በኢትዮጵያ እግርኳስ ከአዲሱ ሚሊኒየም ወዲህ ብቅ ካሉ ጥሩ የፊት መስመር ተጫዋቾች አንዱ ነው ፤ ግዙፉ አጥቂ ተመስገን ተክሌ። በክለብ ደረጃ በ1999 በኦሜድላ (ፌድራል ፖሊስ) መጫወት የጀመረው ተመስገን ከአንድ ዓመት በኃላ ወደ ወደ ደደቢት አምርቶ ለአምስት ዓመታት ድንቅ ጊዜን አሳልፏል። በመቀጠል በ2005 አጋማሽ ወደ ሀዋሳ አምርቶ እስከ 2007 ተጫውቷል። ሆኖም ተጫዋቹ በእግር ኳሱ የረጅም ዕድሜ ቆይታን ሳያሳየን ገና በጊዜ በጉልበት ጉዳት ህመም የተነሳ ያለፉትን አራት ዓመት ከግማሽ ከእግርኳሱ ርቋል።
በግንባር ገጭቶ ግቦች ማስቆጠር መገለጫው የሆነው አጥቂው ወደ እግር ኳስ ለመመለስ አስቦ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ህክምና ቢያደርግም ወደሚወደው ስፖርት ሊመልሰው ግን አልቻለም፡፡ ተጫዋቹን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ስንጠይቀው ጉዳቱ በውስጡ የፈጠረበት እጅጉን አሳዛኝ ስሜት ከባድ ቢሆንም ኋላ ላይ ፍቃደኝነቱን አረጋግጦልን ስለ አጠቃላይ የእግርኳስ ሕይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታን አድርጓል፡፡
የት ተወለድክ ? ስለአስተዳደግህ እና ስለእግር ኳስ አጀማመርህ ጠቅለል አድርገህ ንገረን…
የተወለድኩት በኢሉ አባቡራ ዞን በደሌ ከተማ ነው፡፡ እንደማንኛውም የሀገራችን ተጫዋች በሰፈር ውስጥ ነው ኳስን ስጫወት ያደኩት። ከዛም ዕድሜዬ እያደገ ሲመጣ በፕሮጀክት ታቀፍኩ ፤ ትምህርቴን እስክጨርስም ከበደሌ ከተማ አልወጣሁም። ትምህርቴን ልክ እንደጨረስኩ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ወንድሜ ታገል ተክሌ (ኦሜድላ ይጫወት ነበር ፤ የመጀመሪያ የቤታችን ልጅ ነው፡፡) ለንጉሴ ገብሬ ልምምድ ብቻ እንዳደርግ አስፈቀደልኝ። እኔ እዛው ያለ ደመወዝ ልምምድ ብቻ ማድረግን ጀመርኩ። እዛው ኦሜድላ ውስጥ በዛኑ ዓመት ግማሽ ላይ ቴሴራ ወጥቶልኝ ተጫወትኩ። በቀጣዩ ዓመት 2000 ላይ ከደደቢት ጋር ይመስለኛል የወዳጅነት ጨዋታ ተጫውተናል። እዛ ጨዋታ ላይ የደደቢት አሰልጣኝ የነበረው ኃይለሚካኤል (ኮከቤ) ተመለከተኝ። ያኔ ደደቢት ልክ ብሔራዊ ሊግ ሲገቡ እኔም ወደ ደደቢት እንድመጣ አሰልጣኝ ኮከቤ ደወለልኝ። 2000 ላይ ከኦሜድላ ወጥቼ ወደ ደደቢት ገባሁ፡፡
በደደቢት ጥሩ ጊዜን አሳልፈሀል ማለት ይቻላል። ጌታነህ ክለቡን በተቀላቀለበት ወቅትም ጥሩ ጥምረት ነበራችሁ። የደደቢት ቆይታህ እንዴት ነበር ?
የደደቢት ቆይታዬ በጣም አሪፍ ነው፡፡ 2000 – 2001 ከክለቡ ጋር ብሔራዊ ሊግ ነበረ የተጫወትኩት። ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። በሁለቱም ዓመታት የክለቡ ኮከብ ጎል አግቢ እኔ ነበርኩ። በ2001 ከደደቢት ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጋችንን ካረጋገጥን በኋላ እነ ጌታነህ ከበደ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ሙሉጌታ ምህረት.. ብዙ ትልልቅ የሚባሉ ተጫዋቾች ወደ እኛ ክለብ መጡ። የዛኔ ገና ልጆች ነን። ገና ከብሔራዊ ሊግ ነበር የመጣነው ፤ ለእኔም ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ 2002 ፕሪምየር ሊግ ላይ የክለቡ ጎል አስቆጣሪ ነበርኩ። እኔ ፣ ጌታነህ ፣ የተሻ እና ጥላሁን የሚባል አጥቂ ነበርን በስብስባችን ውስጥ የነበርነው። አብዛኛውን ጊዜ እኔ ፣ ጌታነህ እና የተሻ እየተፈራረቅን አሪፍ ጥምረት ነበረን። እንደ ቡድንም በጊዜው ጥሩ ነገር ነበረን። በመጀመሪያ ዓመታችን ሁለተኛ ሆነን ከዛ በመቀጠል ደግሞ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና ሆንን። ያ ጊዜ ልረሳው የማልችለው ወቅት ነበር።
ከደደቢት በምን ምክንያት ተለያየህ ? በመቀጠል የነበረው የሀዋሳ ቆይታህስ ምን መሳይ ነበር ?
በደደቢት ብዙ ጊዜ ቆይቻለሁ፤ ከ2000 እስከ 2005 ጥር ወር ድረስ ቆይቼ በሰላማዊ ሁኔታ ነበር የተለያየነው። ከኮሎኔል ዐወል ጋር ጥሩ ወዳጆች ነበርን። በወቅቱ ከክለቡ ስለያይ መጫወት ባለብኝ ሰዓት መጫወት ስላልቻልኩ ነበር ፤ ወይ የኔ ወይም የአሰልጣኙ ችግር ይሆናል በወቅቱ አያጫውተኝም። አሰልጣኛችን አብርሀም ተክለሀይማኖት ነበር። እኔ ደግሞ በሰዓቱ መጫወት የምፈልግ ልጅ ነኝ። በዚህ የተነሳ ተጋጭተን ነበር። ‘እኔ መጫወት እፈልጋለሁ ፤ ካልፈለከኝ እና የማትጠቀምብኝ ከሆነ ልቀቀኝ’ ብዬ ጠየኩት። እሱም ‘እሞክራለሁ’ ብቻ ነበር ያለኝ። መጫወት በነበረብኝ ሰዓት ተጠባባቂ አደረጉኝ። ከዛ በቀጥታ ኮሎኔል ዐወልን ደውዬለት ያለውን ነገር ነገርኩት። ‘እኔ መጫወት ነው የምፈልገው። በዚህ ዕድሜዬ ቁጭ ማለት አልፈልግም። በማንኛውም ሁኔታ መጫወት ነው የምፈልገው ፤ አልቀመጥም። ለቅቄ ሌላ ቦታ ልጫወት ፤ ቡድኔን ካልጠቀምኩ እኔም እየተጎዳሁ ነው። ስለዚህ ልቀቀኝ።’ ብዬ ጠየኩት። ከሦስት ቀናት በኃላም ደወለልኝ እና ‘ቡድን ፈልግ’ አለኝ። ወዲያውኑ ቀጥታ ወደ ሀዋሳ ከተማ ነው የሄድኩት። በወቅቱ ሌላ ክለብ የመግባት ብዙ አማራጮች ነበሩኝ። አዳማ ፣ ንግድ ባንክ ፣ መድን እና ሌሎች ክለቦችም ይፈልጉኝ ነበር፡፡ ግን ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጋር እንግባባ ነበር። ምክንያቱም በደደቢት ከገብረመድህን ኃይሌ ጋር አሰልጥኖኛል። በሰዓቱ በቢኒያም ሀብታሙ እና ሙሉጌታ ምህረት በኩል ከዘላለም ሽፈራው ጋር ተነጋግረን ተስማማን። በ2005 የመጨረሻ አራት ወራት ጥሩ ነገር አሳየሁ። በዛች አጭር ቆይታዬ ስምንት ጎል አገባሁ። በቀጣዩ ዓመትም ክለቡ ፍላጎት ስለነበረው እንድቀጥል ተደረገና ውል አራዘምኩ። ሁለቱንም ዓመት በጥሩ ሁኔታ ካሳለፍኩ በኋላ በድጋሚ እዛው እንድቀጥል ተደረገ። ከዛ በኋላ ግን የጉልበት ህመሜ መጣ። በ2007 ለወራጅነት የምንጫወትበት ወቅት ስለነበር አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ እኔም አሞኛል ብዬ መናገር ከበደኝ ፤ ያኔ ምንም አማራጭ አልነበረኝም ውበቱ የመጣበት ዓመት ነበር። በሰዓቱ እያመመኝ ድንገት ወደ ሜዳ እየገባሁ ጎል የማስቆጥረው እኔ ነበርኩ። ጎል እያስቆጠርኩም ስለሆነ ህመም እየተሰማኝ መውጣትም አመመኝ በቃኝ ማለትም ከበደኝ። ጉዳቱ እየባሰብኝ እንደመጣ ደግሞ እኔ አላውቅም ነበር። እውነት ለመናገር ህመሙ ይሰማኝ ነበር። ግን ሳላውቀው ውስጥ ውስጡን በጣም እየተጎዳው ነበር። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወቅት እኔ ተቀይሬ ገብቼ 2-1 ያሸነፍንበት ጨዋታ ላይ ልምምድ አልሰራሁም ነበር። ሀዋሳ ላይ አሰልጣኝ ውበቱ መጥቶ አናገረኝ ‘የምትችል አይመስለኝም ጥሎ ማለፉን’ አለኝ ‘አዎ ውቤ የምችል አይመስለኝም ፤ ግን እግሬን ጠምጥሜም ቢሆን እጫወታለሁ እንደተለመደው’ አልኩት። ከዛን ልምምድ አልሰራሁም ቤንች ሆንኩኝ በጨዋታው ስልሳ ምናምነኛ ደቂቃ ላይ ነው ቀይሮ ያስገባኝ። እያመመኝ ነበር የተጫወትኩት ፤ ገባሁ 2ለ1 አሸነፈን ወጣን። ያኔ ህመሙን ነው እንጂ የማውቀው ጡንቻዬ ይቀንስ አይቀንስ የማውቀው ታሪክ የለም። ለካ ውስጥ ውስጡን በጣም እየተጎዳ ነው። ሎሚዬ ላይ ያመኛል ፤ ስረግጥ ሁላ መታመም ጀመርኩ። ጡንቻዬ ምንም የለም ፤ ደክሟል። ዳገት መውጣት እስካለመቻል ደረስኩኝ ይታወቀኝ ጀመር። ልክ ውድድር ጨርሰን ክረምት ላይ ነው ህመሜን በደንብ ያወቅኩት። እግሬን ከአንደኛው ጋር ሳነፃፅረው ጉልበቴን ነበር ያመመኝ። የጉልበት ህመም ደግሞ ጡንቻዎችን በጣም ይከሳል። ክረምት ላይ ቤት ቁምጣ አድርጌ ቁጭ ብዬ እግሮቼን ሳይ በጣም ነበር የደነገጥኩት ፤ መናገር ከምችለው በላይ። ከዛም በቀጥታ ለ2008 ዝግጅት ግቡ ተባልን። እኔም ዝግጅት ከቡድኑ ጋር ብገባም ህመሙን አልቻልኩም። የዛን ዓመት ደግሞ የሀዋሳ ሜዳ አርቴፊሻል ሳር ሆኖ ጠብቆናል። እሱ ደግሞ በጣም ጉልበት የሚጠይቅ ሜዳ ነው። እኔ ደግሞ አልቻልኩም መታከም እንዳለብኝ ከራሴ ጋር አወራሁ ከቤተሰቤም ጋርም ተነጋገርኩ ከዛ በኃላ በቃ ኳሱን አቁሜ ወደ ህክምና ነው የገባሁት፡፡
ለህክምና ወደ ደቡብ አፍሪካ ነበር ያቀናኸው። የህክምናህ ሁኔታ እንዴት ነበር ? አሁንም ላይሻልህ የቻለበትስ ምክንያት ?
ብዙ ህክምና አድርጌበታለሁ። እግዚአብሔርን ምን እንዳደረኩት አላውቅም። ምክንያቱም የኔ በሽታ ትንሽ አስቸጋሪ ነው ብዬ ነው የማስበው። በጣም ብዙ ቦታ ለህክምና ሄጃለሁ። በወቅቱ የነበረኝ አመራጭ ከሀገር ውስጥ ይልቅ ውጪ መሄድ ነበር። ወደ ህንድ ለመሄድ አስቤ ነበር። እንደ ድንገት ከጌታነህ ጋር እንዲሁ እያወራን (እሱ በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ ነበር የሚጫወተው) ‘ለምን እዚህ አትሞክርም እዚህ እኮ ህክምናቸው አሪፍ ነው’ አለኝ። እዛ ደግሞ የኔ ወንድምም ስላለ ብዙ የነሱ ከጎኔ መኖር ይጠቅመኛል ብዬ አሰብኩ። ወዲያውኑ ጌታነህ ወዲያ ወዲህ ብሎ የቪዚት ወረቀት ላከልኝ። ወደዛ ለመሄድም ትንሽ አስቸጋሪ ነገር ነበረው በዕርግጥ። እንደምንም አሳክቼ እዛ ሄድኩኝ መታከም ጀመርኩኝ ከዛን ታክሜ መጣሁኝ ሆኔም እግሬ ያን ያህል ሰላም ሊሆን አልቻለም፡፡
ከህክምናው በኋላ ድጋሚ ወደ ሜዳ ላትመለስ የቻልከው ለምን ይሆን ? ከህክምና ጥራት ማነስ ወይስ ?
የሚገርመው ከዛ መጥቼ ተመልሼ ድጋሜ ደቡብ አፍሪካ ሄጃለሁ ፤ ህንድም ጭምር ሄጃለሁ። ህንድ ስሄድ ፋይሎቼን ይዤ ነው የሄድኩት። እዛው ራሱ ኤምአር አይ ተነሳሁ ‘ደህና ነው’ አለኝ ሰውዬው። በጣም ግራ አጋባኝ። አየኝ እና ‘ምንም የለውም’ አለኝ። ‘ሰርጀሪው ምናምን ደህና ነው’ አለኝ እና ችግሩ ምን እንደሆነ ስጠይቀው ‘ፊዚዮቴራፒ ስራ’ አለኝ። ፊዚዮቴራፒ መስራት እዛው ጀመርኩኝ እዚህም መጥቼ መስራት ቀጠልከኝ ምንም ሰላም ልሆን አልቻልኩም። እዚህም መጥቼ እንደገና ተመልሼ ዶክተሩን ማየት አለበት ብዬ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄድኩኝ። በድጋሜ ሁለተኛ ዙር አየኝ ፊዚዮቴራፒ አደረገልኝ። እዛው ቁጭ ብዬ ለሁለት ወራት ያህል ታየው። ‘አጥንቶችህ ቦታ ቦታቸው ላይ ገብተዋል ሰርጀሪ የተደረገውም ቦታ ጠንክሯል’ ነው ያለኝ። ግን እስከ አሁን ድረስ ወደ ጤንነቴ ልመለስ አልቻልኩም። በቃ በዚሁ ተስፋ ቆረጥኩ። በቅርብም ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ስር ከአሜሪካ የመጡ ባለሙያዎች አሉ ተብለን ተደውሎልኝ ሄድኩኝ ያለውን ነገር ነገርኳቸው። እነሱም በተመሳሳይ ደህና እንደሆነ እና ፊዚዮቴራፒ ብቻ እንድሰራ ነገሩኝ። እያመመኝ እንደሆነ ገለፅኩላቸው ፤ እነሱም ግራ ገባቸው። እናም አሁንም እዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለሁት። መጫወት እፈልጋለሁ ከህመሜ የተነሳ ግን አሁን ላይ አቁሜያለሁ። ተሽሎኝ ብጫወት ከማንም በላይ ደስተኛ ነኝ። ኳስ ህይወቴ ነበር ፤ የምወደውም ነገር ነው። ግን አሁን ላይ መጫወቱን ማሰቡን ትቼዋለሁ። እኔ አሁን የማስበው ጤነኛ ሆኜ መራመድ መቻልን ነው ፤ ስለዛ እያሰብኩ ነው ያለውት እሱም ቢሆን የራሱ የሆነ ስሜት አለሁ አሁንም ድረስ ግራ እያጋባኝም ያለው ይሄ ነው። ዶክተር ጋር ሄጄ ምንም የለም ከተባለ ምንድነው መፍትሄው ? ምን ባደርግ ይሻላል ? ግራ ነው የገባኝ። እያመመኝ ከአንዴም ሦስት ጊዜ ሀኪም ቤት ሄጄ ‘ሰላም ነህ’ ስባል ምን ሊሰማኝ እንደሚችል መገመት ነው።”
አሁን ያለህበት ሁኔታ ምን ይመስላል ?
“አሁን አዲስ አበባ ነው እየኖርኩ ያለሁት። ጀሞ አካባቢ በግሌ አንዳንድ ስራዎችን እየሰራሁ እገኛለሁ። መቼም ሰው ነኝ እና ዝም ብዬ አልቀመጥም። ትንሽም ቢሆን ለኑሮ እየተሯሯጥኩ እገኛለሁ፡፡”
አሁን ካለው የኢትዮጵያ እግርኳስ እና በሊጉ ከሚገኙ አጥቂዎች አንፃር ከጉዳት ነፃ ብሆን ኖሮ የት ደረጃ ላይ እገኛለሁ ብለህ ታስባለህ ?
“አሁን እንደዚህ ብሎ መገመት አይቻልም። ግን ምንም በኛ ሀገር ሊግ የሚከብደኝ ነገር የለም። መጫወት እችል ነበር። ለኔም ለማንም ያው በሽታ አስቸጋሪ ነገር ነው ፤ እሱ ያዘኝ። ከፈጣሪ ጋር ደግሞ በዚህ የተነሳ አትጣላም እንጂ የትም መድረስ ይቻል ነበር። ጥሩ ነገር ማሳየት እችል ነበር። ደግሞም ጥሩ እየመጣሁ ነበር። ደደቢት የነበረኝን ነገር እንደገና መልሼ ሀዋሳ ቤትም እያሳየሁ የነበረው ነገር ነበር። ሀዋሳ ለኔ ብዙ ነገሩ ተመችቶኝ ወደ ጥሩ ደረጃም እየደረስኩ ባለበት ሰዓት ነው ይሄ ነገር የተፈጠረብኝ።”
በሊጉ ከታዩ አጥቂዎች በቦታ አያያዝ እና በጊዜ አጠባበቅህ ብዙዎች ያደንቁልሀል። ይህን እንዴት አዳበርከው ?
“በእርግጥ የአሰልጣኞች ስራ ይመስለኛል። ክፍለ ሀገር እያለህ በፕሮጀክት ያን ያህል ስለ ፖዝሺን ምናምን ላታውቅ ትችላለህ ፤ መጫወት ግን ትችላለህ። ይሄን ነገር አሰልጣኝህ ነው ሊሰጥህ የሚችለው። አንዳንዴ ደግሞ አንተም የሳጥን ውስጥ ተጫዋች ስትሆን በቦክስ ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ምን እንደሚያደርጉ ታያለህ። ያንን ከማየት እና የአሰልጣኝም ድጋፍ ታክሎበት ነው። በተለይ የሳጥን ተጫዋች የሚባሉትን የውጪዎቹ እነሱዋሬዝ እና ሉዋንዶውስኪን የመሳሰሉትን በደንብ ስታይ ምን ማድረግ እንደምትችል ትረዳለህ። ለማን መስጠት እንዳለብህ የት ጋር መሄድ እንዳለብህ ትረዳለህ። እነሱን እያየው ለመተግበር ምክራለሁ። ከአንድ አንድ ሳይሆን በሂደት ተግባራዊ አደረኩት። ሳጥን ውስጥ ያለውን ግን ደደቢትም እያለሁ ክንፍ ላይ ኳስ ከወጣ ቦክስ ውስጥ መገኘት እንዳለብኝ እረዳለሁ። አጥቂ ስለሆንኩኝ ኳሱ የትም ይሁን የትም እዛ መገኘት እንዳለብኝ አምናለሁ። ኳሱን አግኘሁም አላግኘሁም እኔ አዕምሮ ውስጥ ያለ ነው። በዕርግጥ በሒደት ነው በፕሮጀክት እያለህ አታውቀም በክለብ ደረጃ ነው ስትጫወት የምታውቀው። ሀገር ውስጥ ባሉ ትልልቅ አሰልጣኝ ሰልጥኛለሁ። ስለዚህ ያን ያን ነገር ሲነግሩ ማዳበር ነው፡፡”
በሀገራችን ኢትዮጵያ ጥቂት በግንባር ገጭተው ግብ ከሚያስቆጥሩ መገለጫቸውም ከሆኑ ጥቂት ተጫዋቾች መሀል አንተ አንዱ ነህ፤ ይሄስ ከየት የመጣ ልምድ ነው ?
“በግንባር መግጨት በዕርግጥ ችሎታ ይጠይቃል ፤ ጊዜ አጠባበቅም ይጠይቃል። እኔ መዝለል እችላለሁ። በፊትም ዝም ብዬ እዘል ነበር ክፍለሀገር እያለሁ። በክለብ ደግሞ የመጀመሪያ አሰልጣኜ ንጉሴ ገብሬ ነው። ንጉሴ ገብሬ እንደሚታወቀው ገጪ ነው። በግንባር የሚገጭ ተጫዋች በጣም ነው የሚወደው እናም ያንን ነገር በደንብ ማዳበር ጀምርኩኝ። በራሴ መዝለል እንደምችል አወኩኝ። መግጨት ደግሞ እንዴት እንዳለብኝ ለኔ ኖርማል ነው ከእግር በላይ በጣም ቀላል ነው ብዬ ነው የማምነው። ከክሮሱ ችግር በስተቀር እኔ ግንባሬ ላይ ካረፈ ማስቆጠር አይከብደኝም። ግን ታይሚንግ ይፈልጋል። የተከላካዩን አቋቋም ማየት አለብህ። የራስህን ታይሚንግ ታውቃለህ። የግብ ጠባቂውን የእግሩን ነቀላ ማወቅ አለብህ። ይሄንን አውቀህ ነው አየር ላይ መግጨት ያለብህ። መግጨት ብቻም አይደለም ለሰከንዶች ሽርፍራፊ መቆም አለብህ። መቆም እስከቻልክበት ሰከንድ ድረስ ብቻ ከዛ በዘለለ ልትቆም አትችልም። ሁለት ሰከንድ ነው በዕርግጥ ቀድመህ መዝለል ያለብህ። ቀድመህ ስትዘል ደግሞ አድቫንቴጁ ያንተ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንተ ቀድመህ ዘለሀል ሰከንዶች ስትቆይ ያኛው ዘግይቶ ሊነሳ ይችላል ፤ ስትነሳ እሱን ትጋርደዋለህ። ያን ያንን ካደረክ ደግሞ በጣም ቀላል ነው። በልምምድ የሚዳብር ነው። አሰልጣኞችም አስተዋፅኦ ሲጨመርበት ማድረግ እንደምትችል ስታምንም ይበልጥ ቀላል ይሆናል።”
በእግርኳሱ ባለማሳካትህ የሚቆጭህ ነገር ምንድነው?
“እኔ በእግርኳስ ምንም አላሳካሁም። ማድረግ ካለብኝ ነገር ምንም ሳላደርግ ከእግርኳስ ወጥቻለሁ። ካለኝ አቅም አንፃር ብዙ ማሳካት እየቻልኩ ምንም ዜሮ ላይ ሆኜ ማጠናቀቄ ይቆጨኛል። ሁሌም ስለኳስ ሲነሳ እየቆጨኝ ነው ያለው። ይሄ ይሆነው ሳልችል ተባርሬ አይደለም። ይሄ የገጠመኝ በሽታ ነው። በሽታ ደግሞ እኔ ብቻ ላይ አይደለም። ከእኔ በፊት የነበሩ ትልልቅ ተጫዋቾች በጉዳት ከሜዳ ርቀዋል። ጉዳት ገጠመኝ መጫወት እየቻልኩ ወጣሁ ፤ በቃ ወጣሁ። ይሄ ነው እኔን የሚቆጨኝ። ማሳካት አለማሳካት ኖርማል ነው ለኔ። ምክንያቱን ማድረግ እችል ነበር። ለመመለስ እየሞከርኩም ነበር ስላልሆነ በዛው ቀርቷል፤ በቃ፡፡”
በመጨረሻም በቅፅበት ወደ እግር ኳስ የመመለስ ተስፋ ቢኖርህስ ፍላጎትህ…?
“እውነት ለመናገር ወደ እግርኳስ የመመለስ ፍላጎት ውስጤ በጣም አለ። ኳስ ሱስ ነው ለኔ። ከሱሱ ደግሞ እኔ አልወጣልኝም። እግዚአብሔር ፈቅዶ …(እኔ ነግሬሀለው የመጫወት ነገሩ ከውስጤ ወጥቷል ፤ የለውበትም) ለጠየቀኝ ጥያቄ ግን መልስ እየሰጠሁ ነው። ፍላጎቴ ሞቷል ፤ አሁንም ህመሙ አለ። እኔ ስለመጫወት ሳይሆን ጤነኛ ስለመሆን ብቻ ነው ማስበው፡፡ ለጠየከኝ ጥያቄ ልመልስልህ እና እኔ ነገ ቢሻለኝ መጫወት እፈልጋለሁ። የተሻለ ሆኜ ቀርባለሁም ብዬ አስባለሁ።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ