ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ካሉ ጥሩ አጥቂዎች መካከል አንዱ የነበረው እና በሁለቱ የሸገር ባላንጣ ክለቦች መጫወት የቻለው ቢንያም አሰፋ አሁን የት ይገኛል?
“ደፋር ነው፣ ሜዳ ውስጥ ሲገባ ሁሉ ነገሩን ይሰጥሀል” ይሉታል አብረውት የተጫወቱ ሲመሰክሩ። ከተለመዱት የፊት አጥቂዎች በተለየ ባለተስጥኦ መሆኑ እና የግራ እግሩ ጠንካራ ምት መለያው ነው። ቢንያም አሰፋ ትውልድ እና ዕድገቱ አዲስ አበባ ነው። በኒያላ፣ በወንጂ ስኳር፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በሰበታ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (በሦስት ጊዜያት)፣ ጅማ አባ ቡና እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫውቶ አሳልፏል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አምስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከማንሳቱ ባሻገር በ1998 የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። በኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድን፣ ኦሊምፒክ እና በዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሏል። በተለያዩ ዓመታት የኮከብ ጎል አግቢነት ፉክክር ውስጥ መግባት የቻለው ቢንያም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከዕይታ መራቁን ተከትሎ ኳስ አቆምክ? ወይስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ? ስንል ካለበት ሀገር አሜሪካ በስልክ ጠይቀነው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቶናል።
“በእግርኳስ ተጫዋችነት በቆየሁባቸው 15 ዓመታት እጅግ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉት ሁለቱ ትልልቅ ቡድኖች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወቴ በጣም ዕድለኛ እና ሁሌም ሳስበው የሚያስደስተኝ ነው። አሁንም ቢሆን የመጫወት አቅሙ፣ ልምዱ ነበረኝ። ሆኖም የኢትዮጵያ እግርኳስ እንዲህ ነው ብለህ የማትገልፀው በርካታ ውስብስብ ችግሮች እና እግርኳሱን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚቀይሩ በርካታ ነገሮች መኖራቸው እግርኳስን ለማቆም (ጫማ ለመስቀል) አንዱ ምክንያት ሆኖኛል። ወደፊት በስፖርቱ የሚኖረኝን ተሳትፎን አሁን ላይ ሆኜ መናገር ባልችልም ወደፊት የምናየው ይሆናል። አሁን ከኢትዮጵያ ውጭ በሀገረ በአሜሪካ ከባለቤቴ እና ከወንድ ልጄ ጋር እየኖርኩ እገኛለው”።
ሶከር ኢትዮጵያ ከቢንያም አሰፋ ጋር አጠቃለይ የእግርኳስ ህይወቱ አስመልክቶ ሰፊ ቃለ መጠይቅ ያደረገች መሆኗን እየገለፀች ምሽት ላይ በ”ትውስታ” አምድ እንዲሁም በቅርብ ቀናት ደግሞ የእግርኳስ ሕይወቱን የሚዳስሰውን ቃለመጠይቅ ለንባብ የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ