ሪፖርት | ሰበታ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ወልቂጤ ላይ አስመዝግቧል

በአራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሜዳው ጨዋታውን በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታድየም ያደረገው ወልቂጤ ከተማ ሰበታ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ወልቂጤ ከተማ ባለፈው ሳምንት ፋሲል ከነማን ካሸነፈበት ስብስቡ ኤፍሬም ዘካርያስ (በቅጣት) እና ሄኖክ አወቀን በፍፁም ተፈሪ እና አህመድ ሁሴን በመተካት ወደ ሜዳ ሲገባ በአንፃሩ ሰበታዎች ከአዳማ ጋር አቻ ከወጡበት ስብስብ ውስጥ ተከላካዩ ወንድይፍራው ጌታሁን እና አማካዩን ታደለ መንገሻን አስወጥተው በምትካቸው መስዑድ መሐመድ እና ሳቪዮ ካቩጎን ተጠቅመዋል።

ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጀምሮ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የጀመሩት ወልቂጤዎች በ1ኛው ደቂቃ በጫላ ተሺታ ሙከራ የሰበታ ከተማዎችን ግብ መፈተሽ የጀመሩ ሲሆን በ4ኛው ደቂቃ የጨዋታውን ገፅታ ሊለውጥ የሚችል ክስተት ተከስቷል። ፍፁም ተፈሪ ወደፊት የጣለውን ኳስ ጫላ የተሻ በፍጥነት ከሁለት ተከላካዮች መሐል ተስፈንጥሮ በመውጣት ብቻውን ይዞ ቢሄድም በሰበታ ተከላካይ ጥፋት ተሰርቶበት ወድቋል። በዚህም ተጫዋቹ ከሜዳ መወገድ አለበት በሚል ተጨዋቾች ከዳኛው ጋር እስጠ ገባ ውስጥ ገብተው ታይተዋል።
ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመጣል የወልቂጤ ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ሰበታዎች ጎል በጊዜ ማስቆጠር ችለዋል። በሰባተኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ መስዑድ መሐመድ ያሻማውን ኳስ አግኝቶ ወደግብነት ለውጦታል።

ከግቡ መቆጠር በኃላ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት የነበረው የሰበታዎች እንቅስቃሴ በአንፃራዊነት ጫና እንዲፈጠርባቸው አድርጓል። ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት የሚያደርጉት ወልቂጤዎች በአንፃሩ በ18ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ፍፁም ተፈሪ ያሻማውን ጃኮ በግንባሩ ሞክሯት ወደ ውጪ የወጣች እንዲሁም በ25ኛው ደቂቃ አዳነ በላይነህ በተመሳሳይ ከቀኝ መስመር አሻምቶለት አህመድ ሁሴን በግንባሩ ገጭቶ ዳንኤል አጄይ ያዳነበትን ሙከራ አድርገዋል።
በሂደት እየቀዘቀዘ በመጣው ጨዋታ ወልቂጤዎች የተሻለ ኳስን የመቆጣጠር እንዲሁም በሰበታ ከተማዎች በኩል በመልሶ ማጥቃት የመጫወት አዝማሚያዎችን ተመልክተናል። አህመድ ሁሴን በ32ኛው ደቂቃ ብቻውን አግኝቶ ወደ ግብ ለወጠው ሲባል አዲስ ደርሶ ተደርቦ ያወጠበት እንዲሁም ጫላ ተሺታ በ40ኛው ደቂቃ የሞከረው ሙከራ በወልቂጤዎች በኩል የታዩ ሌሎች ሙከራዎች ነበሩ።

በተቃራኒው በሰበታዎች በኩል በ37ኛው ደቂቃ ባኑ ዲያዋራ ከግራ መስመር አጥብቦ የመታውን ኳስ ሶሆሆ ሊያድንበት ችሏል። በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ባኑ ዲያዋራ አየር ላይ ከፍፁም ተፈሪ ጋር ተጋጭቶ በመውደቁና ጉዳቱ ከፍ በማለቱ በአንቡላንስ ከሜዳ ወጥቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ይልቁንም ረጃጅም ኳሶች በዝተውበት የነበረ ሲሆን ሰበታዎች ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ በአንፃሩ ወልቂጤዎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በተለይ ተቀይረው ገቡት ሳዲቅ ሴቾ ከቀኝ መስመር በሚያሻማቸው ኳሶች እንዲሁም አብዱልከሪም ወርቁ ወደፊት በሚጥላቸው ኳሶች ዕድል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም የሰበታን የተከላካይ ክፍል በቀላሉ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

79ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት በረከት ጥጋቡ ከሰበታ ከተማ ተጫዋቾች ጋር ታግሎ ያቀበለውን ጫላ ተሺታ ወደ ግብ የላካትና ዳንኤል አጄዬ ያዳነበት፣ በ80ኛው ደቂቃም አዳነ አባይነህ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው በሰራተኞቹ በኩል የሚጠቀሱ ሲሆን በሞግሌዎቹ በኩል ደግሞ ጌቱ ከቀኝ መስመር ያሻማውንና በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው አሊ ባድራ ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ በሁለተኛ አጋማሽ የታዩ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት 0-1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ ከተማ የውድድር ዓመቱትን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ በማስመዝገብ ከሠንጠረዡ ግርጌ መውጣት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ