የአዕምሮ ጤና ጉዳይ በእግርኳሱም ሆነ በሌሎች የውድድር ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባውን ስፍራ አላገኘም። በፕሮፌሽናል እግርኳስ የሚደረጉ በርካታ ሳይንሳዊ ጥናቶችም ባብዛኛው በተጫዋቾች አካላዊ ጤና እና ብቃት ላይ ያተኮሩ በመሆኑ በስፖርቱ ተሳታፊዎች የአዕምሮ ጤና እና እክሎቹ ላይ ብዙ መረጃ አይገኝም።
በቀደሙት ዓመታት በከፍተኛ ውድድሮች የሚጫወቱ በርካታ ተጫዋቾች ለስራቸው እንቅፋት ላለመፍጠር እና መገለልንም በመፍራት በጉዳዩ ላይ ዝምታን በመምረጣቸውም ምናልባትም የሚያደርጉት መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የሚያገኙት የቡድን ድጋፍ እና በጥሩ ማህበራዊ ሁኔታ መገኘታቸው (ጥሩ የፋይናንስ አቅም፣ በህዝብ መወደድ) ተጫዋቾቹ የአዕምሮ ህመም እንዳያጋጥማቸው ሊከላከሉላቸው እንደሚችሉ ሲታመንበት ቆይቷል። እንደ ፖል ጋስኮኝ እና ሰባስቲያን ዳይስለር ያሉ ተጫዋቾች የአዕምሮ ጤና እክል ስላጋጠማቸው እና ይህንንም ይፋ አድርገው ስላወጡ ብቻ በወቅቱ የደረሰባቸው መገለል፤ የቡድናቸውም ደካማ አካል ሆነው መብጠልጠላቸው ሲታይ በርካታ ተጫዋቾች በጉዳዩ ዙሪያ ከመነጋገር ይልቅ ችግራቸውን ይዘው መቀመጥ ለምን እንደመረጡ ግልፅ ይሆናል።
በቅርብ ዓመታት ግን ነገሩ እየተለወጠ የመጣ ይመስላል። ከዓለም አቀፉ የእግርኳስ ማህበር ፊፋ ጀምሮ ሌሎችም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ውይይቶች እንዲደረጉ እየሰሩ ሲሆን በአውሮፓ ታላላቅ ሊጉች የሚሳተፉ ክለቦችም ለተጫዋቾቻቸው ድጋፍ የሚሰጡ ቋሚ የስነ-አዕምሮ ሐኪሞችን ቀጥረው በማሰራት ላይ ይገኛሉ።
በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ ጥናቶች ቁጥር በአንፃራዊነት እየጨመረ ሲገኝ የሁሉም ጥናቶች ውጤትም እግርኳስ ተጫዋቾች ለአዕምሮ ጤና እክሎች ያለው ተጋላጭነት ከአጠቃላይ ህዝቡ ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ መሆኑን ነው። ለአብነት የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማህበር (ፊፍፕሮ) እ.ኤ.አ. በ2015 የዳሰሳ ጥናት ብንመለከት በጥናቱ ከተሳተፉ ተጫዋቾች ውስጥ 38%፤ ከቀድሞ ተጫዋቾች ደግሞ 35% የሚሆኑት ችግሩ እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።
ተጫዋቾች በጨዋታ ዘመናቸው የአዕምሮ ጤና መዛባትን ሊያስከትሉ ለሚችሉ የተለያዩ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የውጥረት ምንጮች (Stressors) ተጋላጭ በመሆናቸው የጥናቱ ውጤት አስገራሚ ላይሆን ይችላል። ተጫዋቾች ሁልጊዜም ከፍተኛ ጫና ባለው እና ውጤት በሚጠበቅበት ሁኔታ ላይ ከመገኘታቸው ጀምሮ፣ ከቤተሰብ መራቅ፣ የአቋም መውረድ፣ በጉዳት ሜዳ መራቅ፣ ከቡድን አጋሮች እና ከአሠልጣኞች ጋር የሚከሰቱ ግጭቶች፣ ውጤት ማጣት፣ በዕድገት እና ዝውውር ጉዳዮች ደስተኛ አለመሆን፣ አልኮል እና ሌሎች ዕፆችን መጠቀም፣ በመጨረሻም በዕድሜ ምክንያት ከጨዋታ መገለል እንደ ጭንቀት እና ድባቴ ላሉ የአዕምሮ ህመሞች የሚያጋልጡ ምክንያቶች ናቸው።
ዓለምን እያመሠ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (COVID-19) ስርጭት ለመቆጣጠር በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት የፕሮፌሽናል እግርኳስ የውድድር ዓመት በጊዜያዊነት እንዲቆም ወይም እንዲሰረዝ ሆኗል። በዚህ ምክንያት የእግርኳስ ጨዋታዎች ባለመደረጋቸው ተጫዋቾች ቤት ውስጥ ለመዋል እና ልምምድ በግላቸው ለመስራት ተገደዋል። ከሚወዱት ጨዋታ፣ ከቡድን ጓደኞቻቸው እና ከሚከታተላቸው ደጋፊ መራቃቸውም በተጫዋቾች ላይ የሚያደርሰው ስነልቦናዊ ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ድባቴ እና ጭንቀት በዚህ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ህመሞች ናቸው። ነገሮችን ለማድረግ ተነሳሽነት ማጣት ፤ ከመጠን በላይ መተኛት ወይም እንቅልፍን ማጣት ፤ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፤ ለ2 ሳምንታት እና ከዛ በላይ የሚቆይ የሐዘን ሰሜት (low mood) እና የመሳሰሉት የድባቴ መገለጫዎች ናቸው። ጭንቀት ደግሞ ከመጠን በላይ ስለነገሮች በማሰብ እና ማላብ እንደዚሁም የልብ ምት መጨመር በመሳሰሉት ይገለፃል።
የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማህበር (ፊፍፕሮ) እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 22 እስከ ሚያዚያ 14, 2020 ዓ.ም. በ1,602 ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ላይ አደረግኩት ባለው ጥናት መሠረትም 22% የሚሆኑ ሴት ተጫዋቾች እንደዚሁም 13% የሆኑ ወንድ ተጫዋቾች ድባቴን የሚጠቁሙ ምልክቶች ሲያሳዩ 18% ሴቶች እና 16% ወንዶች ደግሞ በጭንቀት ተጠቅተዋል። ይህ አሃዝም የአዕምሮ ጤና እክል ያጋጠማቸው የእግርኳስ ተጫዋቾች ቁጥር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች ከቆሙ በኋላ በእጥፍ መጨመሩን ያሳያል።
የፊፍፕሮ የህክምና ሃላፊ ዶ∕ር ቪንሰንት ጎውተባርግ “ወጣት ወንድ እና ሴት የእግርኳስ ተጫዋቾቻችን በማህበራዊ ህይወታቸው መለየት እና የዕለት ተለት ስራቸውን ለማቋረጥ የተገደዱበት፤ እንዲሁም ስለ ወደፊት ኑሯቸው ጥርጣሬ እና ፍርሃት እንዲገባቸው የሆኑበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። አንዳንዶቹ እነዚህን ፈተናዎች ለመወጣት የሚያስችላቸው ጥንካሬ የላቸውም፤ እኛም ከሚያምኑት ሰው ወይም ከስነ-አዕምሮ ባለሞያ እርዳታን እንዲጠይቁ እናበረታታቸዋለን” ሲሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የፊፍፕሮ መልዕክትም የእግር ኳስ ክለቦች የተጫዋቾቻቸውን የአዕምሮ ጤና በቅርበት መከታተል የሚችሉ የሕክምና ባለሙያዎች ሊኖሯቸው እንደሚገባ ይገልፃል።
የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝን ለመግታት መውሰድ ያለብን ጥንቃቄዎች አሁንም ወሳኝነታቸው እንዳለ ሆኖ በዚህ ወቅት በተለየ ሁኔታ ለአዕምሮ ጤና የተለየ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። በተቻለ መጠን ስለሚያጋጥሙን ችግሮቻችን በግልፅነት መወያየት እንደዚሁም ስሜታችን ጥሩ አለመሆኑ የሚቀጥል ከሆነም የጤና ባለሙያን ማማከር መቻል አለብን።
በቅርቡ በድረገፃችን እንዳስነበብነው ከውድድሮች ርቀው በቤታቸው ለሚገኙ ስፖርተኞችን የመረጃ መረብን በመጠቀም ነፃ የስነ-ልቦና ህክምና ድጋፍ ለማድረግ ያቀደ እና የስነ-አዕምሮ ሬዚደንት ሃኪሞችን ያቀፈ የበጎ ፈቃድ ቡድን ወደ ስራ ገብቷል። ሀኪሞቹም ዘወትር ረቡዕ ምሽት ከ11:00 – 01:00 እንዲሁም እሁድ ጠዋት ከ05 ፡00 – 07:ዐዐ ድረስ ለዚሁ ዓላማ በተከፈተው እና ከታች በተገለፀው የቴሌግራም ግሩፑ ላይ ኦንላይን ሆነው የሚጠባበቁ ሲሆን ህክምናውንም ኦንላይን ወይንም በስልክ በኩል ከዛም አለፍ የሚል ከሆነ በአካል በመገናኘት በበጎ ፍቃደኝነት የሚሰጡ ይሆናል። እኛም ከላይ በተለይም ከላይ የተጠቀሱትን የድባቴ እና የጭንቀት ምልክቶች በራሳቸው ላይ የሚመለከቱ እግርኳስ ተጫዋቾች እና አትሌቶች ወደ ቴሌግራም ግሩፑ በመግባት የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንመክራለን።
እገዛውን ማግኘት የምትፈልጉ ስፖርተኞች ይህን ሊንክ በመጠቀም ወደ ቴሌግራም ግሩፑ መቀላቀል ትችላላችሁ። 👉 TELGRAM