በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን ያደረጉት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።
አዳማዎች ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሰበታ ከተማ ጋር ያለ ጎል አቻ ከተለያየው ስብስባቸው ሱሌይማን መሐመድ፣ ሱሌይማን ሰሚድ እና አማኑኤል ጎበናን በማሳረፍ መናፍ ዐወል፣ ፉአድ ፈረጃ እና ዱላ ሙላቱን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል። በሜዳቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባዶ ለባዶ ተለያይተው ወደዚህ ጨዋታ የመጡት ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ ከባለፈው ስብስባቸው ግብጠባቂው መክብብ ደገፉ፣ ያሬድ ዳዊት፣ ተስፋዬ አለባቸው እና ነጋሽ ታደሰን አሳርፈው ግብጠባቂው መኳንንት አሸናፊ፣ ይግረማቸው ተስፋዬ፣ ተመስገን ታምራት እና ዘላለም ኢያሱን በመያዝ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ለእግርኳስ ሠላም! ሠላም ለኢትዮጵያ! በመመኘት የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የሠላም ምልክት የሆነች እርግብ በመልቀቅ ያሳዩት ተግባር በስታዲየም የነበረውን ተመልካች ምስጋናውን በጭብጨባ ተቸሯቸዋል።
ፌደራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በመሩት በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ የነበረው ትልቁ ቁም ነገር ጎል መቆጠሩ ካልሆነ በቀር በሁለቱም በኩል ብዙም ማራኪ ያልሆነ፣ ግልፅ የሆኑ የጎል ሙከራዎች ያልተመለከትንበት ጨዋታ ሆኖ ታይቷል። በሁለቱም በኩል የሚቆራረጡ ኳሶች እየተመለከትን ባለበት ሰዓት በአዳማ የዘንድሮ ውድድር ዓመት መልካም እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ ከራሱ የሜዳ ክፍል የነጠቀውን ኳስ ወደ ፊት ገፍቶ በመሄድ በጥሩ መንገድ ለዳዋ ሆቴሳ ሰንጥቆ ያቀበለውን ዳዋ በጥሩ አጨራረስ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል።
ባዬ ገዛኸኝን ተደራሽ ያድገው የወላይታ ድቻ የማጥቃት እንቅስቃሴ አብዛኛዎቹ ለእርሱ የሚጣሉ ኳሶች ይበላሹ እንጂ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በእንቅስቃሴው የአዳማ ተከላካዮችን በግሉ ሲፈትን እንደነበረ ተመልክተናል። መሐል ሜዳ ላይ ተገድቦ በሚደረግ ኳስ ማንሸራሸር በሚሰሩ ስህተቶች ኳሱ እየተቆራረጠ ጨዋታው ቀጥሎ በ42ኛው ደቂቃ በአዳማ በኩል በረከት ደስታ በግራ መስመር ወደ ጎል ያሻገረውን የድቻ ተከላካይ አንተነህ ጉግሳ ኳሱን አርቃለው ሲል በእግሩ ስር ስትሾልክ ዱላ ሙላቱ ነፃ ኳስ አግኝቶ ያልተጠቀመባት ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት ከማምራታቸው አስቀድሞ በአዳማ በኩል ያልተጠቀሙባት የመጨረሻ የግብ ዕድል ነበረች።
ከመጀመርያው አጋማሽ ፍፁም በተቃራኒው ሳቢ እንቅስቃሴ እና በርከት ያሉ የጎል ሙከራዎች የተመለከትንበት ሁለተኛው አጋማሽ ገና በጨዋታው ጅማሬ በደቂቃዎች ልዩነት የጎል አጋጣሚዎች አዳማ ከተማዎች አግኝተው ያልተጠቀሙበት ሙሉ ለሙሉ የጨዋታውን ከባቢ መቀየር የሚችል ነበር። 47ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከመስመር አሻግሮት ቡልቻ ሹራ በግንባሩ ኳሱን ከመሬት አንጥሮ ግብጠባቂው መኳንንት አሸናፊ ያዳነበት፣ በ49ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከርቀት በአስገራሚ ሁኔታ በጠንካራ ምት የመታውን ኳስ በድጋሚ ግብጠባቂው መኳንንት አሸናፊ ወደ ውጭ ያወጣበት የአዳማዎችን የጎል መጠን ማስፋት በቻለች ነበር።
ሁለት ያለቀለት የጎል ሙከራ ቢደረግባቸው በሂደት ወደ ጨዋታው ለመመለስ እየተነቃቁ የመጡት ወላይታ ድቻዎች ከረዥም ርቀት ተሻግራ የአዳማ የግብ ክልል ውስጥ የምኞት ደበበን ጀርባ ነክታ ባዬ ገዛኸኝ እግር ስር የገባችውን ኳስ ባዬ ወደ ጎል ሊመታው ሲል ምኞት ደበበ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ባዬ ገዛኸኝ ወደ ጎልነት በመቀየር ወላይታ ድቻን አንድ አቻ ማድረግ ችሏል።
ብዙም ሳይቆይ መረጋጋት ያቃታቸውን የአዳማ ተጫዋቾች ስህተት ተጠቅሞ በ59ኛው ደቂቃ በዕለቱ በወላይታ ድቻ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው እድሪስ ሰዒድ አንድ ጊዜ ብቻ ኳሷን ወደ ፊት በመግፋት ከሳጥን ውጭ ከጎሉ ፊት ለፊት የመታው ግሩም ኳስ ወላይታ ድቻን መሪ ወዳደረገ ጎልነት ተቀይሯል።
ከመምራት ተነስተው ወደ መመራት የተመለሱት አዳማዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ጫና በመፍጠር በጀመሩበት ቅፅበት 62ኛው ደቂቃ ላይ አንተነህ ጉግሳ በረከት ደስታ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር አዳማን አቻ ማድረግ ችሏል።
የጨዋታው ግለት በጥሩ ፉክክር ይቀጥል እንጂ አዳማዎች ከወላይታ ድቻ በተሻለ በመንቀሳቀስ የጎል አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። 78ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ተስፋዬ ነጋሽ ከዳዋ ሳጥን ውስጥ የተቀበለውን አንድ ተከላካይ በማለፍ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ሳይጠቀምበት የቀረው፣ 81ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ ከነዓን ወደ ፊት በመሔድ ሳጥን ውስጥ ሊገባ ሲል በተከላካዮች ሲመለስበት ከኃላ የነበረው በረከት ደስታ ኳሷን አግኝቶ አክርሮ ወደ ጎል የመታውን ግብጠበቂው መኳንንት አሸናፊ በሚገርም ሁኔታ ወደ ውጭ ያወጣት አዳማዎች መምራት የሚችሉባቸው የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት ባዬ ገዛኸኝ ከሚፈጥራቸው አደጋዎች ውጭ መከላከል ላይ ያመዘኑ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ ከነዓን ከርቀት የተሻገረውን ኳስ በቀላሉ ተቆጣጥሮ አንድ ተከላካይ በማለፍ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ወደ ጎል የመታውን ግብጠባቂው መኳንንት አሸናፊ በሚገርም ብቃት አዳነው እንጂ ውጤቱ ይቀየር ነበር።
በመጨረሻም የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታቸውን በተመሳሳይ ያለ ጎል አቻ ውጤት ያጠናቀቁት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻም የዛሬውንም ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቀው ወጥተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ