በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ከተመሳሳይ የሽንፈት ጉዞ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ድል አድራጊነት የተሸጋገረው ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታን በተከታዩ ዳሰሳ ተመልክተናል።
ባሳለፍነው ሁለት የጨዋታ ሳምንቶች ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ተስፋ ሰጪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውን በውጤት ማጀብ ተስኗቸው በባህርዳር ከተማና ፋሲል ከነማ ሽንፈትን ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ የቀደመው ሞገሱ እየከዳው የሚገኘውን ሲዳማ ቡና የሚገጥም ይሆናል።
የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | አቻ | አሸነፈ |
ኢትዮጵያ ቡና በተለይ የመጨረሻ ሁለት በሜዳቸው ያደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ በድምሩ 9 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። ይህም በእስካሁን የሊጉ ጉዞ በርካታ ጥያቄዎች በሚነሱበትና 12 ግቦችን ላስተናገደው የሲዳማ ቡና የተከላካይ ክፍል ከፍተኛ የራስ ምታትን የሚፈጥር ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደ ወትሮው ሁሉ ዘንድሮ በአሰልጣኝ ካሣዬ እየተገነባ የሚገኘው በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት በዚህኛው ጨዋታ ላይ የሚጠበቅ ሲሆን ከሌላው ጊዜ በተለየ ግን በማጥቃት ሂደት ወቅት ለሚከፋፈቱ ቦታዎች ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ተቆጣጥረው ከራሳቸው ሜዳ ጀምረው በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተቃራኒ የሜዳ አጋማሽ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት ወቅት በተለይ የቅብብል ስህተቶችን የሚሰሩ ከሆነ ፈጣን በሆኑት አዲስ፣ ሀብታሙና ይገዙ የተገነባው የሲዳማ ቡና የአጥቂ መስመር የሚምራቸው አይመስልም።
ቡናማዎቹ አቡበከር ናስርን በጉዳት፣ አቤል ከበደን በቅጣት የማያሰልፉ ሲሆን ታፈሰ ሰለሞን ከጉዳቱ ማገገሙ ተነግሯል።
የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
ከተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት በመመለስ የተነቃቃው ሲዳማ ቡና ወደ ተፎካካሪነት ለመመለስ ማሸነፍን አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።
ከፋሲል ከተማ (17) ቀጥሎ በርካታ ግቦችን (15) ያስቆጠሩት ሦስቱ የሲዳማ ቡና ፈጣን አጥቂዎች በተለይ ፈጠን ባሉ ሽግግሮች የተጋጣሚን ቡድን በመቅጣት የተዋጣላቸው ናቸው። በዚህኛው ጨዋታ ላይም በተለይ ኳስ ተቆጣጥሮ የሚጫወተው ቡናን እንደመግጠሙ ፈጣን መልሶ ማጥቃት አዋጪ እንደሚሆንላቸው ይገመታል።
በበርካታ ጨዋታዎች ላይ በአደገኛ የጨዋታ ቅፅበት ውስጥ ኳስ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ መስርቶ ለመውጣት ጥረት የሚያደርገው የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ አማካይ ዓለምአንተ ካሳ ላይ ጫና በማሳደር ስህተቶችን እንዲሰራ የሚያስገድዱት ከሆነም ያላቸውን የአጥቂዎች አቅም በስፋት መጠቀም የሚችሉበት እድል እንደሚኖር ይጠበቃል።
በሲዳማ ቡናዎች በኩል ከጉዳት የተመለሰው የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዮናታን ፍሰሃ ከጉዳት መልስ ከስብስቡ ጋር ወደ አዲስአበባ ሲያቀና ሚለዮን ሰለሞን፣ ሙሉቀን ታሪኩ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም እና አዲሱ አቱላ አሁንም በጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
እርስ በርስ ግንኙነት
እስካሁን በሊጉ ለ20 ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 8 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
– በ20 ግንኙነቶች 47 ጎሎች ሲቆጠሩ ሲዳማ ቡና 24፣ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 23 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
በረከት አማረ
አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ- አስራት ቱንጆ
ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – ዓለምአንተ ካሣ – አማኑኤል ዮሐንስ
ሚኪያስ መኮንን – ሀብታሙ ታደሰ – እንዳለ ደባልቄ
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
ፍቅሩ ወዴሳ
አማኑኤል እንዳለ – ሰንደይ ሙቱኩ – ግርማ በቀለ- ተስፉ ኤልያስ
ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሐንስ – አበባየሁ ዮሐንስ
አዲስ ግደይ – ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
© ሶከር ኢትዮጵያ