ሁለቱ አሰልጣኞች የቀድሞ ክለቦቻቸውን በተቃራኒ የሚገጥሙበት የሰበታ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በነገው ዕለት በብቸኝነት የሚካሄደው እና ሁለት ተቀራራቢ የአጨዋወት መንገድ ያላቸው ቡድኖችን የሚያገናኘው ይህ የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ ማራኪ እንቅስቃሴ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአስቸጋሪ የሊግ አጀማመር በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ ሆሳዕና ተጉዞ ወልቂጤን በማሸነፍ በጥሩ መነቃቃት የነገውን ጨዋታ የሚያደርገው ሰበታ ከተማ ተከታታይ ድል በማስመዝገብ በሰንጠረዡ አናት ወደሚገኙ ቡድኖች መጠጋትን አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።
ቡድኑ አመዛኙ በክረምቱ በተሰባሰቡ ተጫዋቾች እንደመሞላቱ የውህደት ችግር የሚታይበት ሲሆን ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ከታየው የፊት አጥቂዎችን ኢላማ ያደረጉ ቀጥተኛ የማጥቃት አቀራረብ ኳሶች እምብዛም ውጤታማ እንዳልሆነም ተስተውሏል። በዚህም ቀስ በቀስ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደሚመርጡት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መምጣቱ አይቀሬ ይመስላል። በነገው ጨዋታም ከተጋጣሚው በተሻለ ኳሱን በመቆጣጠር የበላይነቱን ለመውሰድ የሚያስችለውን አቀራረብ ይመርጣል ወይስ የፋሲልን እንቅስቃሴ በመግታት በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ይቀርባል የሚለው የሚጠበቅ ነው።
ቡድኑ በነገው ጨዋታ የሚገጥመው ዐምና አሰልጣኝ ውበቱ ያሰለጠኑትና በአጨዋወትም ሆነ በተጫዋቾች ረገድ እምብዛም ለውጥ ያልተደረገበት ፋሲል ከነማን መሆኑም የቡድኑን ደካማ ጎን ለመለየት ፍንጭ የሚሰጥ በመሆኑ ለሰበታ መልካም አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።
ሰበታ በነገው ጨዋታ የረጅም ጊዜ ጉዳት ያስተናገደው አንተነህ ተስፋዬን የማይጠቀም ሲሆን ባለፈው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ባኑ ዲያዋራም ለነገው ጨዋታ የማይደርስ ይሆናል።
በሜዳቸው በሰፊ የጎል ልዩነት እና በፍፁም ብልጫ ጨዋታዎች እያሸነፉ ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እየተቸገሩ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በነገው ዕለት ከሜዳቸው ውጭ ነጥብ ይዘው በመመለስ ወደ ሊጉ አናት ለመውጣት አልመው እንደሚገቡ ይጠበቃል። በዚ ዓመት ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ አልፈው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ የሚደርስ ቡድን የሰሩት ዐፄዎቹ እየተሻሻሉ የመጡበት ተሻጋሪ ኳሶች እና ፈጣን የመስመር ሽግግር ሰበታ ላይ የበላይተነት ለመውሰድ ቁልፉ መሳርያቸው እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዐፄዎቹ በነገው ጨዋታ የመሐል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ከተጋጣሚያቸው ቀላል ፈተና እንደማይጠብቃቸው እሙን ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከሜዳቸው ውጭ ጨዋታዎች ግብ ያለማስቆጠር ችግራቸውን ቀርፈው መግባት ግድ ይላቸዋል።
ፋሲሎች በነገው ጨዋታ ጉዳት ላይ ያሉት እንየው ካሣሁን፣ ሰለሞን ሀብቴ እና አብዱራህማን ሙባረክን ግልጋሎት አሁንም አያገኙም።
እርስ በርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል አጃይ
ጌቱ ኃይለማርያም – ሳቪዮ ካቩጎ – አዲስ ተስፋዬ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ
ደሳለኝ ደባሽ – መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ
በኃይሉ አሰፋ – ፍፁም ገ/ማርያም – አስቻለው ግርማ
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሀሰን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን
ሀብታሙ ተከስተ – ጋብሬል አህመድ
ኦሴይ ማዊሊ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሽመክት ጉግሳ
ሙጂብ ቃሲም
© ሶከር ኢትዮጵያ