በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ የሚገኙት ስሑል ሽረዎች ከሜዳቸው ውጭ ወሳኝ አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻው ጨዋታ መልስ በሀይደር ሸረፋ ምትክ ከጉዳት የተመለሰው ጌታነህ ከበደን በመጀመርያ 11 ውስጥ ሲያካትት በተመሳሳይ ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሰው አሜ መሐመድ በተጠባባቂነት ጨዋታውን ጀምሯል። በአንፃሩ ባሳለፍነው ሳምንት በወልዋሎ በሰፊ ውጤት የተሸነፉት ሽረዎች ያለወሳኝ የውጭ ዜጋ ተጫዋቾቻቸው የዛሬውን ጨዋታ ለማድረግ ሲገደዱ አምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ወንድወሠን አሸናፊ በምንተስኖት አሎ፣ አብዱሰላም አማን በክፍሎም ገብረሕይወት፣ ሙሉዓለም ረጋሳ በአክሊሉ ዋለልኝ፣ ነፃነት ገ/መድህን በያስር ሙገርዋ እንዲሁም ብሩክ ሀዱሽ በዲዲዬ ለብሪ ምትክ ጨዋታውን ጀምረዋል።
እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ፍፁም መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት የሽረ ተጫዋቾችን አልፈው የግብ እድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውሏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉዓለም መስፍን ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ገጭቶ ወደ ግብ የሞከረው እንዲሁም በ40ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻማውና ጌታነህ ከበደ ሞክሮት ወንድወሰን ካዳነበት ኳስ ውጭ ተጠቃሽ ሙከራዎች አልነበሩም።
በ25ኛው ደቂቃ የጨዋታውን ይዘት ልትቀይር የምትችል አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። የሽረ ተጫዋቾች ጌታነህ ከበደ ላይ በሰሩት ጥፋት ፈረሰኞቹ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኝም ጌታነህ ከበደ የመታት ኳስ ወደ ውጪ ልልወጣ ችላለች። የፍፁም ቅጣት ምት መሰጠቱ ያልተዋጠላቸው የሽረ ተጫዋቾችም በከፍተኛ ሁኔታ ተቋውሞ ሲያሰሙ የተስተዋለ ሲሆን በዚህም አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች የማሸነፊያ ግብን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት እምብዛም ፍሬያማ አልነበረም። ጌታነህ ከበደ ባደረጋትና የሽረ ተጫዋቾች ተደርበው ባወጡበት ሙከራ በጀመረው አጋማሽ ጊዮርጊሶች በቀሪ ደቂቃዎች ውስጥ ጋዲሳ መብራቴ ከሳጥን ውጭ እንዲሁም ሀይደር ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት የሞከራትና ከግቡ አናት በላይ ከወጣችባቸው ሙከራ በቀር ወደ ግብ መቅረብ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጋዲሳ መብራቴን በዛቦ ቴጉይ ተክተው በመግባት በተሻለ የማሸነፍ ፍላጎት ጨዋታውን ቢጀምሩም ከፍላጎት በዘለለ የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ለሙሉ 90 ደቂቃ በአሉታዊ አቀራረብ ፍፁም መከላከልን ለመረጡት ሽረዎች በመላ ክፍለ ጊዜ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በማዘግየት እንዲሁም በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች የማጥቃት ተነሳሽነታቸው ከፍ ሲል ይስተዋል የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊሶችን ፍጥነት በማውረድ በኩል የስሑል ሽረው ግብጠባቂ ወንድወሰን አሸናፊ ኳስ በማዘግየት የጨዋታው መወያያ ርዕስ ሆኖ ውሏል።
በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ በመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረው የስሑል ሽረው የመሐል ተከላካይ ዮናስ ግርማይ በእለቱ አርቢትር ፌደራል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ቢመለክትም ለተወሰኑ ደቂቃዎች በሜዳ ላይ ቆይታ ካደረገ በኃላ በረዳት ዳኛው ጥቆማ መሠረት ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።
አሰልቺ የነበረው ጨዋታው የጠሩ የግብ እድሎችን ሳያስመለክተን 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ