የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ አርባምንጭ ሁለተኘመ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። ደቡብ ፖሊስ፣ ጌዴኦ ዲላ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደግሞ የመጀመርያ ድላቸውን አሳክተዋል፡፡
አርባምንጭ ከተማ 2-0 የካ ክ/ከተማ
(በፋሪስ ንጉሴ)
እንደተለመደው በርካታ ደጋፊዎች የተገኙበት የአርባምንጭ ከተማ እና የየካ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ቀዝቀዝ ባለ ድባብ የተጀመረ ሲሆን ሁለቱም ክለቦች ጥንቃቄ የተሞላበትና ከማጥቃት የተገደበ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተው በ22ኛው ደቂቃ ከወርቅይታደስ አበበ የተሻገረለትን ኳስ ቶጓዊው አጥቂ ኤደም ኮድዞ በግሩም ሁኔታ በግንባር ገጭቶ አርባምንጭ ከተማን መሪ እንዲሆን አስችሏል።
ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላ ጨዋታው ፈጣን እንቅስቃሴ ይታይበታል ተብሎ ቢጠበቅም ሁለቱም ክለቦች የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴያቸው ማራኪ ባለመሆኑ የተነሳ አሰልቺ መልክ ይዟል። በዚህ ወጣ ገባ በሚለው የሁለቱ ክለቦች እንቅስቃሴ ላይ አልፎ አልፍም ቢሆን ሙከራዎች ይታዩ ነበር። 30ኛ ደቂቃ ለይ ንጉሥ ጌታሁን በጥሩ ሁኔታ ተከላካዮችን አታሎ ወደ ውጭ የመታው ከመጀመርያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። የመጀመርያው አጋማሽም በዚህ መልኩ ጥሩ እንቅስቃሴ ሳይታይበት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴ የእንግዳዎቹን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶች ላይ ያተኮረ የማጥቃት እንቅስቃሴ ይዘው በመግባት ሙከራዎችን ለማድረግ የጣሩት አርባምንጮች 48ኛው ደቂቃ ለይ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት በመጠቀም አሸናፊ ኤሊያስ አክርሮ መቶ በግብ ጠባቂው የመለሰበት፣ 50ኛው ደቂቃ ላይ አቦነህ ገነቱ ከርቀት አክርሮ መቶ እንደገና በግብ ጠባቂው ተመልሶ ወደ ውጭ የወጣበት የአርባምንጭ ከተማ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
በእንግዳዎቹ የካዎች በኩል 58ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ከበደ የአርባምንጭ ከተማ ተከላካዮች የፈጠሩትን ስህተት መጠቀም ሲችል ወደ ውጭ የወጣበት ሙከራ የሁለተኛውን አጋማሽ ከመጀመርያው አጋማሽ በሙከራ እንዲሻል ያደረጉበት ነበር።
አርባምንጮች እሱባለው ፍቅሬንና ፍቃዱ መኮንን ወደ ሜዳ ቀይረው ካስገቡ በኋላ በፈጣን እንቅስቃሴ ጥሩ የግብ እድሎችን ለመፈጠር ችለዋል። በተለይ ፍቃዱ መኮንን በረጅሙ የሚጣሉለትን ኳሶች ተከላካዮችን በማምለጥ ከግብ ጠባቂው ጋር እስከ መገናኘት የደረሰ እንቅስቃሴ አድርጓል። ፍቃዱ የተከላካዮችን አቅም ሲፈትን ቆይቶ 73ኛው ደቂቃ ላይ የግል ችሎታውን ተጠቅሞ ግብ ጠባቂውን ጭምር በማለፍ ለባለሜዳው አርባምንጭ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል።
በድጋሚ ከግቡ መቆጠር በኋላ 78ኛ ደቂቃ ላይ ፍቃዱ መኮንን ከአቦነህ ገነቱ በተረጋጋ ሁኔታ ከመሃል የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ግብ ጠባቂው አምክኖበታል። ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ደቡብ ፖሊስ 2-0 ነጌሌ አርሲ
(በቴዎድሮስ ታከለ)
አስር ቢጫ ካርድ እና ሁለት ቀይ ካርድ በታየበት በዚህ ጨዋታ ነገሌዎች ተሽለው በታዩበት የመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃዎች ምንም እንኳን የኳስ ቁጥጥሩን በበላይነት የውሰዱት እንጂ ደቡብ ፖሊሶች በተደራጀ የማጥቃት ሂደት ላይ የሚታሙ አልነበሩም፡፡ በዚህ መንገድ ቢጫ ለባሾቹ 19ኛው ደቂቃ ዩጋንዳዊው አማካይ ኢቫን ሳካዛ ከርቀት አክርሮ መቶ የግቡን የላይ ብረት ነክታ በወጣችበት አጋጣሚ ቀዳሚ የጨዋታውን ሙከራ አድርገዋል፡፡
ነገሌዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ የሚያገኙበት ክፍት ዕድል አምክነዋል፡፡ 21ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂው ነጋ ከበደ በረጅሙ ከግብ ክልል የላከለትን ኳስ አጥቂው አላዛር ዝናቡ አግኝቶ አገባው ሲባል ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ አውጥቶበታል፡፡ በዚህ ሁኔታ የነገሌዎችን ክፍተት ሲጠብቁ የነበሩት ፖሊሶች 25ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። ሚካኤል ልዑልሰገድ የመከላከል ክፍተታቸውን ተጠቅሞ በቀኝ በኩል ያቀበለውን ያሬድ መሀመድ አስቆጥሮ ባለሜዳውን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር የእለቱ ዳኛ በተደጋጋሚ ከሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ጋር የሚገባቸው ያልተገቡ እሰ ሰጣ ገባ የጨዋታውን መንፈስ እያቀዘቀዘው ከመምጣቱ ባለፈ አራት ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድን በዚሁ ሂደት ተመልክተናል፡፡ 36ኛው ደቂቃ ብሩክ ኤልያስ ከእለቱ ዳኛ ጋር ምክንያቱ ባልታወቀ መልኩ በተፈጠሩ ክርክሮች በፍጥነት ሁለት ቢጫ ተመልክቶ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ቢጫ ለባሾቹ ተጨማሪ የማስቆጠር አጋጣሚን በምትኩ ማመጫ አማካኝነት አግኝተው በቀላሉ አምክነዋል፡፡
ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ መጀመሪያ ከታየበት ክፍተት መሻሻሎችን ቢያሳይም ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገዷል፡፡ አማካዩ ቦታ ላይ የታዲዮስ ወልዴ ከመጀመሪያው አጋማሽ ድክመቱ ተሻሽሎ ቦታውን ሳያስከፍት በመጫወት ለተከላካዮቹም ሆነ ለአጥቂዎቹ ሽንፋን በመስጠቱ ድክመታቸውን ባለሜዳዎቹ ሊሸፈንላቸው ችሏል፡፡ 53ኛው ደቂቃ ላይም ታዲዮስ ወደ ቀኝ በኩል ያሳለፋትን ኳስ ያሬድ መሀመድ አየር ላይ እንዳለች ለአማካዩ ምትኩ ማመጫ ሰጥቶት ተጫዋቹ በግንባር ገጭቶ የደቡብ ፖሊስን ሁለተኛ ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡
በዚህኛው አጋማሽ የነገሌ አርሲ ምክትል አሰልጣኝን ጨምሮ በድምሩ ስድስት ቢጫ ካርድ እና አንድ ቀይ ካርድ የታየበት ነበር፡፡ ነገሌ አርሲዎች ቀዝቀዝ ባሉበት በዚህኛው ክፍለ ጊዜ 80ኛው ደቂቃ ላይ ወንድማገኝ ሊሬ ከዳኛው ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ በሁለተኛ ቢጫ ተወግዷል፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ደቡብ ፖሊስ 2-0 አሸናፊ ሆኖበታል፡፡
ሌሎች ጨዋታዎች
(በአምሀ ተስፋዬ)
ጌዴኦ ዲላ በሜዳው ከንባታ ሺንሺቾን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። የባለሜዳዎቹን ብቸኛ ጎልም በ88ኛው ደቂቃ ዘመድኩን ሾርኮ ማስቆጠር ችሏል።
አዲስ አዳጊው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሌላው አዲስ አዳጊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን ገጥሞ 1-0 አሸንፏል። ተስፋዬ ደርቤም ብቸኛዋ ጎል ባለቤት ነው።
ባቱ ላይ ባቱ ከተማ ከቡታጅራ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። እንግዶቹ በድንቅነህ ከበደ ጎሎች 2-0 መምራት ቢችሉም ባቱዎች ያሬድ ወንድማገኝ እና ሱራፌል አየለ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች አቻ መውጣት ችለዋል።
መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጽያ መድን ከስልጤ ወራቤ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሳይከናወን ቀርቷል። በ9፡00 ሊካሄድ መርሀግብር የወጣለት ጨዋታ ቦታው ላይ የፀጥታ ኃይል ባለመገኘቱ ነው ሳይደረግ የቀረው።
በሜዳው ላይ የሁለቱም ቡድን አባላት ሜዳው ውስጥ የተገኙ ቢሆንም የፀጥታ ኃይል ሳይኖር ጨዋታው እንዳይጀመር በሚለው የፌዴሬሽኑ ህግ መሰረት ከ30 ደቂቃ በላይ የፀጥታ ኃይል ቢጠበቅም ሳይመጣ በመቅረቱ ሳይደረግ ቀርቷል። ይህን ተከትሎ የዳኞቹን እና የኮሚሽነሩን ሪፖርት የሚጠብቀው የከፍተኛ ሊግ ኮሜቴ በሳምንቱ አጋማሽ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ