የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ | ወልዋሎ

የመጀመርያው ዙር መጠናቀቁን ተከትሎ የሊጉን ተሳታፊዎች በተናጠል እየዳሰስን መቆየታችን ይታወሳል። ለዛሬ ደግሞ በአስራ ስድስት ነጥብ በአስራ አምስተኛ ደረጃን ያጠናቀቀው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን እንዳስሳለን።


የመጀመርያ ዙር ጉዞ

ወልዋሎ ባለፈው ዓመት በሁለተኛው ዙር ውጤቱን አሻሽለው በጥሩ ጎዳና እንዲጓዝ የረዱት ዮሐንስ ሳሕሌን በማስቀጠል እና ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚቻል ሁኔታ በአዳዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን በማዋቀር ዓመቱን ጀምሯል።

ከሜዳቸው ውጭ ሰበታ ከተማን አሸንፈው ዓመቱን የጀመሩት ወልዋሎዎች በትግራይ ስታዲየም ባደረጓቸው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ስሑል ሽረ እና ወላይታ ድቻን በማሸነፍ ከሦስት ጨዋታ 9 ነጥብ በማግኘት ድንቅ አጀማመር ማድረግ ችለዋል። ሆኖም ከሦስቱ ሳምንታት በኃላ የተንሸራተተው ቡድኑ በቀጣይ ከጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ሀዋሳ ከተማ ትግራይ ስታዲየም ላይ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ሰብስቦ ነበር ማሽቆልቆሉን የጀመረው።

ቡድኑ በሰባተኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ከሜዳው ውጪ አሸንፎ እፎይታ ቢያገኝም በሀዲያ ሆሳዕና በሜዳው፣ በባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ተሸንፎ ከደረጃው ወርዷል። ከባህር ዳር መልስ ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ አቻ የተለያየው ቡድኑ በቀጣይ ሳምንታት በሲዳማ ቡና፣ ፋሲል ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ተከታታይ አራት ሽንፈቶች አስተናግዶ ወራጅ ቀጠናው ላይ ገብቷል። በመጨረሻው ሳምንትም ወደ ዓዲግራት ተመልሶ ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ከወልቂጤ ከተማ ጋር 3-3 አቻ ተለያይቶ ዙሩን አጠናቋል።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ዓምና በዚህ ወቅት ቢጫ ለባሾቹ 20 ነጥቦች በመሰብሰብ ከወራጅ ቀጠናው በ9 ነጥቦች ርቀው 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለው ነበር። ዘንድሮ በአንፃሩ ነጥባቸው በ4 ዝቅ ሲል በወራጅ ቀጠናም ይጠኛሉ። በጎል ረገድ ከዓምናው በ11 የሚበልጡ ጎሎች አስቆጥሮ መሻሻሉን ሲያሳይ ከዓምናው በ14 የበለጡ ጎሎችን አስተናግዶ የኋላ መስመሩ መዳከሙ ታይቷል።

የቡድኑ አቀራረብ

አመዛኙ 4-2-3-1 አደራደር ምርጫቸው የነበረው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በአንዳንድ ጨዋታዎች በሁለት አጥቂ ጥምረት ለመግባት ካደረጓቸው መጠነኛ የቅርፅ ለውጦች በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ የተጠቀሰው አደረደር መርጠው ነበር የገቡት። በመጀመርያው ዙር ለግምት አዳጋች ከነበሩት ቡድኖች የሚጠቀሱት ወልዋሎዎች በዙሩ በርካታ አቀራረቦች አቀያይረው ተጠቅመዋል። በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ጠጣር እና ለተጋጣሚ ክፍተት የማይሰጥ ቡድን የነበረው ቡድኑ ቆይቶ ግን የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት ለመመከት የሚቸገር እና በቀላሉ ግቦች የሚቆጠርበት ቡድን ሆኗል።

ካርሎስ ዳምጠው በተሰለፈባቸው የመጀመርያ ጨዋታዎች የተጫዋቹ ግዝፈት ላይ ያነጣጠሩ ረጃጅም ኳሶች መሰረት አድርገው የገቡት ቢጫ ለባሾቹ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ውጤታማ ቢሆኑም ከአምስተኛው ሳምንት በኋላ ግን በጉዳት ምክንያት እና በአጨዋወቱ አተገባበር ላይ በነበረባቸው መሰረታዊ ክፍተቶች ውጤታቸው አሽቆልቁሏል። በተጫዋቾቻቸው ተክለ ሰውነት እና በተጫቾቹ የግል አቅም አንፃር ለረጃጅም ኳስ አጨዋወት የሚሆን በቂ ግብአት ያልነበራቸው ወልዋሎዎች በዙሩ በሁሉም ጨዋታዎች በሚባል መልኩ ለአጨዋወቱ ታማኝ ነበሩ።

እንደ ሰመረ ሀፍታይ፣ ኢታሙና ኬይሙኔ እና ጁንያስ ናንጂቡ አይነት በተክለ ሰውነት ግዙፍ የማይባሉ አጥቂዎች የተጠቀሙት ወልዋሎዎች በተጠቀሱት ተጫዋቾች አጨዋወቱን ለመተግበር ያደረጉት ጥረት ከመጀመርያ ሳምንታት ውጭ ፍሬ አልባ ነበር። በጥቂት ጨዋታዎች የመስመር አጨዋወት ለመተግበር ጥረት ያደረጉት ቢጫ ለባሾቹ ለአጨዋወቱ የሚመቹ በርካታ ጨዋታዎች ቢኖራቸውም ከጥቂት ጨዋታዎች በስተቀር አጨዋወቱን ሲተገብሩ አልተስተዋሉም።

በተጫዋቾች ምርጫ ረገድ ወልዋሎ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ስር በየጨዋታዎቹ በሚለዋወጥ ሚና ተጫዋቾችን ሲጠቀሙ የተስተዋለ ሲሆን ከግብ ጠባቂዎቹ በቀር በአንድ ቦታ ላይ በወጥነት የተጫወተ ተጫዋች ለማግኘት ይቸግራል።

ጠንካራ ጎን

በዙሩ ተከታታይ የሆነ እና በየሳምንቱ ቀጣይነት ያለው ወጥ አቋም ለማሳየት ከሚቸገር ቡድን አንድ ጠንካራ ጎን ለማውጣት ከባድ ቢሆንም በቡድኑ የነበረው የማጥቃት ጥምረት በአንፃራዊነት የተሻለ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። በአመዛኙ ኢታሙና ኬሙይኔ፣ ጁንያስ ናንጂቡ እና ሰመረ ሀፍታይ የመሩት የማጥቃት ጥምረት የፈጠራ አቅሙ እጅግ የወረደ የአማካይ ጥምረት ባለው ቡድን ውስጥ ያሳዩት እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነበር። ሦስቱ ተጫዋቾች በአንዳንድ ጨዋታዎች ግቦች በማምከን ቡድኑን ዋጋ የሚያስከፍሉ የግል ስህተቶች ቢሰሩም የተፈጠረላቸው ጥቂት ንፁህ የግብ ዕድሎች እና ያስቆጠሩት የግብ መጠን ሲሰላ ግን ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል ለማለት ያስደፍራል።

ደካማ ጎን

ከጥሩ አጀማመር በኋላ ተንሸራተው በሊጉ ግርጌ ሆነው ሊጉን ያጠናቀቁት ወልዋሎዎች በዙሩ የአማካይ ክፍላቸው እና የቡድኑ አጨዋወት ደካማ ጎናቸው ነበር። በስብስባቸው ውስጥ ተመሳሳይ የመከላከል ባህሪ ያላቸው አማካዮች የነበሯቸው ወልዋሎዎች በአማካይ ክፍል የነበራቸው ስብስብ የቡድኑን ሚዛን ያሳተ ነበር።

በአብዛኛው ገናናው ረጋሳ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ፣ አቼምፖንግ አሞስ እና ፍቃድ ደነቀ አይነት ተፈጥሯዊ ቦታቸው ተከላካይ መስመር ላይ የሆኑ ተጫዋቾች ሲጠቀሙ የተስተዋሉት ወልዋሎዎች በቡድናቸው የፈጠራ አቅሙ ከፍ ያለ ተጫዋች ባለማካታተታቸው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውለዋል።

አሰልጣኙ በዚህ ስብስብ የተጠቀሰው የረጅም ኳስ አጨዋወት ለመተግበር የወሰኑት ውሳኔ ሌላው በደካማነት የሚጠቀስ ነው። የቡድኑ አሰልጣኞች ለአጨዋወቱ የሚመቹ ግዙፍ ተክለ ሰውነት የሌላቸው እና የ50/50 ኳሶች ማሸነፍ የማይችሉ ተጫዋቾች ይዘው አጨዋወቱን ለመተግበር መሞከራቸው ለቡድኑ ውጤት መጥፋት የራሱን ድርሻ ነበረው።

ሌላው የሚጠቀሰው የቡድኑ ድክመት የተከላካይ ክፍሉ ነበር። 23 ጎሎች በማስተናገድ ሁለተኛ ብዙ ጎል የተቆጠረበት ቡድን የሆነው ወልዋሎ ፕሪምየር ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ባስፈረማቸው ተከላካዮች እና በተለመደው የአሰልጣኙ ጠጣር አቀራረብ ምክንያት የመከላከል ድክመት ይኖረዋል ብሎ የገመተ አልነበረም። ሆኖም በተለይም በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ቡድኑ የተቆጠሩበት የግብ መጠን ክፍተቱ ምን ያህል የጎላ እንደነበር ጠቋሚ ናቸው።

በሁለተኛው ዙር ምን ይጠበቃል?

በሁለተኛው ዙር አሰልጣን ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ቀጥረው በርካታ ተጫዋቾች ያስፈረሙት ወልዋሎዎች በሁለተኛው ዙር በርካታ ነገሮች ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ቡድኑ ባልተለመደ መልኩ በጥር ዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች ማስፈረሙን ተከትሎ ውህደቱ ቶሎ ወደሚፈለገው ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ስለማይጠበቅ አሰልጣኙ በአጭር ጊዜ ውጤታማ ይሆናሉ ተብሎ አይገመትም። ስለዚህ ቡድኑ በስነ-ልቦና ደረጃ በቂ ድጋፍ ካልተደረገለት መቸገሩ አይቀሪ ነው።

ሌላው የሚጠበቀው ነገር በመጀመርያው ዙር ጥሩ የሚባል የአማካይ ጥምረት ያልነበረው ይህ ቡድን በአዲሱ ስብስብ የተጠቀሰውን ቦታ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ጊዜ የማያስፈልገው ጉዳይ ነው። እንደ ቡድን በርካታ ለውጥ ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው ወልዋሎ በሁለተኛው ዙር በአዲስ ቋሚ ተሰላፊዎች ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በመጀመርያው ዙር በጨዋታዌች ጥቂት የግብ ዕድሎች የሚፈጥር ቡድን የነበራቸው ወልዋሎዎች በሁለተኛው ዙር በአማካይ ክፍል የፈጠራ አቅማቸው የተሻሉ ተጫዋቾቹ ስላስፈረሙ ችግሩ በተወሰነ መልኩ ይፈታል የሚል ግምት ቢኖርም በአጥቂ ክፍል ላይ ያላቸው የአጨራረስ ችግርም እንደ ቀላል የሚታይ ባለመሆኑ በአጨራረስም በርካታ ለውጦች አድርገው መመለስ ይጠበቅባቸዋል።



የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች

ሳሙኤል ዮሐንስ፡ በውድድር ዓመቱ በተከታታይነት ጥሩ ብቃት ካሳዩት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ሳሙኤል ዮሐንስ በበርካታ ቦታዎች ተሰልፎ ባሳየው ብቃት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል። ቡድኑ ጥሩ ባልሆነባቸው ጨዋታዎች ጭምርም በግሉ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ይህ ተጫዋች በመስመር ተከላካይነት እና በአማካይነት ተሰልፎ ተጫውቷል። ክለቡን በተቀላቀለበት የመጀመርያ ዓመት በአምበልነት እስከ መምራት የደረሰው ሳሙኤል ለብሔራዊ ቡድን ደረጃም ተስፋ ያለው ተጫዋች ነው።

ተስፈኛ ተጫዋች

ሰመረ ሀፍታይ፡ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለወጣቶች ዕድሎች በመስጠት የተሻሉ የነበሩት ወልዋሎዎች ሰመረ ሀፍታይ እና ስምዖን ማሩን አሳይተውናል። ጉዳት እስካጋጠመው ድረስ የተሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ ጥሩ በመንቀሳቀስ ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠረው ሰመረ ሀፍታይ ለሱ በማይመች የረጅም ኳስ አጨዋወት ባለው ቡድን ውስጥ ያሳየው ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ተጫዋቹ ምን ያህል ተስፋ እንዳለው አሳይቷል። ከዕድሜው አንፃር ሲታይ ጥሩ የአጨራረስ እና የውሳኔ አሰጣጡ ብቃት ያለው ይህ ተጫዋች በቀጣይ የወልዋሎ ወሳኝ ተጫዋች እንደሚሆን እያስመሰከረ ይገኛል።

በመስመር አጥቂነት / መስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው እና በብዙዎች ትኩረት ውስጥ ያልገባው ስምዖን ማሩም የቡድኑ ሌላው ተስፈኛ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ