አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲችን በመተካት ኢትዮጵያ ቡናን ይዘው የአመቱን ውድድር የጀመሩት አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች ከትናንት ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ የሊግ እርከን ወደሚወዳደረው ሮያል ኤግልስ ተመልሰው ማሰልጠን መጀመራቸውን መቀመጫውን በሀገሪቷ ያደረገው ፓካቲ ዘ ሲትዝን የተሰኘው ድረ ገፅ ዘግቧል።
ድረ-ገፁ ከክለቡ የቅርብ ሰዎች አገኘውት ባለው መረጃ መሰረት አሰልጣኙ ወደ ቀድሞው ክለባቸው መመለሳቸውን እና ከሰዐት በኃላ ከተጨዋቾች ጋር ትውውቅ እንደሚያደርጉም አስነብቧል። ዘ ሲትዝን ባሳለፍነው መጋቢት ፓፒች ሮያል ኤግልስን ሲለቁ ጀርባቸው ላይ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ወደ ሰርቢያ እንዲያመሩ የህክምና ፍቃድ ጠይቀው ወደ ሀገራቸው ካቀኑ በኃላ በዛው ከክለቡ ጋር መለያየታቸውን አስታውሷል። ሮያል ኤግልስ ከአሰልጣኝ ፓፒች ጋር ከተለያየ በኃላ በተለያዩ ጊዜያት ሁለት አሰልጣኞችን ቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ሁለቱንም በውጤት ማጣት ምክንያት አሰናብቶ አሁን ከቀድሞው አሰልጣኙ ጋር በድጋሚ አብሮ ለመስራት ተስማምቷል። ክለቡ በመጪው እሁድ ከጆሞ ኮስሞስ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ በአሰልጣኝ ፓፒች እየተመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ ኤግልሶች የአሰልጣኙን ቅጥር ይፋ ያደርጋሉም ተብሏል።
ኢትዮጵያ ቡናን ይዘው በሊጉ ሦስት ጨዋታዎችን ያደረጉት አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች ቡድኑ ካደረገው የአምስተኛ ሳምንት የወልዋሎ ዓ.ዩ ጨዋታ በፊት ከኢትዮጵያ መውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ የአሰልጣኙ ምክንያትም አባታቸው ባጋጠማቸው የጤና ዕክል ምክንያት ወደ ሰርቢያ እንደሚያመሩ በመግለፅ ነበር፡፡ አሰልጣኙ በኢትዮጵያ ቡና በነበራቸው የደሞዝ ክፍያ ደስተኛ ያልነበሩ መሆኑ ሲወራ ቢቆይም በዚህ ፍጥነት ሌላ ክለብ መያዛቸው ግን አስገራሚ ሆኗል። ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኙ አባታቸውን ለማስታመም እንደተጓዙ ብቻ መረጃ እንዳለው የተነገረ ሲሆን ከጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ተተኪ አሰልጣኝ ለማግኘት ፍለጋ መጀመሩ ተሰምቷል።