“በመንግሥት ለውጥ ምክንያት በ17ኛው ሳምንት የተሰረዘው ውድድር…” ትውስታ በገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) አንደበት

በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት የ2012 አጠቃላይ የሊግ ውድድሮች እንዲሰረዙ ዛሬ መወሰኑ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም በ1983 በመንግሥት ለውጥ ምክንያት ስለተሠረዘው ውድድር ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) በትውስታ አምዳችን አጫውቶናል።

በዘንድሮ ዓመት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ስለምትገኝ እና ወረርሽኙ እንደ ሀገር መቆጣጠር እንደሚቻል ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ተከትሎ የ2012 የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ተሰርዘዋል። በዚህም መሠረት በየትኛውም የውስጥ ሊግ ቻምፒዮን እንዲሁም ወራጅ የሌለ በመሆኑ ቀጣይ ዓመት የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴርሽንስ ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክል ክለብ አይኖርም በማለት ማሳወቁ ይታወሳል። በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ መሰል ውሳኔ የተስተናገደው ከ29 ዓመታት በፊት ሲሆን የደርግ መንግሥት ግንቦት 20 ቀን 1983 ከሥልጣን በተነሳበት ወቅት ነበር የውድድር መሰረዝ ያጋጠመው። የ2012 የ17ኛው ሳምንት ተጠናቆ 18ኛው ሊጀመር ሲል ሲቋረጥ፣ የ1983 ውድድር ደግሞ 17ኛው ሳምንት ተጠናቆ ከ18ኛው ሳምንት አንድ ጨዋታ ብቻ ተደርጎ ውድድሩ መሰረዙን “የኢትዮጵያ እግርኳስ ተንቀሳቃሽ ቤተ መፀሐፍት” እየባለ የሚሞካሸው ጋዜጠኛ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ጊዜውን ወደ ኋላ ሃያ ዘጠኝ ዓመት መልሶ እንዲህ ያስታውሰናል። መልካም ንባብ

“በ1983 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ የሚካፈሉ ቡድኖችን ለመለየት በየክፍለ ሀገሩ የዙር ውድድሮች ይካሄዳሉ። የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በበላይነት የሚመራው የአዲስ አበባ ሻኝፒዮናም የዚህ አካሄድ አካል ነበር። የአዲስ አበባው ውድድር 12 ክለቦች መካከል የሚካሄድ ሲሆን በሁለት ዙር በሚደረጉ 22 ጨዋታዎች አሸናፊው ቡድንና ወደ ኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚያድጉ ሁለት ቡድኖች ይለይበታል። (በወቅቱ በአንድ ጨዋታ ላሸነፈ ቡድን ይሰጥ የነበረው ነጥብ ሁለት መሆኑ ልብ ይሏል።) በጊዜው ውድድሩ አንደኛው ዙር ተጠናቆ የሁለተኛው ዙር 17ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። (የታሪክ መገጣጠም ዘንድሮም በ17ኛው ሳምንት መቋረጡ…)። በወቅቱ ኪራይ ቤቶች፣ እርሻ ሠብል፣ ሜታ ቢራ፣ መብራት ኃይል (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)፣ አዲስ ቢራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ቡና ገበያ (ኢትዮጵያ ቡና) ባህር ኃይል፣ ባንኮች (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) መድን (ኢትዮጵያ መድን)፣ ምድር ጦር፣ ኦሜድላ ተካፋይ ነበሩ።

” በ17 ሳምንታት በተደረጉ ጨዋታዎች አዲስ ቢራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) በ24 ነጥቦች ሲመራ ኪራይ ቤቶች በ22 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር። ኤሌክትሪክ እና እርሻ ሰብል ደግሞ 21 ነጥቦች ሰብስበው ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል። መድን፣ ቡና እና ባንኮች በ19 ነጥቦች ተከታትለው ሲቀመጡ ሜታ ቢራ በ6 ነጥብ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ መውረዱን አረጋግጦ ነበር ወደ 18ኛ ሳምንት ጨዋታ የተሸጋገሩት። በጊዜው በአዲስ አበባ ስታዲየም የ18ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ ግንቦት 17 ምድር ጦር ከ ኪራይ ቤት፣ እሁድ ግንቦት 18 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ እርሻ ሠብል እና ኢትዮጵያ መድን ከባንኮች እንዲጫወቱ መርሐግብር ወጥቶላቸው ነበር። ግንቦት 20 (ማክሰኞ) የመንግሥት ለውጥ ሊሆን ቅዳሜ ግንቦት 17 በአዲስ አበባ ስታዲየም በኪራይ ቤት እና በምድር ጦር መካከል ጨዋታ ሊደረግ ወደ ስታዲየም ሄድን፤ ሆኖም የስፖርት ቤተሰቡ ጨዋታ ለመከታተል ወደ ሜዳ አልመጣም። ምክንያቱም ከተማው በስጋት ተወጥሮ፣ አንዳንዱ ፈርቶ ቤቱ የቀረ አለ፣ ሌላኛው በግርግሩ ተጠቅሞ ዝርፊያ የገባም ነበር። ብቻ ብዙም ከተማዋ ላይ የተረጋጋ ነገር አልነበረም። ጨዋታው የሚደረግበት ሠዓት ሲደርስ ኪራይ ቤት ሜዳ ሲገኝ ምድር ጦር ሳይመጣ ቀርቷል። ምድነው ብለን ስናጣራ የምድር ጦር ተጫዋቾች እዛው መከላከያ ግቢ ውስጥ መሳርያ እየዘረፉ ነው ተባለ። እንዲያውም አንድ የቡድኑ ተጫዋች (በኋላ አሰልጣኝ የሆነ እና ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ስሙ ያልተጠቀሰ) ብዙ መሳርያ እንደዘረፈ ይነገራል። በመጨረሻም የዚህ ጨዋታ ለኪራይ ቤት ፎርፌ ሲሰጠው ከ22 ነጥብ ወደ 24 ከፍ ሲል በነጥብ ከአዲስ ቢራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ጋር እኩል 24 ነጥብ ላይ በመሆን በጎል ክፍያ በልጦ አንደኛ ሆነ። እሁድ ግንቦት 18 ቀን ሊካሄዱ የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ እርሻ ሠብል እና ኢትዮጵያ መድን ከባንኮች ጨዋታዎች ከተማው ላይ ከፍተኛ ሁከት እና ፍራቻ በመኖሩ ሳይካሄድ ሲቀር ሌሎች የ18ኛ ሳምንት የማክሰኞ ጨዋታዎችም ሳይደረጉ ግንቦት 20 የመንግሥት ለውጥ መጥቷል።

” ከመንግሥት ለውጡ በኋላ ውድድሩ ያልቀጠለ ሲሆን አወዳዳሪው አካል የ1983 ውድድር ቻምፒዮንም ሆነ ወራጅ ቡድን እንዳይኖራቸው ተደርጎ እንዲሰረዝ ወስኗል። በተመሳሳይ የ1983 የኢትዮጵያ ሻምፒዮናም ሳይካሄድ ቀርቷል። በቀጣዩ ዓመት የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና አዲስ ቢራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ተሳታፊ የነበረ ሲሆን በምን አኳኋን እንደተሳተፈ ግን ግልፅ መረጃ የለም።”

* በቀጣዩ ዓመት ( 1984) የተፈጠረውን አስገራሚ የውድደር ክስተት አስመልክቶ ከገነነ መኩርያ ጋር ያደረግነውን ጥሩ ቆይታ ነገ ይዘን እንመለሳለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ