“አወዛጋቢው የኮከብ ተጫዋችነት ምርጫ” ትውስታ በዮሴፍ ተስፋዬ አንደበት

ኮከብ ተጫዋችነት እና እርሱ አልተገጣጠሙም እንጂ አንፀባራቂ የእግርኳስ ዘመን አሳልፏል። የወቅቱ የኢትዮጵያ ቡና የተስፋ ቡድን አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ ስለ አወዛጋቢው የኮከብ ተጫዋችነት ምርጫ በትውስታ ይናገራል።

በሰማንያዎቹ መጨረሻ እና ዘጠናዎቹ መጀመርያ ለአራት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ ጎሎችን በማስቆጠር ምርጥ ጊዜ አሳልፏል። በሙገር፣ ኢትዮጵያ መድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀጠለው የእግርኳስ ህይወቱ እስከ ብሔራዊ ቡድንም አድርሶታል። ስኬታማ ቆይታ ካደረገበት ሀዋሳ ከተማ በኋላ ለሦስት ዓመት ለሐረር ቢራ በድምሩ ለአስራ ስድስት ዓመታት መልካም በሚባል ሁኔታ የእግርኳሱ ዘመኑን አጠናቋል። ከ1996–98 ለሦስት ዓመታት በሀዋሳ ከተማ ከተማ በነበረው ቆይታ በ1996 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ሆኖም በወቅቱ ዓመቱን ሙሉ ካሳየው ወጥ ብቃት አንፃር ኮከብ ተጫዋች ሽልማትን ያገኛል ተብሎ ሲጠበቅ ሳያገኝ የቀረበት ሁኔታ በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በዛሬው “ትውስታ” አምዳችን ይህን ጉዳይ አንስተንለት በዚህ አጫውቶናል።

“የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴው በየጨዋታው ያሳየሁትን እንቅስቃሴ እየተከታተለ ለእኔ ጥሩ ነጥብ ሰጥቶኝ እንደነበረ አውቃለው። ሆኖም አንድ አሰልጣኝ የክልል ቡድን አሸናፊ በሆነበት ዋንጫ እንዴት የአዲስ አበባ ልጅ ኮከብ ይባላል። በሚል ምክንያት የኮሚቴው አባል ኢትዮጵያ መድን በሚያሰለጥንበት ወቅት ከእኔ ጋር የነበረውን አለመግባባት ተገን አድርጎ ለእኔ ሊሰጥ የነበረውን ሽልማት በመጨረሻው ዕለት ለሙልጌታ ምህረት እንዲሰጥ አድርጓል። በወቅቱም ራሱ ሙልጌታ ምህረት ሌላ ሚዲያ ላይም ተናግሮታል፤ ይህ ሽልማት ለዮሴፍ ይገባው ነበር በማለት። ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላም ወደ እኔ በመምጣት አቅፎኝ ይህ ሽልማት ላንተ ይገባህ ነበር ብሎኛል። ይገርምሀል ኢትዮጵያ ቡና እያለውም በ1989 ኮከብ ጎል አግቢን በ11 ጎል እየመራው በመጨረሻ ተከተል ኦርጌቾ በአንድ ጎል በልጦኝ ኮከብ ሆኗል። በ16 ዓመት የተጫዋችነት ቆይታዬ ኮከብነት እና እኔ አልተገጣጠምንም ማለት ይቻላል”።

ዮሴፍ የአሰልጣኝነቱን ጎራ በመቀላቀል ያለፉትን ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ቡና ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድንን ሲመራ የቆየ ሲሆን በቅርቡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን አገልግሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ