የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች አርባምንጭ እና አዲስ አበባ ላይ ተካሂደዋል፡፡ ሲዳማ ቡና ድል ሲቀናው ዳሽን ከአርባምንጭ አንድ ነጥብ ይዞ ተመልሷል፡፡
አርባምንጭ ላይ ዳሽን ቢራን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ ካለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ይህ ጨዋታ ጥቂት የግብ ሙከራዎች ያስተናገደ ሲሆን ዳሽን ቢራ ኳስ በአርባምንጭ የግብ ክልል በእጅ ተነክቶ የፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል በሚል ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ የአቻ ውጤቱ ዳሽንን ባለበት 10ኛ ደረጃ ላይ እንዲቆይ ሲያደርገው አርባምንጭ ከተማ አንድ ደረጃን አሻሽሎ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡
በ11፡30 ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 2-1 ተሸንፏል፡፡ ሲዳማ ቡና በአዲስ ግደይ የ38ኛ ደቂቃ ግብ መሪ ሲሆን ከእረፍት መልስ በ47ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሃንስ ቡናን አቻ አድርጓል፡፡ የሲዳማን የማሸነፍያ ግብ ከመረብ ያሳረፈው አማካዩ ፍፁም ተፈሪ በ62ኛው ደቂቃ ነው፡፡ በጨዋታው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ አዲስ ግደይ (ፎቶ) ለሲዳማ ቡና ድል ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ላይ ተቀይሮ ሲወጣም በጥላ ፎቅ እና ትሪቡን አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአድናቆት አጨብጭበውለታል፡፡
የሲዳማ ቡናው የመስመር አማካይ ወሰኑ ማዜ በከባድ ጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን የጉዳት መጠኑ ከቀጣይ ጨዋታዎች ሊያርቀው እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ድሉ ሲዳማ ቡና 17 ነጥብ ሰብስቦ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጠው 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን የሚያሻሽልበትን እድል አበላሽቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ 10ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ሲቀጥሉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ ቅዳሜ በ9፡00 ሀድያ ሆሳዕናን ያስተናግዳል፡፡ እሁድ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከንግድ ባንክ 11፡30 ላይ ሲጫወት በ9፡00 መከላከያ ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዥ ፡-
የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ፡-