የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ለተጨማሪ ወራት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚያቆየውን ውል ፌዴሬሽኑ አራዝሞለታል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቡሩንዲን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፍ ያስቻሉት የቀድሞ የደደቢት እና የሲዳማ ቡና የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ለተጨማሪ ሦስት ወራት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚቆዩበትን አዲስ ኮንትራት ፈርመዋል። ለውሉ መራዘም እንደ ምክንያት የቀረበው ብሔራዊ ቡድኑ ተስፋ ሰጪ ነገር በማሳየቱ እንደሆነ ሰምተናል።
በተያያዘ ዜና መጋቢት 13 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለሚያደርገው ጨዋታ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ተደርጎላቸው ዝግጅታቸውን ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲየም እያከናወኑ የቆዩ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ካፍ በኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ሥጋት ምክንያት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገራቸውን ማሳወቁን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ ለጊዜው መበተኑ ታውቋል።
©ሶከር ኢትዮጵያ