ባለፈው ሳምንት ከተጋጣሚዎቻቸው ጋር በተመሳሳይ ያለ ጎል ነጥብ ተጋርተው የወጡት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋርን የሚያገናኘው ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።
ጅማ አባ ጅፋር የውድድር ዓመቱ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በሜዳው ጨዋታ ያደርጋል። ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን ከዐምና በይደር በተላለፈ ቅጣት ምክንያት አዳማ ላይ ለማድረግ የተገደደው ጅማ አባ ጅፋር አዲስ በተገነባው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ላይ ፈረሰኞቹን የሚያስተናግድ ይሆናል።
አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጪ እንደማከናነወናቸው ለመከላከል ቅድሚያ የሚሰጥ ቡድን አስመልክተውናል። ባለፈው ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ መሪው ወልዋሎን ገጥመው ወሳኝ አንድ ነጥብ ይዘው እንዲመለሱም ጠጣር የነበረው የኋላ መስመር ከፍተኛ እገዛ አድርጎላቸዋል።
ይህ የቡድኑ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት በነገው ጨዋታም የግብ እድል ለመፍጠር እና ጎል ለማስቆጠር በሚቸገረው የፈረሰኞቹ የአጥቂ ክፍል ይፈተናል ተብሎ ባይጠበቅም በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ያለበት ድክመት ግን በነገው ጨዋታም ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል ይገመታል። በተለይም ተጋጣሚው ጊዮርጊስ የሊጉ ምርጥ የመከላከል ሪከርድ ያለው ቡድን መሆኑ ለጅማ አጥቂዎች ከባድ ቤት ስራ የሚሰጥ ነው።
ጅማ አባጅፋር በጉዳትም ሆነ በቅጣትም የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ቢሆንም የውጪ ዜጋ ተጫዋቾቹን ግን አሁንም አይጠቀምም። በወረቀት ጉዳዮች ምክንያት የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂ፣ ተከላካይ እና አጥቂ ተጫዋቾቻቸውን ከዓመቱ መጀመርያ ጀምሮ መጠቀም ያልቻሉት አሰልጣኝ ጳውሎስ አማራጮቻቸውን እንዳጠበባቸው ባለፉት ጨዋታዎች የታየ ሲሆን ጉዳዩ በቶሎ እልባት ካላገኘ በቀጣይ ሊፈጠሩ ከሚችሉ የተጫዋቾች ጉዳቶች ጋር ተደምሮ ለቡድኑ ጉዞ እክል መሆኑ አይቀሬ ነው።
በሊጉ እስካሁን ድረስ ግብ ያላስተናገዱት ፈረሰኞቹ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ በማለም ወደ ጅማ አምርተዋል።
ጊዮርጊሶች ያለ ዋና ተመራጮቻቸውም (ማታሲ እና አስቻለው) የጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ባለቤቶች መሆናቸውን ቢያረጋግጡም እስካሁን ግን በተከታታይ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የሚያበቃቸውን የማጥቂያ ቀመር ለማግኘት ተቸግረዋል።
ቡድኑ አሁንም ሳልሀዲን ሰዒድ በማይኖርባቸው ጨዋታዎች ላይ አማራጭ ግብ አዳኝ እንደሌለው በግልፅ እየታየ የሚገኝ እውነታ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ከሽረ ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ በፊት መስመር መጫወት የሚችሉ አራት ተጫዋቾችን ይዞ ቢገባም እምብዛም ውጤታማ ካልሆኑት በረጃጅሙ ከሚላኩ ኳሶች ውጭ አማራጭ የማጥቂያ መንገዶች የሌሉት ስለመሆኑ ይስተዋላል። በክረምቱ ቡድኑን የተቀላቀሉት እንደነ ሀይደር ሸረፋና አቤል እንዳለን የመሰሉ ተጫዋቾችን ጠንካራ ጎን ለመጠቀም እምብዛም ያልፈቀዱት አሰልጣኙ ይህን መላ ያጣውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማገዝ በቀጣይ የእነዚሁ ተጫዋቾች ተሳትፎ የሚጠይቅ ይመስላል።
ፈረሰኞቹ ከጉዳት መልስ አስቻለው ታመነ እና ፓትሪክ ማታሲን በስብስባቸው በማካተት ወደ ጅማ ያመሩ ሲሆን ሳላሀዲን ሰዒድ እና ለአለም ብርሀኑ አሁንም ማገገም አልቻሉም። ባለፉት ጨዋታዎች በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው መሀሪ መና እና ሳላዲን በርጊቾ ደግሞ በመጠነኛ ጉዳት ወደ ጅማ አላመሩም።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ለአራት ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ጊዜ ድል ሲያስመዘግብ ጅማ አባ ጅፋር አንድ ጊዜ አሸንፏል። ቀሪውን ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።)
– በአራቱ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ 6 ጎሎችን ሲያስቆጥር፤ ጅማ 2 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ሰዒድ ሀብታሙ
ወንድማገኝ ማርቆስ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ
ሄኖክ ገምቴሳ – ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ኤልያስ አህመድ
ጀሚል ያዕቆብ – ብሩክ ገብረዓብ – ኤርሚያስ ኃይሉ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ባህሩ ነጋሽ
አብዱልከሪም መሐመድ – ምንተስኖት አዳነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ሄኖክ አዱኛ
ሙሉዓለም መስፍን – የአብስራ ተስፋዬ – ሀይደር ሸረፋ
አቡበከር ሳኒ – ዛቦ ቴጉይ – አቤል ያለው
© ሶከር ኢትዮጵያ