የፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

👉 ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአምስተኛ ሳምንት በአጠቃላይ 25 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም የዘንድሮው ሊግ ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው።

– በዚህ ሳምንት በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ጎሎች ተቆጥረዋል። (ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ነው)

-በዚሀ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥር የወጣው ቡድን 1 ብቻ (ፋሲል ከነማ) ሲሆን ይህም ሊጉ ከተጀመረ ወዲህ ዝቅተኛው ነው።

– በዚህ ሳምንት 22 ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር ተሳትፈዋል። በዘንድሮው ሊግ ካለፈው ሳምንት ጋር በጋራ ከፍተኛው የጎል አስቆጣሪዎች ቁጥር ነው።

– ከተቆጠሩት 25 ጎሎች መካከል 17 ጎሎች በአጥቂ (የመሐል እና የመስመር) ተጫዋቾች ሲቆጠሩ 7 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተቆጥሯል። 1 ጎሎች ደግሞ በተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች (በራስ ላይ) ተቆጥሯል።

– ብሩክ በየነ፣ ኦኪኪ አፎላቢ እና ግርማ ዲሳሳ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከፍተኛውን የጎል ቁጥር ሲያስመዘግቡ ቀሪዎቹ 19 ተጫዋቾች አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ከ25 ጎሎች መካከል 19 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ 1 ጎል ከፍፁም ቅጣት ምት፣ 5 ጎል ደግሞ ከቅጣት ምት እና ማዕዘን ምት ተሻምተው የተገኙ ናቸው።

– ከዚህ ሳምንት 25 ጎሎች መካከል 19 በእግር ተመትተው ሲቆጠሩ 6 ጎሎች በግንባር ተገጭተው ተቆጥረዋል።

– ከ25 ጎሎች መካከል 20 ጎሎች ከሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 5 ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ጎል ሆነዋል።

– በዚህ ሳምንት ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥተው አንድ (እንዳለ ደባልቄ) ወደ ጎልነት ሲቀይር አንድ (አማኑኤል ገብረሚካኤል) አምክኗል።


👉 ካርዶች

– በዚህ ሳምንት 30 የማስጠንቀቂያ (ቢጫ) እና 0 ቀይ ካርዶች ተመዘዋል።

– ወልቂጤ ከተማ ምንም ማስጠንቀቂያ ካርድ ያልተመለከተ ቡድን ሲሆን መቐለ፣ ወልዋሎ፣ ሀዋሳ፣ ድቻ፣ እና ሲዳማ ቡና (3) በርካታ ማስጠንቀቂያ ካርዶች የተመለከቱ ቡድኖች ሆነዋል።

👉 የሀዲያ ሆሳዕና አንድ ነጥብ

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የዓመቱን የመጀመርያ የሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ድል ያሳኩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዚህ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ የራሳቸውን ታሪክ አድሰዋል። ቡድኑ በ2008 በአጠቃላይ በ26 ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን ብቻ አስመዝግቦ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ የሚታወስ ሲሆን ዘንድሮ ገና በ9ኛ ሳምንት 9 ነጥቦችን በማሳካት የቀደመ ታሪካቸውን አድሰዋል።

👉 ግርማ ዲሳሳ እና ብሩክ በየነ

ሁለቱ ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት ደምቀው ውለዋል። ተጫዋቾቹ ቡድኖቻቸው ድል እንዲያደርጉ የረዷቸው ሁሉም ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ችለዋል። ሁለት በማስቆጠር እና አንድ በማመቻቸት…

👉 የስሑል ሽረ ወቅታዊ ድንቅ አቋም

በአስደናቂ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙት ስሑል ሽረዎች ለተከታታይ ሦስተኛ ጨዋታ ድል አስመዝግበዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተከታታይ ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ወደ ስድስት ከፍ ሲያደርጉ በተከታታይ አራት ጨዋታዎች መረባቸውን ባለማስደፈር ምርጥ የኋላ መስመር እንዳላቸው አሳይተዋል።

👉 የመቐለ 70 እንደርታ ስኬታማ ጉዞ

የዐምናው ቻምፒዮን በድንቅ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኝ ሌላው ቡድን ነው። ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በማስመዝገብ መሪነቱን አጠናክሯል። ቡድኑ ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም (9) ጨዋታዎች ላይ ጎል አስቆጥሮ የወጣ ብቸኛው ቡድን ነው።

👉 የወላይታ ድቻ የሜዳ ውጪ ድል

ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር የተለያየው ወላይታ ድቻ በጊዜያዊ አሰልጣኙ ደለለኝ ደቻሳ እየተመራ ከሜዳው ውጪ ጅማ አባ ጅፋርን 2-1 አሸንፏል። ይህ ድል ለቡድኑ የዓመቱ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል ሆኖ ሲመዘገብ ከ7 ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ የተገኘ ሦስት ነጥብ ሆኗል። 

ወላይታ ድቻ በአጠቃላይ በፕሪምየር ሊጉ ከሜዳው ውጪ ድል አስመዝግቦ ሲመለስ ከ17 ጨዋታዎች በኋላ የመጀመርያው ሆኗል። (ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በፎርፌ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ሳይጨምር)


👉 በዚህ ሳምንት…

– በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ላይ ኳስና መረብን አገናኝቶ የነበረው ሙጂብ ቃሲም በዚህ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥር ወጥቷል።

– ባህር ዳር ከተማ ለአራተኛ ተከታታይ ጨዋታ በሜዳው ሦስት እና ከዚያ በላይ ጎል እያስቆጠረ ማሸነፉን ሲቀጥል በተቃራኒው ለስምንተኛ ተከታታይ ጨዋታ መረቡን አስደፍሮ ወጥቷል።

– የ2010 የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ኦኪኪ አፎላቢ በዓመቱ የመጀመርያ ጎሉን አስቆጥሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በሶከር ኢትዮጵያ የሚወጡትን ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች በቀጥታም ሆነ በግብዓትነት ሲጠቀሙ ምንጭ ይጥቀሱ።