የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ | ስሑል ሽረ

የመጀመርያው ዙር መጠናቀቁን ተከትሎ የፕሪምየር ሊጉን ክለቦች የመጀመርያ ዙር ጉዞ ዳሰሳ ቀጥለን በ21 ነጥብ በስምንተኛ ደረጃ ዙሩን ያጠናቀቀው ስሑል ሽረን ጉዞ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።


የመጀመርያ ዙር ጉዞ

በሊጉ ጅማሬ ላይ ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው የኋላ የኋላ መሻሻሎች አሳይተው ከወራጅ ቀጠናው ወጥተው ወደ ሰንጠረዡ አናት የመጡት ስሑል ሽረዎች በመጀመርያው ዙር ጥሩ መሻሻሎች ካሳዩ ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ። በብዙ የሜዳ ውጭ ችግሮች ተወጥረው ዓመቱን የጀመሩት ሽረዎች በመጀመርያው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳቸው አሸንፈው ቢጀምሩም በወልዋሎ እና ሲዳማ ቡና በተከታታይ በሰፊ የጎል ልዩነት ተሸንፈው ውጥረት ውስጥ ገብተው ነበር። በሦስቱም ሳምንታት ደካማ የተከላካይ ክፍል የነበራቸው ሽረዎች በአራተኛው ሳምንት ከሜዳቸው ውጭ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተው ከተመለሱ በኋላ በሜዳቸው በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደው ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ከሜዳቸው ውጭም ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ተለያይተው በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ በማገገም ሰበታ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ (ከሜዳቸው ውጭ) እና ፋሲል ከነማን በማሸነፍ የሚታይ ለውጥ ያሳየው ቡድኑ በአስረኛው ሳምንት ከጅማ አባጅፋር ጋር ነጥብ ቢጋራም በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል።

በአስራ አንደኛው ሳምንት መቐለ 70 እንርደታን ገጥመው ከከፍተኛ ተጋድሎ በኋላ ሽንፈት ያስተናገዱት ሽረዎች በቀጣዩ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን በሰፊ ልዩነት አሸንፈው ወደ ድል መንገድ ቢመለሱም በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት ወሳኝ ነጥቦች ጥለው ደረጃቸው የማሻሻል ዕድል አምክነዋል። በዚህም ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ጎል ነጥብ ተጋርቶ በባህርዳር ከተማ ሽንፈት አስተግዶ ዙሩን በሀያ አንድ ነጥብ በስምንተኝነት አጠናቋል።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

በመጀመርያ የውድድር ዘመን አጋማሽ የውጤት ንፅፅር የስሑል ሽረን ያህል የተሻሻለ ቡድን አልነበረም ለማለት ያስደፍራል። ዓምና በዚህ ሰዓት በ15 ጨዋታ አንድ ድል ብቻ በማሳካት 11 ነጥቦች ሰብስቦ 15ኛ የተቀመጠው ቡድን ዘንድሮ በእጅጉ ተሻሽሎ በ10 የበለጡ ነጥቦች በመሰብሰብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተጨማሪም ከዐምናው በ7 የበለጡ ጎሎች አስቆጥሮ በ9 ያነሱ ጎሎች ተቆጥረውበታል።

የቡድኑ አቀራረብ

በአንዳንድ ጨዋታዎች ካደረጓቸው መጠነኛ የቅርፅ ለውጥ በስተቀር አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በሁሉም ጨዋታዎች የ4-2-3-1 አደራደር ምርጫቸው ነበር። በሊጉ መጀመርያ አካባቢ በቅጡ የማይከላከል እና የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት ለመመከት የሚቸገር ቡድን የነበረው ስሑል ሽረ በወልዋሎ ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ በርካታ ለውጦች አድርጎ ነበር የተመለሰው።

በዙሩ የተለያዩ ሁለት አቀራረቦች የነበራቸው ስሑል ሽረዎች ከአራተኛው ሳምንት በኋላ በሜዳቸው አስፈሪ የመልሶ ማጥቃት አቀራረብ ከሜዳቸው ውጭም ጠጣር እና ከግብ ክልሉ እምብዛም የማይንቀሳቀስ አቀራረብ ነበራቸው። በሁለቱም መስመሮች ተለጥጠው ከመስመር በሚነሱት ዓብዱለጢፍ መሐመድ እና ዲድዬ ለብሪ መሰረት ያደረገ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ሽረዎች በአጨዋወቱ አተገባበር ላይ የነበራቸው ውጤታማነት ለማሻሻላቸው ትልቅ አስተዋፀኦ አድርጓል።

በጨዋታዎች በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገሩት ስሑል ሽረዎች በሊጉ ክለቦች ተገማች እስከሆኑበት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ድረስ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው በውጤታማነት ረገድ በትልቅ ደረጃ የሚነሳ ነው።

በመጀመርያው ሳምንታት በርካታ ተጫዋቾች እያቀያየሩ የተጠቀሙት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ ምንተስኖት አሎ ቀዳሚ ምርጫቸው ሲሆን ለሙከራ ወደ ቱርክ ባመራበት እና በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ጥቂት ጨዋታዎች ወንድወሰን አሸናፊ ተክቶት ተጫውቷል። ቀስ በቀስ ወደ ቀደመ አቋሙ የተመለሰው ምንተስኖት በተለይ ወደ ቱርክ ከማምራቱ በፊት በነበሩ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ጎሉን ባለማስደፈር ጥሩ ጊዜ አሳልፏል።

ቡድኑ ወደ ጥሩ ብቃት ከመጣ በኋላ በተከላካይ መስመር ዮናስ ግርማይ እና አዳም ማሳላቺ የመሐል ተከላካይ ጥምረቱን ሲመሩ ዓወት ገብረሚካኤል እና ረመዳን የሱፍ በሁለቱ መስመሮች ተሰልፈዋል። የቡድኑ ጠንካራ ጎን የሆነው የተከላካይ መስመር በተጠቀሱት ተጫዋቾች ጥምረት ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ያስተናገደው የጎል መጠንም ጥቂት ነው።

በአማካይ መስመር ላይ ወጣቱ ነፃነት ገብረመድኅን ቦታውን ሲያስከብር ከጎኑ በአመዛኙ ሀብታሙ ሸዋለም ተሰልፏል። ነፃነት በመከላከሉ፤ ሀብታሙ ደግሞ በኳስ ስርጭቱ የቡድኑን ሚዛናዊነት በመጠበቅ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ሲሆን ከፊታቸው የሚገኙት የማጥቃት ተጫዋቾች ፈጣን መልሶ ማጥቃት እንዲፈፅሙ ጥሩ አበርክቶ አላቸው። ከሁለቱ አማካዮች ፊት ዲዲዬ ሌብሪ እና ዓብዱለጢፍ መሐመድ ከያስር ሙገርዋ ቀኝ እና ግራ ሲጣመሩ የቡድኑ ዋንኛ መለያ የሆነው የመልሶ ማጥቃት ዋንኛ መሳርያም ናቸው። ቡድኑን ለቆ ወደ ሆሳዕና ያመራው ሳሊፍ ፎፋና ደግሞ በብቸኛ አጥቂነት ከፊት ተሰልፎ አጋማሹን አገባዷል።

ጠንካራ ጎን

ሽረዎች የመስመር እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ጠንካራ ጎናቸው ነው። በዋነኝነት በዓብዱለጢፍ መሐመድ እና በዲዲዬ ሌብሪ የተመሰረተው የመልሶ ማጥቃታቸው በተለይም ቆይቶ ወደ መጀመርያ አሰላለፉ የመጣው ዐወት ገ/ሚካኤል እና በማጥቃት ላይ ባለው ጥሩ ድርሻ የሚታወቀው ረመዳን የሱፍ ጥሩ ብቃት ተደምሮበት የቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አስፈሪ እንዲሆን አድርጎታል። በዙሩ ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት ከነበራቸው ቡድኖች በግንባር ቀደምት የሚጠቀሱት ሽረዎች በቡድናቸው ውስጥ የነበረው ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ችግር በቶሎ ቢፈቱ ኖሮ አሁን ካሉበት ደረጃ የተሻለ ቦታ ይገኙ ነበር።

የመከላከል አደረጃጀት ሌላው የስሑል ሽረ ጠንካራ ጎን ነው። በስምንት ጨዋታ ጎሉን ሳያስደፍር የወጣው ቡድኑ እንደ ቡድን የሚከላከልና በተለይ ከሜዳ ውጪ ሲጫወት ለተጋጣሚ በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ ሲሆን አሁን ያለው ጥምረት በሒደት ውህደት እያሳየ የመጣ ከመሆኑ አንፃር በቀጣይም እየጠነከረ እንደሚሄድ ይገመታል።

ደካማ ጎን

ዙሩን በስምንተኛ ደረጃ ያጠናቀቁት ስሑል ሽረዎች የመጀመርያው ዙር ደካማ ጎናቸው ደካማው የአጥቂ ክፍላቸው እና ተመሳሳይ በመሆኑ ምክንያት የኋላ ኋላ ተገማች የሆነው አቀራረባቸው ነው። በጨዋታዎች በቁጥር በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች የሚፈጥሩት ሽረዎች ዕድሉን በአግባቡ የሚጠቀም ጨራሽ አጥቂ በቡድናቸው ውስጥ ቢኖር ያስቆጠሩት የግብ መጠን በእጅጉ ይጨምር ነበር።

እንደሚፈጥሩት ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ስር የሰደደ ክፍተት ያላቸው ሽረዎች ከሳሊፍ ፎፋና በተጨማሪ ሌላ ጥሩ አማራጭ የሚፈጥር አጥቂ አለመያዛቸው ችግሩ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል። በሊጉ መጀመርያ አከባቢ የነበረው ደካማ የተከላካይ ክፍላቸው ያሻሻሉት ሽረዎች ተገማቹ አጨዋወታቸው ሌላው የሚጠቀስ ደካማ ጎን ነው። ከመልሶ ማጥቃት በተጨማሪ ሌላ አቀራረብ ለመተግበር ያልደፈሩት ሽረዎች በተለይም በዙሩ የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በተገማችነታቸው ነጥቦች ጥለዋል። ቡድኑ እንደ ሙሉዓለም ረጋሳ ፣ ኃይለአብ ኃይለሥላሴ እና ያሳር ሙገርዋ የመሳሰሉ የፈጠራ አቅም ያላቸው አማካዮች እያሉት ሁለተኛ አቀራረቡ (plan B ) በአማካዮቹ ዙርያ አለመስራቱም አስገራሚ ነው።

የዲሲፕሊን ሪከርዱ ሌላው የቡድኑ ድክመት ነው። ከፍተኛ ካርድ ከተመዘዘባቸው ቡድኖች አንዱ የሆነው ሽረ በተጨማሪም ሦስት ቀይ ካርዶች የተመዘዘበት ሲሆን ተጫዋቾች እና ቡድን አባላት ውጥረት በሚበዛበት ሁለተኛው ዙር ተመሳሳዩን ከደገሙ ውጤት በሚያስፈልግበት ሰዓት ቡድኑን ዋጋ ሊያስከፍሉት ይችላሉ። 

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

ከሰዓታት በፊት ከዋና አሰልጣኛቸው ሳምሶን አየለ ጋር የተለያዩት ስሑል ሽረዎች ሁለተኛው ዙር ከመጀመሩ በፊት በፍጥነት ዋና አሰልጣኝ መቅጠር ቀዳሚ ስራቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ ከመጀመርያው ዙር ስብስቡ ብዙም የተለወጠ ቡድን ይኖረዋል ተብሎ ባይጠበቅም  በፍጥነት የአሰልጣኝ ቅጥር ካልፈመ ግን በቡድኑ ውህደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ክለቡ የአሰልጣኝን ቅጥር በፍጥነት ከመፈፀም በተጨማሪ በቡድኑ ያለውን የተጫዋቾች አቅም እና ስብስብ ባገናዘበ መልኩ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠርም ተጨማሪ ሥራው ይሆናል።

በመጀመርያው ዙር ከሌሎች ክለቦች በበለጠ በርካታ ተጫዋቾች አቀያይረው የተጠቀሙት ስሑል ሽረዎች በስብስባቸው በርካታ ተጫዋቾች ቢይዙም በአንደኛው እና በሁለተኛው የተጫዋቾች ምርጫቸው ያለው ሰፊ የጥራት ልዩነት በጉዟቸው እንቅፋት ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ዙር ጨዋታዎች እንደታየው ቡድኑ በቅጣት እና በጉዳት ወሳኝ ተጫዋቾቹ ካጣ በኃላ እንደተቸገረው በሁለተኛው ዙርም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥመው በቁልፍ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ተጫዋቾች ማስፈረም የግድ ይለዋል።

በአሰልጣኙ አጨዋወት ቁልፍ ቦታ የነበረው የመስመር አጨዋወትን ይበልጥ ለማጎልበት ለአጨዋወቱ የሚመቹ የመስመር ተጫዋቾች እና በሳሊፍ ፎፋና ምትክ የፊት አጥቂ ተጫዋች ማስፈረም አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ በዙሩ ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ የነበረው ቡድኑ ከተገማችነት ለመውጣት ጥሩ የሚባል ሁለተኛ የጨዋታ አቀራረብ (Plan B) ማዘጋጀት ዋነኛ የቤት ሥራው መሆን እንዳለበት ይታመናል። በተለይም ቡድኑ የመጀመርያው ዙር ከተጫወትበት በመጠን ሰፊ ከሆነው ትግራይ ስታዲየም ወደ ሽረ እንዳሥላሴ ስታድየም መዞሩን ተከትሎ በአጨዋወቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል ተብሎ ስለሚታመን ቡድኑ ሁለተኛ አማራጭ አጨዋወት የማዘጋጀቱ ጉዳይ አንገብጋቢ ያደርገዋል። በሰፊው ትግራይ ስቴየታድየም በቂ የመጫወቻ ቦታ የነበራቸው ሁለቱ ፈጣን አማካዮች በጠባቡ ሜዳ ላይ በቂ የመጫወቻ ቦታ ያገኛሉ ተብሎ ስለማይታሰብ እንደ ቀድሞው ለተጋጣሚዎች ፈተና የሚሆኑበት ዕድል የጠበበ ነው።

ሽረ በሁለተኛው ዙር ወደ ሜዳው (ሽረ እንዳሥላሴ ስታዲየም) እንደሚመለስ የሚጠበቅ መሆኑ ለቡድኑም ሆነ ለደጋፊዎቹ መልካም ዜና ነው። በሁለተኛ አማራጭ ሜዳው ጥሩ ጉዞ ያደረገው ክለቡ በደጋፊዎቹ ፊት ውጤቱን የበለጠ ሊያሳምር ይችላል።

የመጀመርያው ዙር ኮከብ ተጫዋች

ዓብዱለጢፍ መሐመድ፡ እንደ ቡድን ከሚጫወት ክለብ አንድ ተጫዋች ነጥሎ ለማውጣት የሚከብድ ቢሆንም ዓብዱለጢፍ መሐመድ የመጀመርያው ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች ነው። በመስመር በሚያደርጋቸው ፈጣን ሩጫዎች የሚታወቀው ይህ ጋናዊ ተጫዋች በቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የማይተካ ሚና አለው። በግሉ ጥረት በአንድ ጨዋታ በርካታ የግብ ዕድሎች የሚፈጥረው ይህ ተጫዋች በተለይም በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በብዙ መልክ ማሻሻያዎች አድርጎ የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል። 

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች 

ነፃነት ገብረመድኅን፡ በሊጉ ዘንድሮ ብቅ ካሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ነፃነት ገ/መድኅን በቡድኑ ብቻ ሳይሆን በሊጉ ደረጃም ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ነው። ራሱን ለማሻሻል የሚተጋው እና በልምምድ ሜዳም ታታሪ መሆኑ የሚነገለት ይህ አማካይ በተለይም በቡድኑ ተከላካይ መስመር መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለተከላካዮች በቂ ሽፋን በመስጠት ረገድ ጥሩ የሚንቀሳቀሰው ይህ ተጫዋች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እያሳየ ይገኛል።

© ሶከር ኢትዮጵያ