የ2008 የውድድር ዘመንን በድንቅ አቋም ለጀመረው አዳማ ከተማ ተጠቃሽ የሆኑት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለክለቡ ያቀረቡት ጥያቄ እልባት ሊያገኝ ባለመቻሉ ከስራ ገበታቸው ቀርተው የነበረ ቢሆንም ክለቡ ጥያቄያቸውን እንደሚያሟላ ዋስትና በመስጠቱ ዛሬ ወደ አሰልጣኝነታቸው እንደሚመለሱ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ክለቡን ከተረከብኩበት 2006 ጀምሮ ጥቂት ደጋፊዎች ገንዘብ እንድሰጣቸው በማስፈራራት ሲጠይቁኝ ከርመዋል፡፡ ከ4 የማይበልጡ ደጋፊዎች የልምምድ ቦታ እየመጡ እና ከጨዋታ በኋላ በስልክ ጭምር በተደጋጋሚ አስቸግረውኛል፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩ አሰልጣኞችንም በተመሳሳይ ገንዘብ ለመቀበል እንደሚያስፈራሩ መረጃው አለኝ፡፡ ይህንን ደግሞ ለሚመለከተው አካል ሁሉ አሳውቄያለሁ፡፡ በተደጋጋሚ ያናግሯቸዋል ነገር ግን መፍትሄ የለም፡፡ ይህ ሁኔታ ለራሴ እና ቤተሰቦቼ ደህንነት አስጊ በመሆኑ ጥር 28 ቀን 2008 ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጭምርሁኔታውን የሚገልፅ ደብዳቤ አስገብቻለሁ፡፡ ትላንት ደግሞ ለክለቡ የመልቀቅያ ደብዳቤ ለማስገባት ተገድጃለሁ፡፡ ይህንን ለሚድያ ይፋ ያደረግሁት ጉዳዩ ከአቅሜ በላይ ስለሆነብኝ እና የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች እውነታውን እንዲረዱት ነው፡፡ ›› ሲሉ በምሬት የሚናገሩት አሰልጣኝ አሸናፊ ከጥቂት ደጋፊዎች ውጪ በአዳማ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ ከጥቂት ደጋፊዎች ውጪ ከሌሎቹ ደጋፊዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ጤናማ ነው፡፡ ክለቡ እውቅና የሰጠው የደጋፊ ማህበርም ለስራዬ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገልኝ ነው፡፡ ከከተማው አስተዳደር እና የክልሉ መንግስት ጭምር ድጋፍ እየተደረገልን ነው፡፡››
አሰልጣኝ አሸናፊ ለፌዴሬሽን ደብዳቤ ካስገቡ በኋላ ክለቡ ከድሬዳዋ ከተማ እና ኤሌክትሪክ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች የመሩ ቢሆንም ያለፉትን 2 ቀናት በስራ ገበታቸው ላይ አልተገኙም፡፡ ክለቡም ከውጤታማው አሰልጣኝ ጋር ባደረጉት ውይይት ለደህንነታቸው ዋስትና በመስጠታቸው ወደ ስራ እንደሚመለሱ አሰልጣኝ አሸናፊ ይናገራሉ፡፡
ከስራ መልቀቂያው በኋላ ከክለቡ ፣ ከከተማው ከንቲባ እና ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ተነጋገሬ መፍትሄ ላይ በመድረሳችንና ለደህንነቴ ማረጋገጫ በማግኘቴ ከዛሬ ከሰአት ጀምሮ ወደ ስራ ገበታዬ እመለሳለሁ፡፡ በመጪው ቅዳሜ ክለባችን ከሃድያ ሆሳዕና ሲጫወትም ቡድኔን እመራለሁ፡፡ ›› ብለዋል፡፡
አዳማ ከተማ በ2005 ባስመዘገበው ደካማ ውጤት ወደ ብሄራዊ ሊግ መውረዱን ተከትሎ በፍጥነት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመመለስ እንዲረዱት የሾማቸው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማሳደግ የቻሉ ሲሆን ባለፈው የውድድር ዘመን አዳማ ባልተጠበቀ ሁኔታ 3ኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ድንቅ አጀማመር አድርገው ከ9 ሳምንታት በኋላ 2ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርገውታል፡፡