጉት ወልቂጤ ከተማዎች በ3ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ ከሊጉ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ የሆነው ፋሲል ከነማን 1ለ0 በመርታት በሊጉ የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
በቶጎሊዙ አጥቂ ጃኮ አረፋት ብቸኛ ግብ የመጀመሪያ ሦስት ነጥባቸውን ከማሳካት ባለፈ በ6ኛው ደቂቃ ጃኮ ያስቆጠራት ግብ ሠራተኞቹ በመጀመሪያው የፕሪምየር ሊግ ተሳትፏቸው ያስቆጠሯት የመጀመሪያ ግብ ሆና ተመዝግባለች።
ከሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በመያዝ መልካም ጅማሮን እያደረጉ የሚገኙት ወልቂጤዎች በያዝነው ሳምንት ወደ አግልግሎት እንደሚመለስ በሚጠበቀው ስታዲየማቸው ሰበታ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል።
2. ወልዋሎ በአስደናቂ አጥቂዎቹ መልካም ጅማሮውን አስቀጥሏል
በፕሪምየር ሊጉ አስደናቂ አጀማመር እያደረጉ የሚገኙት ወልዋሎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ስሑል ሽረን 3ለ0 በመርታት በ100% የማሸነፍ ሪከርዳቸው ቀጥለዋል።
በዮሐንስ ሳህሌ “ብሉ ፕሪንት” የተገነባው ቡድኑ ተገማች ባልሆነው የቡድን ስብስብ ምርጫና አጨዋወት ታጅቦ በሊጉ መልካም ጅማሮውን ማስቀጠል ችሏል።
ለተለያዩ የአጨዋወት ስልቶች የተመቹ ጥሩ አቅም ያላቸው አጥቂዎችን ያሰባሰበው ቡድኑ ከኤታሙና ኬይሙኒ በስተቀር በሦስቱ ጨዋታዎች ላይ የተጠቀመባቸው አጥቂዎች እስከአሁን በሊጉ ሁለትና ከዚያ በላይ ግቦችን በማስቆጠር ከወዲሁ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ምንም እንኳን ስለዋንጫም ሆነ በደረጃ ውስጥ ስለማጠናቀቅ ለማወራት ጊዜው ገና ስለመሆኑ ቢናገሩም እያደረጉት ካለው ጠንካራ አጀማመርና የያዙት የቡድን ስብስብ አንፃር በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ይሰነብታሉ ብሎ መገመት ይቻላል።
3. የኢትዮጵያ ቡና መሻሻልና ረጃጅም ኳሶች
በ3ኛ ሳምንት ፕሪምየር ሊግ በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከመመራት ተነስቶ ከዐምናው ቻምፒዮን መቐለ 70 እንደርታ ጋር 1ለ1 መለያየቱ ይታወሳል።
በአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ ጋር ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴን ያሳየው ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ከጅማ አባ ጅፋር ጋር እንዲሁም በትላንቱ የመቐለ ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሾች ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የቡድኑ ዋነኛ ክፍተት ተደርጎ ይጠቀስ በነበረው የኳስ ቅብብሎችን ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል እንዲደርሱ በማድረግና የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ መሻሻሎች ስለመኖራቸው አመላካች እንቅስቃሴ ተስተውሏል።
በጅማው ጨዋታ ከአጨራረስ ችግር የተነሳ አጋጣሚዎቹ ሲባክኑ ቢስተዋልም በትላንቱ ጨዋታ በ16ኛው ደቂቃ በእንዳለ ደባልቄ አማካኝነት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ግባቸውን ለማስቆጠር በቅተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላኛው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የቡድኑ ጠንካራ ጎን የነበረው ለ90 ደቂቃ ያክል ወደ ሜዳ ይዘውት ለገቡት የጨዋታ እቅድ ታማኝ የመሆን ጉዳይ ግን በእነዚህ ጨዋታዎች ላይ በተወሰነ መልኩ ስለመሸርሸራቸው ምልክቶች ታይተዋል፤ በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ በሁለተኛ አጋማሾች ላይ በርከት ያሉ ረጃጅም ኳሶች ወደፊት ሲጣሉ ተስውሏል ይህም ከአሰልጣኙ ትዕዛዝ ውጭ የሚከወኑ ስለመሆናቸው አሰልጣኝ ካሣዬ ከትላንቱ ጨዋታ በኋላ በሰጠው አስተያየት ገልጿል።
“ዛሬ ብዙ ስህተቶች አልተፈጠሩም፤ ምክንያቱም ተጫዋቾቻችን ሃላፊነት ወስደው ለመጫወት አልደፈሩም። ግብ ጠባቂያችንም ኳሶችን በረጅሙ ይልክ ነበር፤ መጫወት ነበረብን። ስህተቶችን እያረምን ነው የምንሄደው። ግን ያንን በትክክል እያደረጉት አልነበረም። ሃላፊነት ለመውሰድ እየፈሩ ነበር፤ ይህ ችግር ይታይ ነበር። እንደዛ ስንጫወት የሚፈጠሩ ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን እንቅስቃሴው ይዘን መቀጠል ነበረብን። ዛሬ ግን ያን ነገር ዛሬ በብዛት አልነበረም።” ብሏል።
4.የሜዳዎች ጉዳይ
” እዚህ ሜዳ ላይ ማንም ቡድን መጫወት አይችልም፤ በዚህ ሜዳ ላይ ማንም ሦስት ነጥብ መውሰድ አይችልም፡፡ ህዝቡም ደግሞ በዚህ ሜዳ በሚደረግ ጨዋታ በፍፁም መደሰት አይችልም። በአጠቃላይ ይህ ሜዳ ፈርሷል ብለው ይቀለኛል።” ሰርዳን ዝቪጅሆቭ (የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ)
“ከሜዳው አለመመቸት አኳያ የምንፈልገውን ነገር ማድረግ ቢከብደንም የተገኙትን አጋጣሚዎች አለመጠቀም ዋጋ አስከፍሎናል። በዚህ ሜዳ ላይ ውድድር ማድረግ በራሱ ከባድ ነው።” ሥዩም ከበደ (የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ)
ከላይ ለማሳያነት የቀረቡት ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች በ3ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ግብ የተለያዩበት እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ፋሲል ከነማን ከረታበት ጨዋታዎች በኃላ የተሰጡ ናቸው።
ከተጀመረ ገና ሦስተኛ ሳምንቱን ባስቀጠረው የዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ የሶዶ ስታዲየም ለጨዋታ ምቹ ስላለመሆኑ ሀሳብ ሲሰጥበት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በተመሳሳይ በ1ኛ ሳምንት የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ መሰል አስተያየት መስጠታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። (ሜዳውን የማሻሻሻል ስራ በአሁኑ ሰዓት እየተከናወነ ይገኛል)
በተመሳሳይ በቅርቡ እድሳት ተደርጎለት ዳግም ወደ ሥራ የተመለሰው የሆሳዕናው የአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ገና ከወዲሁ መሰል ቅሬታዎችን ማስተናገዱ እጅግ አስገራሚ ነው። በዐቢይ ኮሚቴው ውሳኔ መሠረት ሌሎች የመጫወቻ ሜዳዎች ሳርን ጨምሮ ሌሎች ተጓዳኝ እድሳት እየተደረገባቸው የሚገኙ ስታዲየሞች በተለይ በፍጥነት የሊግ ጨዋታዎች በሜዳቸው ለማስተናገድ ካለ ጤናማ ፍላጎት የመነጨ የመጫወቻ ሳሩ በበቂ ሁኔታ እድገቱን ሳይጨርስ ወደ ስራ እንዳይገቡ ክትትል ይሻል።
5. ሰበታ ከተማ እና የሜዳ ተጠቃሚነት ጉዳይ
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተቀላቀሉት ሰበታ ከተማዎች ሜዳቸው በእድሳት ላይ ስለሚገኝ ለተወሰኑ ወራት በፕሪምየር ሊግ የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በተለዋጭነት ባስያዙት በአዲስ አበባ ስታዲየም ለመጫወት እንደሚገደዱ ይታወቃል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከታችኛው የሊግ እርከኖች ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚቀላቀሉ የክልል ቡድኖች ወደ ውጤት በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ደጋፊዎቻቸው በተለይ ከፍተኛ ሚናን ሲወጡ ይስተዋላል። በተመሳሳይ ዐምና ሰበታ ከተማ በተለይ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በርካታ ቁጥር ያለው የከተማው ነዋሪ ክለቡን ሲያበረታታ ይስዋል ነበር።
ምንም እንኳን ቡድኑ ከፍተኛ ነው የሚባል የተጓዥ ደጋፊዎች ቁጥር ባይኖረውም ከሜዳው እድሳት ጋር በተያያዘ ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች እጅግ ውስን ቁጥር ያላቸው የክለቡ ደጋፊዎች በስታዲየም ተገኝተው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተስተውሏል። ሰበታ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ካላት ቅርበት አንፃር ቡድኑ በሜዳው ውጤት ለመያዝ የደጋፊዎቹ እገዛን በሚሻበት በዚህ ወቅት የደጋፊዎች ቁጥር መመናመን ጉዳይ እልባት የሚሻ ይመስላል።
ይህንንም ሀሳብ የክለቡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከአዳማ ጋር ቡድናቸው ነጥብ ከተጋራ በኋላ በሰጡት አስተያየት ለመጥቀስ ሞክረዋል። በንግግራቸውም በጨዋታው ውጤት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ደጋፊዎች ባለመኖራቸው ቡድናቸውን ለመግጠም ለሚመጡ ቡድኖች ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች እኩል ተጠቃሚነት እንደሚኖር ሲገልፁ ተደምጧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ