ትላንት የተጀመረው የአምሰተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ቀጥሎ ሰበታ ከተማ እና ፋሲል ከነማ 3-3 አቻ ተለያይተዋል።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማህየኅበር ለቀድሞ አሰልጣኛቸው ውበቱ አባት፣ ለቡድን መሪያቸው ሀብታሙ ዘዋለ፣ ለቀድሞ ተጨዋቻቸው ታደለ ባይሳ እና ለሶከር ኢትዮጵያ (ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ) ስጦታ አበርክተዋል።
ሰበታ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አምርተው ወልቂጤን 1-0 ካሸነፉበት የተጨዋች ስብስብ አንድ ተጨዋች ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም ባኑ ዲያዋራን በሲይላ ዓሊ ባድራ ተክተዋል። ተጋባዦቹ ፋሲል ከነማዎችም በተመሳሳይ በሜዳቸው ሶስት ነጥብ እና ሶስት ጎል ካስመዘገቡበት የሃዲያ ሆሳዕና ጨዋታ አንድ ተጨዋች ለውጠዋል። በዚህም ጋብሬል አህመድን በበዛብህ መለዮ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ወደ ግብ በፍጥነት ያመሩት ፋሲሎች የመጀመሪያ የመዓዘን ምት አግኝተው ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ይህ የፋሲል ፈጣን አጀማመር ያላስደነገጣቸው ሰበታዎች በ5ኛው ደቂቃ በጌቱ ኃይለማርያም አማካኝነት የራሳቸውን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝረዋል። በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥር የበላይ የነበሩት ፋሲሎች ቶሎ ቶሎ የሰበታ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ቢያደርጉም ፍሬያማ መሆን አልቻሉም። በተቃራኒው ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረግ ፈጣን ሽግግር ጨዋታውን የቀጠሉት ሰበታዎች በ10ኛ ደቂቃ መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ኃ/ሚካኤል አደፍርስ በግራ መስመር ያገኘውን ኳስ ወደ መሃል አሻምቶት አስቻለው ግርማ ቢሞክረውም የግቡ ቋሚ መልሶታል። ነገር ግን በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፍፁም ገ/ማርያም ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ አድርጓል።
ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያለሙ የሚመስሉት ፋሲሎች በ13ኛው ደቂቃ ሙጂብ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት በሱራፌል አማካኝነት ወደ ግብ መተው ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። ገና በጊዜ መሪ የሆኑት የአሰልጣኝ ውበቱ ተጨዋቾች አጨዋወታቸውን ይበልጡኑ ገድበው ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። ምንም እንኳን ቡድኑ አጨዋወቱን ለመገደብ ቢሞክርም በመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን መሰንዘር አላቆመም። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም መሱዑድ መሃመድ ለሲይላ አሊ አቀብሎት ሲይላ አክርሮ በመታው ነገር ግን ኳስ እና መረብ ባልተገናኘበት አጋጣሚ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል።
በራሳቸው አጨዋወት ጥቃቶችን ለመሰንዘር ያልቦዘኑት ፋሲሎች በ26ኛው እና በ30ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ ለበዛብህ መለዬ አቀብሎት በተሞከሩ ሁለት ሙከራዎች ወደ ግብ ቀርበው ነበር። በተለይ ከሱራፌል በሚወጡ አደገኛ ኳሶች ወደ ሰበታ የግብ ክልል መድረሳቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች በ40ኛው ደቂቃ ኦሴ ማውሊ በግል ጥረቱ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ለመቀየር ጥሮ ሲይላ ባወጣበት አጋጣሚ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃም ሱራፌል ዳኛቸው እና ኦሴ ማውሊ ቡድናቸውን አቻ ለማድረግ ጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁለተኛው አጋማሽን በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመሩት ፋሲሎች ገና በጊዜ የልፋታቸውን ውጤት ማየት ጀምረዋል። ገና አጋማሹ በተጀመረ አንድ ደቂቃ ውስጥ ኦሴ ማውሊ በግራ መስመር እየገፋ ሄዶ ባስቆጠረው ጎል አቻ ሆነዋል። በዚህ ብቻ ያላቆሙት ፋሲሎች ሱራፌል ዳኛቸው ራሱ ላይ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ በተገኘ የቅጣት ምት ተጨማሪ ጎል አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ቅጣት ምቱ በሰበታ ተከላካዮች ተጨርፎ የግቡን ቋሚ ሲመልስ ያገኘው ሽመክት ኳስ እና መረብን አዋህዷል።
በፈጠሩት የትኩረት ማነስ ችግር ጎሎችን አስተናግደው ከመሪነት ወደ መመራት የተሸጋገሩት ሰበታዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። በዚህም በ51ኛው ደቂቃ ኃ/ሚካኤል ከርቀት አክርሮ በመታው ኳስ የአቻነት ጎል መፈለግ ጀምረዋል። የሰበታ ነቅሎ መውጣት የተመቻቸው የሚመስሉት ፋሲሎች በ55ኛው ደቂቃ ዳግም ጎል ለማድቆጠር ተቃርበው ነበር። ማውሊ ሶስት ተከላካዮችን ቀንሶ በአየር ላይ የሰጠውን ኳስ ለሙጂብ ያቀበለው ሽመክት ሶስተኛ ጎም ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።
አሁንም የአቻነት ጎል መፈለጋቸውን ያላቆሙት ባለሜዳዎቹ በ62ኛው ደቂቃ የፋሲል አማካዮች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ በተገኘ አጋጣሚ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሱራፌል ለሙጂብ ቃሲም ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት ፋሲሎች መሪነታቸውን አስፍተዋል።
የተጫዋች ለውጦችን በተከታታይ ማድረግ የጀመሩት ሰበታዎች በ67ኛው ደቂቃ ኃ/ሚካኤል ከግራ መስመር አሻምቶት ፍፁም በግምባሩ በሞከረው እና በ75ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ የፋሲልን ግብ ፈትሸዋል። ጨዋታው ባለበት እንዲጠናቀቅ የፈለጉት ፋሲሎች በ71ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ኢዙ አዙካ ከመሃል የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ በሞከረው ኳስ መሪነታቸውን ለማስፋት ጥረዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ ቀይረው ወደ ሜዳ ያስገቧቸው ተጨዋቾች ቡድኑን የበለጠ አነቃቅተው ባለቀ ሰዓት ግቦችን አስቆጥረዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው አራት ደቂቃ በቀኝ መስመር ያመሩት ሰበታዎች በፍፁም የግንባር ኳስ ልዩነቱን አጥበዋል። የመሃል ዳኛው ተከተል በቀለ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰኮንዶችም ዳግም በተመሳሳይ መስመር ወደ ፋሲሎች የግብ ክልል ያመሩት ሰበታዎች ከተከላካይ ጀርባ በተገኘው የአስቻለው ግርማ የግምባር ኳስ የአቻነት ጎል አስቆጥረዋል። በጅማሮ እና በማብቂያው ድራማዊ ክስተቶችን ያስመለከተው የሁለተኛው አጋማሽም 3-3 ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ