የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተከናውነዋል። በስምንቱ ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ 11 ተጫዋቾችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።
* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች በተመለከቷቸው ጨዋታዎች ላይ ለተጫዋቾች በሰጡት የተናጠል ነጥብ ላይ የተመረኮዘ ነው።
*አሰላለፍ፡ 4-1-3-2
ግብ ጠባቂ
ሀሪስተን ሄሱ (ባህር ዳር ከተማ)
የባህር ዳር ከተማው ግብጠባቂ ምንም እንኳን ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 ሽንፈትን ቢያስተናግድም ውጤቱ ከዚህ በላይ እንዳይሰፋ በርካታ ኳሶችን ሲያመክን ውሏል። በጨዋታው ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ሦስት የአንድ ለአንድ ግንኙነቶችን ጨምሮ በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን በማዳን በግሉ ጥሩ ሳምንት ማሳለፍ ችሏል።
ተከላካዮች
ቀኝ – ዳንኤል ደርቤ (ሀዋሳ ከተማ)
ሀዋሳ ከተማ ባህርዳር ከተማን በረታበት ጨዋታ የጨዋታውን 2/3 ያክል ጊዜ በመስመር ተከላካይነት እንዲሁም የተቀሩትን ደቂቃዎች ደግሞ የቦታ ለውጥ አድርጎ በማጥቃት እንቅስቃሴ ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል። በጨዋታውም ከፊቱ ከተሰለፈው መስፍን ታፈሰ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ለአጥቂዎች ጥሩ ጥሩ የጎል እድሎችን መፍጠር ችሏል።
መሐል – በረከት ሳሙኤል (ድሬዳዋ ከተማ)
ከአስከፊ አጀማመር በኋላ ወደ ድል የተለመሱት ድሬዳዋ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 1ለ0 በረቱበት ጨዋታ ላይ የድሬዳዋን የመከላከል አደረጃጀት በመምራት እንዲሁም ሀዲያዎች ጥሩ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት በኩል ጥሩ ጨዋታን አሳልፏል።
መሐል – መሐመድ ሻፊ (ወልቂጤ ከተማ)
በቅርቡ ከጉዳት ያገገመውና በጨዋታው መሰለፍ ባልቻለው ቶማስ ስምረቱ ምትክ የመሰለፍ እድል ያገኘው የወልቂጤው የመሀል ተከላካይ ገና በጊዜ ጎል መቆጠሩን ተከትሎ ለረጅም ደቂቃዎች የቡድኑን ውጤት ለማስጠበቅ በከፍተኛ ትጋት ሚናውን መወጣት ችሏል።
ግራ – ሳሙኤል ዮሐንስ (ወልዋሎ)
ተለዋዋጭ ሚናን መወጣት የሚችለው ሳሙኤል ዮሐንስ በመስመር ተከላካይነት በተሰለፈበትና ቡድኑ ስሑል ሽረን 3ለ0 በረታበት ጨዋታ ገናናው ረጋሳ ያስቆጠራትን ግብ ከቅጣት ምት ያመቻቸ ሲሆን በተጨማሪም በግራ መስመር ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና በመጫወት በግሉ ስኬታማ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል።
አማካዮች
ተከላካይ አማካይ – ገናናው ረጋሳ (ወልዋሎ)
ወልዋሎዎች ሽረን ሲረቱ የመጀመሪያዋን ግብ ከቅጣት ምት ተሻምቶ በግንባሩ በመግጨት ቀዳሚ ማድረግ የቻለው ገናናው ሽረዎች የተሻለ በተንቀሳቀሱበት የመጀመሪያ አጋማሽ የነበራቸው የመሐል ሜዳን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማጨናገፍና የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል።
ቀኝ – መስፍን ታፈሰ – ሀዋሳ ከተማ
ከተለመደ የፊት አጥቂነት ሚናው ውጭ በመስመር አማካይነት የተሰለፈው ወጣቱ መስፍን ታፈሰ ብሩክ በየነ ላስቆጠራት ግብን ኳስ አመቻችቶ ከማስቆጠር ባለፈው በጨዋታው ሀዋሳዎች ለፈጠሯቸው በርካታ የግብ እድሎች በመነሻነት የጎላ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
አጥቂ አማካይ – ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና)
ሲዳማ ቡና ከሜዳው ውጭ ጅማ አባ ጅፋርን ሲረታ ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚያደርገውን ፈጣን ሽግግር በመምራት እንዲሁም በፍጥነት ኳሶችን ወደ መስመር ተለጥጠው በነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኙት የመስመር አጥቂዎች በማድረስ ረገድ ስኬታማ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል።
ግራ – ጫላ ተሺታ (ወልቂጤ ከተማ)
ወልቂጤዎች የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ድላቸው ባሳኩበት ጨዋታ ከጉዳት መልስ ለቡድኑ ግልጋሎት የሰጠው ጫላ በተለይ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ወቅት ከመስመር እያጠበበ በመግባት በተደጋጋሚ ወደ ፋሲል የግብ ክልል በመድረስ ለፋሲል ከተማ ተጫዋቾች ከፍተኛ ፈተና ሆኖ ውሏል። ፋሲሎች በመስመር በኩል እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብም የፈጣኑ ተጫዋች ሚና ከፍተኛ ነበር።
አጥቂዎች
አዲስ ግደይ – ሲዳማ ቡና
ለጅማ አባጅፋር ተከላካዮች እጅግ ፈታኝ በነበረው የሲዳማ ቡና የአጥቂ ሥፍራ ተሰላፊዎች እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበረው አዲስ ግደይ በጨዋታው አንድ ግብ ከማስቆጠሩም በላይ እንደተለመደው ጥሩ ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ተስተውሏል፤ አዲስ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መካተት የቻለ ብቸኛ ተጫዋችም ነው።
ጂኒያስ ናንጂቡ – ወልዋሎ
ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ጁኒያስ ከስሑል ሽረ ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ የመሐል አጥቂ ሆኖ የተጫወተ ሲሆን ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በፕሪምየር ሊግ የግብ አካውንቱን መክፈት ችሏል። ለመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ የተመቸ የሆነው ናሚቢያዊ አጥቂ አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች በማምለጥ እጅግ በተረጋጋ አጨራረስ ሁለት ግሩም ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።
ተጠባባቂዎች
በሳምንቱ መልካም እንቅስቃሴ ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል በግብ ጠባቂ ስፍራ የሰበታ ከተማው ዳንኤል አጃይ፣ በተከላካይ ሥፍራ የኢትዮጵያ ቡናው ፈቱዲን ጀማል፣ በአማካይ ሥፍራ የወላይታ ድቻው ተስፋዬ አለባቸው፣ የመስመር ተጫዋቾቹ ኤርሚያስ ኃይሉ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል እንዲሁም አጥቂው ብሩክ በየነ በሳምንቱ ምርጥ 11 ውስጥ በተጠባባቂነት የተካተቱ ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ