ጌታነህ እና ኡመድ በዚህ ሳምንት. . . 

 

ጌታነህ ለፕሪቶርያ 90 ደቂቃ ተጫውቷል

በደቡብ አፍሪካ በመጫወት ላይ የሚገኘው የፊት መስመር ተሰላፊው ጌታነህ ከበደ ክለቡ የፕሪቶሪያ ዪኒቨርስቲ በሱፐር ስፖርት ዩናይትድ 2-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት ችሏል፡፡ የፕሪቶሪያው ክለብ ወራጅ ቀጠናው ላይ ለመቆየት በተገደደበት ጨዋታ ለሱፐር ስፖርት ግቦቹን ሲቡሲሶ ኩማሎ እና ቱሶ ፓላ አስቆጥረዋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ በ13 ነጥብ 15ኛ ተቀምጧል፡፡ ሊጉን በሳምንቱ መጨረሻ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ በዚምባቡዌው ቺክን ኢን የ1-0 አስደንጋጭ ሽንፈት የደረሰበት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ሲመራ የኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን ዛማቢያዊው ኮሊንስ ምቤዙማ በ11 ግቦች ይመራል፡፡ ምቤዙማ በ2013 ደቡብ አፍሪካ ላይ ተደርጎ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከ ዛምቢያ 1-1 ስትለያይ ዋሊያዎቹ ላይ ግብ አስቆጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

 

ኡመድ አሁንም ለኢኤንፒፒአይ መጫወት አልቻለም

የኡመድ ኡኩሪ ክለብ የሆነው ኢኤንፒፒአይ ወራጅ ቀጠና በሚገኘው ኢቲሃድ ኤል ሾርታ የ3-1 አስደንጋጭ ሽንፈት ደርሶበታል፡፡ ኡመድ በጨዋታው ላይ ከኢኤንፒፒአይ ቡድን ውጪ በመሆኑ ሳይሰለፍ ቀርቷል፡፡ ኢኤንፒፒአይን በፈቃዳቸው ለቀው ኤል ሾርታን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት ሃኒ ራምዚ ጣፋጭ የሆነ ድል የቀድሞ ክለባቸው ላይ ተቀዳጅተዋል፡፡ ለኤል ሾርታ ግቦቹን ሆሳም አብደላል፣ መሃመድ ባስኦኒ እና ሳላ ሪኮ አቲፍ (በራሱ ግብ ላይ) አስቆጥረዋል፡፡ ሳላ አሹር ለኢኤንፒፒአይ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ የግብፅ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዠ አል አሃሊ በ39 ነጥብ ሲመራ ዛማሌክ በ32 ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡ ምስር አል ማቃሳ እና አል መስሪ በዕኩል 31 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 3ኛ እና 4ኛ ናቸው፡፡ ፔትሮጀት በ30 ነጥብ ስድስተኛ ነው፡፡ አንድ ቀሪ ጨዋታ የሚቀረው ኢኤንፒፒአይ በ25 ነጥብ አስረኛ ነው፡፡ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ናይጄሪያዊው የዋዲ ደግላ አጥቂ ስታንሊ ኦዉቺ በ11 ግብ ይመራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *