በአስራ ሦስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብቸኛ የዛሬ ጨዋታ ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን አስተናግዶ 3-2 ረቷል፡፡
ሲዳማ ቡና በቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ሳምንት ሲረታ ከተጠቀመበት ስብስብ አዲስ ግደይ፣ ዮናታን ፍሰሀ፣ ጊት ጋትኮች እና ግሩም አሰፋን በማስወጣት በአማኑኤል እንዳለ፣ ትርታዬ ደመቀ፣ ብርሀኑ አሻሞ እና ክፍሌ ኪአ ሲተኩ አዳማዎች በበኩላቸው ሱሌይማን መሐመድን በምኞት ደበበ፣ ከነዓን ማርክነህን በአዲስ ህንፃ፣ ዳዋ ሆቴሳን በሚካኤል ጆርጅ ለውጠው ጀምረዋል፡፡
ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዳማ ከተማ በተወሰነ መልኩ ከባለሜዳው ተሽሎ ቀርቧል፡፡ በተለይ በረከት ደስታ በመስመር በኩል በግል ጥረቱ የሚያደርጋቸው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ትኩረት የሚስቡ ሲሆኑ ሲዳማ ቡናዎች በተቃራኒው ረጃጅም ኳስ ላይ አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች አሳልፈዋል፡፡ አዲስ ግደይን በገጠመው መጠነኛ ጉዳት ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጠው የጀመሩት ሲዳማዎች በተወሰነ መልኩ የሱን ያለመኖር ተከትሎ ሲያደርጉት የነበረው የማጥቃት ሂደት በመቀዛቀዙ ይገዙ ቦጋለን ከተለመደው ባህሪው ውጪ እንዲንቀሳቀስ አስገድደውታል፡፡
በግብ ሙከራ ረገድ ተመሳሳይ መንገዶችን በመከተል ሁለቱም ቡድኖች ለመረበሽ ቢጥሩም ቀዳሚዎች ባለሜዳዎቹ ነበሩ፡፡ አበባየው ዮሐንስ በክፍት አጋጣሚ የሰጠውን አማኑኤል እንዳለ ለመምታት ሲጣጣር በተከላካዮች የተመለሰበት ቀዳሚው ነበር፡፡ ከዚህች ሙከራ በኋላ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አዳማ ከተማ ድንቅ በነበረው ቡልቻ ሹራ ታግዞ በርካታ ዕድሎችን አግኝቷል፡፡ በረከት በረጅሙ ሲጥል ቡልቻ ፊት ለፊት አግኝቶ መረጋጋት ተስኖት ወደ ላይ የሰደዳት ኳስም አስቆጪ ዕድል ነበረች፡፡
ከወትሮው በተለየ ረጃጅም ኳስ ለመጠቀም የተገደዱት ሲዳማዎች በተወሰነ መልኩ በአዳማ ቢበለጡም መሪ የሚሆኑበትን ግብ አግኝተዋል፡፡ 18ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት አበባየው ዮሀንስ በረጆሙ ወደ ግብ ሲያሻማ አዲስ ግደይን ተክቶ ከፊት የተሰለፈው አማኑኤል እንዳለ ከመሀል ዘሎ ተነስቶ በግንባር ገጭቶ ግብ ጠባቂው ደረጀ ዓለሙን አቅጣጫ በማሳት አስቆጥሮ ባለሜዳውን መሪ አድርጓል፡፡
ሆኖም ግብ ካስቆጠሩ በኃላ መረጋጋት ያልቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ገና ያስቆጠሩት ግብ ደስታ ሳይረግብ ግብ አስተናግደዋል፡፡ 20ኛው ደቂቃ በመስመር በኩል በፍጥነት ወደ ሲዳማ ግብ ክልል ከደረሱ በኃላ በግራ በኩል ሱለይማን ሰሚድ በረጅሙ ሲያሻማ የሲዳማ ተከላካዮችን መዘንጋት ተከትሎ በጨዋታው ድንቅ አቋሙን ሲያሳይ የነበረው ቡልቻ ሹራ በግንባር በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል፡፡
ልክ ሲዳማ ግብ ካገቡ በኃላ መረጋጋት እንዳልቻሉት ሁሉ አዳማዎች ካገቡ በኋላ ለመረጋጋት በመቸገራቸው ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ 23ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ በረጅሙ በግራ በኩል ለሀብታሙ ገዛኸኝ ያመቻቸለትን ኳስ ሀብታሙ በፍጥነት ለዳዊት ተፈራ ሰጥቶት ዳዊት ከሳጥን ውጪ ቀለል አድርጎ መትቶ በማስቆጠር ሲዳማን ወደ መሪነት አሸጋግሯል፡፡
አዳማ ከተማዎች መረባቸው ከተደፈረባቸው በኃላ በቡልቻ ሹራ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ቢያደርጉም ከግብ ለመገናኘት ተቸግረዋል፡፡ 44ኛው ደቂቃ ግን ዳግም ሲዳማዎች ተጨማሪ ግብ አግብተዋል፡፡ ዳዊት ተፈራ በአዳማ ተከላካዮች መሀል ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ በድንቅ አጨራረስ ከመረብ አሳርፎ ሲዳማን ወደ 3ለ1 አሸጋግሯል፡፡ ሆኖም ወደ መልበሻ ቤት በዚሁ አመሩ ሲባል ከማዕዘን የተሻማውን ቴዎድሮስ በቀለ በቀላሉ አስቆጥሮ የግብ መጠኑን አጥቦ ለዕረፍት ወጥተዋል፡፡
የዳኞች ውሳኔ እና ቅሬታ ጎልቶ በታየበት እንዲሁም አዳማ ከተማዎች ተሽለው በቀረቡበት ሁለተኛው አጋማሽ እንግዳው ቡድን የታየበትን የተከላካይ ክፍል ምኞት ደበበን ለውጦ በማስገባት ለማረጋጋት የጣረበት ሲሆን ሲዳማ ቡናዎች ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው አዲስ ግደይን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ኳስን በብስለት ለመጫወት የሞከሩበት ሒደት ታይቷል፡፡ መልሶ ማጥቃት ላይ ጥሩ የነበሩት አዳማዎች በተለይ በግራ እና ቀኝ በተሰለፉት ፉአድ እና በረከት መልካም እንቅስቃሴዎች በማድረግ አቻ ለመሆን ቢጥሩም የኳሱ የመጨረሻ ማረፊያ ግን ስኬታማ አልነበረም፡፡
65ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን መንፈስ የቀየረ ክስተት ተስተናግዷል። ከዳዊት ተፈራ በረጅሙ የተሻገረን ኳስ አዲስ ግደይ ከምኞት ደበበ ጋር ተጋፍቶ ከነጠቀ በኋላ ወደ ግብ በማምራት ኳሷን ከመረብ አሳርፎ የመሀል ዳኛው አክሊሉ ድጋፌ እና ረዳቶቻቸው ግቧን ቢያፀድቋትም አራተኛ ዳኛው እያሱ ፈንቴ አዲስ ግደይ በእጅ እንደነካ እና ግብ እንዳልሆነች ለመሐል ዳኛው የመግለፃቸው ኳሷ ተሽራለች። የሲዳማ ቡና ደጋፊዎችም በእያሱ ፈንቴ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን በዚህም ምክንያት ጨዋታው ለአስራ ሦስት ደቂቃዎች ተቋርጧል፡፡
በዚህ መቋረጥ መሐል አዳማዎች አልገባም፤ ሲዳማዎች ገብቷል በሚል ከተጠባባቂ አንስቶ ሜዳ ውስጥ ባሉ ተጫዋቾችም ጭምር ያልተገባ ሰጣ ገባ ውስጥ የገቡ ሲሆን ጨዋታው ከተቋረጠበት ዳግም ጀምሮ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች አዳማዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የሰነዘሩ ቢሆንም በርካታ አጋጣሚን አግኝተው ወደ ግብነት ሳይለውጡ ቀርተዋል፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ሲዳማዎች ጨዋታውን አስቁመው ክስ በአምበላቸው አዲስ ግደይ አማካኝነት ያስያዙ ሲሆን ጨዋታውም በሲዳማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም የተጨመረው ደቂቃ በአግባቡ ሳይጠናቀቅ ፊሽካ ተሰምቷል በሚል የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተስተውሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ