ወደ ፊት ብዙ ተሰፋ የተጣለበት እና የበርካታ የሊጉ ክለቦች ዓይን ማረፊያ የነበረው የቀድሞው የአዳማ ከተማ የመስመር አጥቂ ታከለ ዓለማየሁ አሁን የት ይገኛል?
የአሁኑ የለገጣፎ አሰልጣኝ በዳዊት ሀብታሙ በሚሰለጥነው ፕሮጀክት በመጫወት ያደገው ታከለ በ2002 የአዳማን ተስፋ ቡድን ተቀላቅሎ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አማካኝነት ወደ ዋና ቡድን አድጓል። የመስመር አጥቂ እና አማካይ ሆኖ መጫወት የሚችለው ባለ ተስጦኦው ተጫዋች በ2005 ባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የወቅቱ መጠርያው ብሔራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ላይ አዳማ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዳግም ሲመለስ ትልቁን አስተዋፆኦ ከመወጣቱ በተጨማሪ ወሳኙን ጎል በማስቆጠር ወሳኝ ሚና ተወጥቷል። እስከ 2008 መጨረሻ አካባቢ ድረስ በጥሩ አቋም መዝለቅ የቻለው ታከለ 66 ሺህ ብር ወርሐዊ ደሞዝ በመከፈል ከአስራት መገርሳ ጋር የወቅቱ ወድ ተከፋይ መሆንም ችሎ ነበር።
ተጫዋቹ በወቅቱ ኮንትራቱ መጠናቀቂያ ላይ ደርሶ የነበረ በመሆኑ በርካታ ክለቦች እርሱን ለማስፈረም ቢፈልጉም በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን ተጫዋች ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይቶ ነበር። ይህ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ተጫዋች በአንድ አገጣሚ ዓይኑ ላይ በደረሰበት ጉዳት በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ህክምናውን ሲከታተል ቢቆይም አንድ ዓይኑን ማትረፍ ባለመቻሉ (በመጥፋቱ) ያለ ዕድሜው ከሚወደው እርግኳስ ተለይቷል። በወቅቱ የተፈጠረው ድርጊት የብዙዎችን የስፖርት ቤተሰብ ልብ የሰበረ ጉዳይ መሆኑም ይታወቃል። ያለፉትን ሦስት ዓመታት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ተሳክቶ ይህን ብሎናል፡-
” ጊዜው በጣም ከባድ ነበር። አንዳንዴ እውነት አይመስለኝ ሁሉ ነበር። በአንድ አጋጣሚ በተፈጠረ አለመግባባት እንዲህ ይሆናል ብዬ የማላስበው ሁኔታ ተፈጥሯል። ብዙ ነገር ለማድረግ በትልቅ ደረጃ ለጫወት ፍላጎት ነበረኝ። ያው ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው። አሁን ከዛ ህይወት አውጥቶ ጥሩ የሥራ ዕድል ፈጥሮልኝ እንዳላማርረው አድርጎኝ ሥራ እየሰራሁ እገኛለው። ከምወደው እግርኳስ መለየቴ ብቻ ካልሆነ በቀር አሁን ባለኝ ነገር ደስተኛ ነኝ። እግርኳስ ካቆምኩ በኋላ ሜዳ እየመጣው ኳስ እመለከት ነበር። ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን መመልከትን አቁሚያለው። ምክንያቱም ጓደኞቼ ሲጫወቱ ሳይ እኔም ብኖር እያልኩ መረበሽ ስጀምር እግርኳስን ሜዳ መጥቼ ማየት አቁሜያለው።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ