የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አምስተኛ ሳምንት ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው በምድብ ለ ሀላባ ከተማ ከ መከላከያ አቻ ሲለያዩ በምድብ ሐ ደግሞ ነገሌ አርሲ እና የካ ክ/ከተማ አሸንፈዋል።
ምድብ ለ
ሀላባ ላይ መከላከያ በጭማሪ ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ከሀላባ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቷል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ይዘው ለመጫወት ገና ከጅምሩ ያለሙ ቢመስሉም የሀላባ ሜዳ ምቹነቱን የጠበቀ ካለመሆኑ የተነሳ የሚቆራረጡ ኳሶች በዝተውበት ውሏል።
ከጨዋታው በዘለለ መስመሩ ጠርዝ ላይ ጨዋታው እየተደረገ ከእግር ኳሱ ውጪ ተጨማሪ ስራዎች እየተደረጉ መኪኖችም እየተንቀሳቀሱ ተመልካቹ በተረጋጋ መንፈስ ኳሱን እንዲመለከት ያላስቻሉ ስራዎች ሲሰሩ የተመለከትንበት የዕለቱ ዳኞች በበኩላቸው ለማስቆም ያደረጉት ጥረት ካለመኖሩ የተነሳ እስከ ፍፃሜው ከጨዋታው ዕኩል እየተደረገ ሲፈፀም ያየንበት ሂደት አስገራሚ ክስተት ነበር።
ወደ መስመር ያዘነበለው የቀይ ለባሾቹ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ አቡሽ ደርቤ አዘንበለው በመጫወት ጥቃት ቢሰነዝሩም የኳሱ የመጨረሻ ማረፊያ ግን ስኬታማ አልነበረም። ሆኖም 21ኛው ደቂቃ አቡሽ በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ያሻማትን ኳስ በኃይሉ ወገኔ በግንባር ገጭቶ ብረት የገጨበት ክስተት የመጀመሪያዋ የጨዋታው ሙከራ ነበረች፡፡ መከላከያዎች በአንፃሩ ወደ ምንይሉ ወንድሙ በሚሻገሩ ረጃጅም ኳስ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረጓቸው ጥረቶችም ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። ሙከራዎቹ ምንም እንኳን በርከት ያሉ ቢሆኑም ኢላማቸውን መጠበቅ ግን አልቻሉም፡፡
የጨዋታው መንፈስ እየገላ ሲመጣ የዕለቱ ዳኛ በፀጋው ሽብሩ ሀይል የተቀላቀለባቸውን የአጨዋወት መንገዶች ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በዝምታ ማለፋቸው ጨዋታው ደብዛዛ ቅርፅ እንዲኖረው ያደረገ ሂደት ነበር፡፡ በተለይ 34ኛው ደቂቃ በመሀል ሜዳው ላይ የሀላባው አማካይ ስንታየው አሸብር በሁለት የመከላከያ ተጫዋቾች ላይ የሰራው አደገኛ አጨዋወትን በዝምታ ማለፋቸው በመከላከያ ተጫዋቾች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ለእረፍት ሁለቱ ክለቦች ሊወጡ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ አበበ ጥላሁን በግራ በኩል ከርቀት አክርሮ የመታትን እና ግብ ጠባቂው እንደምንም ያወጣት የመከላከያ ጠንካራ የአጋማሹ ሙከራ ነበረች፡፡
ከእረፍት መልስ ሁለቱም ክለቦች በመጀመሪያው አጋማሽ ካሳዩት እንቅስቃሴ ለወጥ ባለ መልኩ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ቀርበዋል፡፡ በተለይ ሜዳው ኳስን እየነዱ ለመጫወት ምቹ ካለመሆኑ የተነሳ ቀዳዳን እየፈለጉ ከርቀት የሙከራ ዕድሎችን ለመፍጠር ተገደዋል፡፡ ከዚህም ተደጋጋሚ መከራዎች በኃላ የመጀመሪያዋን ግብ 81ኛው ደቂቃ ላይ ተመልክተናል። የመከላከያ ተከላካዮች የአቋቋም ስህተት የተመለከተው ካሜሩናዊው አማካይ ሮጀር መሀል ለመሀል በአየር ላይ ያሻገረለትን ኳስ ሌላኛው ካሜሩናዊ አጥቂ ጆን ማሉማ ወደ ግብነት ለውጧት በርበሬዎቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ቡድኑ ግን መሪ መሆን የቻለው አስራ አንድ ደቂቃን ብቻ ነው 90+1 ላይ ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ በሙሉ ኃይላቸው ነቅለው መጫወት የቻሉት መከላከያዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ አናጋው ባደግ በቀኝ በኩል በረጅሙ ሲያሻግር መከላከያዎቹ እንደሰሩት የተከላካይ ስህተት ሁሉ ሀላባዎች በሰሩት ስህተት ተከላካዩ አበበ ጥላሁን ከመሀል ዘሎ በመነሳት በግንባር ገጭቶ በጭማሪ ሰአት መከላከያን 1ለ1 ያደረገ ሲሆን ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተገናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በእለቱ ዳኛ ላይ የሀላባ ደጋፊዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ምድብ ሐ
ኦሜድላ ሜዳ ላይ የካ ክፍለ ከተማ ከመድን ያደረጉት ጨዋታ በየካ 1’0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ እንዳለማው ጋንተሪ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል።
አርሲ ነገሌ ላይ ቂርቆስን የገመው ነገሌ አርሲ በአብዱላዚዝ አህመድ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል።
©ሶከር ኢትዮጵያ