የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ በኬንያ አስተናግጅነት ዛሬ ተጀምሯል፡፡ ካካሜጋ ከተማ ላይ በሚገኘው ቡኩንጉ ስታዲየም እና ማቻኮስ በሚገኘው ኬንያታ ስታዲየም በተደረጉ የምድብ አንድ ጨዋታዎች ውድድሩ ሲጀመር ኬንያ በአዲሱ አሰልጣኛቻቸው ፖል ፑት እየተመራች ሩዋንዳን 2-0 አሸንፋለች፡፡ ሊቢያ እና ታንዛኒያ ያለግብ በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን ፈፅመዋል፡፡
ካካሜጋ ላይ ኬንያ ሩዋንዳን አስተናግዳ በመጀመሪያው 45 በተቆጠሩ ሁለት ግቦች 2-0 አሸንፋለች፡፡ በጨዋታው ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ የኬንያ ህዝብ ፕሬዝደንት በመሆን ቃለ መሃላ ለመፈፀም እየተሰናዱ የሚገኙት እና ቀንደኛው የፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያ ተቀናቃኝ የኬንያ ፖለቲከኛ ታዋቂው ራይላ ኦዲንጋ በእንግድነት ተገኝተዋል፡፡
የሩዋንዳ የኃላ መስመር ክፍተት መሆን አማቩቢዎቹ ለሐራምቤ ከዋክብቶቹ እጅ እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል፡፡ የሩዋንዳው ሶተር ካዩምባ ኦቴኖን ጎትቶ በመጣሉ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት መሱድ ጁማ በማስቆጠር ኬንያን ሲያደርግ ደንከን ኦቴኖ ከ25 ሜትር ባስቆጠረው ግሩም ግብ ኬንያ የ2-0 መሪነትን መጨበጥ ችላለች፡፡ ሩዋንዳ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተሻለ ብትቀሳቀስም ሶተር በ50ኛው ደቂቃ የእለቱን አርቢትር ጋር በመጋጨቱ በቀይ ካርድ መሰናቡትን ተክተሎ ለአማቩቢዎች ጨዋታውን እንዲከብድ አድርጎታል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በስታዲየሙ በጣለው ዝናብ ሜዳው ይበልጥ ለሩዋንዳ የተመቸ ቢመስልም የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ግን በሁለተኛው 45 ተዳክመው የታዩት ኬንያዎች ይሻላሉ፡፡
ማቻኮስ ላይ ተጋባዧ ሊቢያ እና ታንዛኒያ ጥሩ ፉክክር አሳይተው ያለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ በእንቅስቃሴ ሊቢያ በጨዋታው ላይ የተሻለች የነበረ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ያገኟቸውን ግልፅ የግብ ማግባት እድሎች አምክነዋል፡፡ ኤሊያስ ማጉሪ ከታንዛኒያ በኩል እንዲሁም ዛክሪ አፍሪ ከሊቢያ በኩል የተገኙትን እድሎች ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የኪሊማንጃሮ ከዋክብቶቹ በመጀመሪያው 45 ተቀዛቅዘው እንደመታየታቸው ሊቢያ ግብ አለማስቆሯ የኃላ ኃላ ሁለት ነጥብ አሳጥቷታል፡፡ አሚ ኒንጄ በህዳር ወር የታንዛኒያ አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ባደረጉት ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል፡፡ ምድቡን ኬንያ በሶስት ነጥብ ትመራለች፡፡
ውድድሩ ሰኞ ሲቀጥል በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ዩጋንዳ እና ቡሩንዲ 9፡00 ላይ ይጫወታሉ፡፡
የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ሙሉ ፕሮግራም እና ውጤት
የዛሬ ውጤቶች
ኬንያ 2-0 ሩዋንዳ
ሊቢያ 0-0 ታንዛኒያ
ሰኞ ህዳር 25
9፡00 – ዩጋንዳ ከ ቡሩንዲ (ካካሜጋ)
ማክሰኞ ህዳር 26
8፡00 – ዛንዚባር ከ ሩዋንዳ (ማቻኮስ)
9፡00 – ኢትዮጵያ ከ ደቡብ ሱዳን (ካካሜጋ)
10፡00 – ኬንያ ከ ሊቢያ (ማቻኮስ)
ሐሙስ ህዳር 28
8፡00 – ታንዛኒያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)
9፡00 – ኢትዮጵያ ከ ብሩንዲ (ካካሜጋ)
10፡00 – ሩዋንዳ ከ ሊቢያ (ማቻኮስ)
አርብ ህዳር 29
9፡00 – ዩጋንዳ ከ ደቡብ ሱዳን (ካካሜጋ)
ቅዳሜ ህዳር 30
8፡00 – ሩዋንዳ ከ ታንዛኒያ (ማቻኮስ)
10፡00 – ኬንያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)
እሁድ ታህሳስ 1
9፡00 – ኢትዮጵያ ከ ዩጋንዳ (ካካሜጋ)
ሰኞ ታህሳስ 2
8፡00 – ሊቢያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)
9፡00 – ደቡብ ሱዳን ከ ቡሩንዲ (ካካሜጋ)
10፡00 – ኬንያ ከ ታንዛኒያ (ማቻኮስ)
የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ በሶከር ኢትዮጵያ እንዲቀርብ ያስቻለው ጎ ቴዲ ስፖርት ነው፡፡ ጎ ቴዲ ስፖርት በኢትዮጵያ የማራቶን ትጥቆች ወኪል አከፋፋይ!!