የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ሰበታ ከተማ

በ4ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ በአስቻለው ግርማ ብቸኛ ጎል ወልቂጤ ከተማን አሸንፈው የዓመቱ መጀመሪያ ሶስት ነጥብ ካሳኩ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።


“ተከታታይ ሽንፈት ይዞት ከሚመጣው ተፅእኖ ለመውጣት ተጫዋቾቼ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል” ውበቱ አባተ – ሰበታ ከተማ

” ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር፤ ተከታታይ ሽንፈት ይዞት ከሚመጣው ተፅእኖ ለመውጣት ተጫዋቾቼ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይህ የመጀመሪው ሦስት ነጥባችን ነው፤ ቡድናችንም ከእለት ወደ እለት እየተሻሻለ ነው። ከዚህም በኋላ ጠንክረን በመስራት ወደ ሊጉ ሠንጠርዥ ከፍ ማለት እንችላለን።

” ከሜዳችን ውጭ ነው የተጫወትነው፤ ሜዳው አስቸጋሪ ነው፤ የገጠምነው ቡድን ጥሩ መጫወት የሚችል ነው፤ በሁለታችንም በኩል ብርቱ ፉክክር አድርገናል። የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ ማሳካት መቻላችን ደስ ብሎኛል።”



” ተጋጣሚያችን ልምዳቸው ለዛሬ ጨዋታ ጠቅሟቸዋል” ደግአረግ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

“ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነበር። በእኛ በኩል ውጤቱን ለመቀልበስ እንዲሁም ተጋጣሚያችን መሪነቱን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ያሳኩበት ነው። ቡድናችን ውጤቱን ለመለወጥ ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ነበር። በመጀመሪያው ደቂቃዎች የገባብን ጎል ተፅዕኖ ውስጥ ቢከተንም በተቻለን መጠን ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። ተጋጣሚያችን ያለው ስብስብ በሊጉ ረጅም ጊዜ የመጫወት ልምድ መያዛቸው ለዛሬ ጨዋታ ጠቅሟቸዋል።

“ቡድናችን በቶሎ ወደ አሸናፊነት ይመለሳል፤ ተጫዋቾቼ ጋር ትልቅ መነሳሳት ነው ያለው። የዛሬው ጨዋታ ውጤት ባይገባንም እግርኳስ እንዲህ ነው፤ አንዳንዴ ያላሰብከው ውጤት ይገጥማል። በቀጣይ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ