በዛሬው ዕለት ሕልፈተ ሕይወቱ የተሰማው ተስፋዬ ኡርጌቾ የእግርኳስ ሕይወትን አንጋፋው ጋዜጠኛ ታሪኬ ቀጭኔ በዚህ መልኩ አሰናድቶታል።
ትውልድ እና እድገቱ ወንጂ ከተማ ነው። በአንጋፋው የቀድሞ በአሰልጣኝ ሀጎስ ደስታ አማካኝነት የመጀመርያ ክለቡ ለሆነው አየር ኃይል መጫወት የጀመረው ተስፋዬ በቡድኑ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ በአሰልጣኝ ካሣሁን ተካ አማካኝነት በ1983 ለኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሏል። በግብፅ አስተናጋጅነት በተካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ግብፅ ላይ ከጠፉት 15 ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ቢሆንም በኃላ ላይ የደርግ መንግስት እና የግብፅ መንግስት ባደረጉት ድርድር ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ለአምስት ቀናት ተንገላተው በእስር ቤት ከቆዩ በኃላ የመንግስት ለውጥ ሊመጣ መዳረሻው ላይ ከእስር እንደተፈቱም አውቃለው።
በወጣት ቡድን እና በአየር ኃይል የሚያደርገውን ድንቅ እንቅስቃሴ የተመለከተው ኢንስትራክተር መንግስቱ ወርቁ በ1984 ላይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምጥቶታል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በቆየባቸው ሰባት ዓመታት እጅግ ስኬታማ ተጫዋች የነበረው ተስፋዬ በ1986 የአዲስ አበባ ሻምፒዮን ኮከብ ተጫዋች በመባል መመረጡ ታሪክ ያስረዳል። በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለተከታታይ ሦስት ዓመት ከ1986-88 ድረስ የአዲስ አበባ ሻምፒዮን ሲሆን ጎል በማግባት (በጣም ተለይተው የታወቁት) ሙሉጌታ ከበደ፣ ፍስሀ በጋሻው እና አሸናፊ ሲሳይ ቢሆኑም ከጀርባ ሆኖ ትልቁን ሥራ ይሰራ የነበረው የተስፋዬ ኡርጌቾ ነበር። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ አገልግሎት የሰጠው ተስፋዬ በብዙ የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ የማይዘነጋው በዋናው ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት በ1985 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ ናይጄርያን 1-0 ስታሸንፍ የብቸኛውን ጎል ያስቆጠረበት ነበር።
ብዙም ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ወደ አውሮፓ ወጥተው መጫወት በማይታሰብበት ዘመን ኤልያስ ጁሀር፣ አሸናፊ ሲሳይ፣ ሸዋንግዛው እና ሌሎቹም ቤልጅየም ሲሄዱ እርሱ ወደ ፊላንድ አቅንቶ የመጫወት እድል በማግኘት ጥሩ ቆይታ እያደረገ ቢቆይም የአኗኗር ዘይቤውን ለመልመድ ከመቸገር እና ከቤተሰብ ናፍቆት ጋር በተያያዘ ወደ ሀገሩ ተመልሶ በድጋሚ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቷል። በ1990 ” የእኔ አልጋ ወራሽ ሙሉዓለም ረጋሳ ነው።” ብሎ ለአስራት ኃይሌ ጥቆማ አድርጎ ለሙሉዓለም በቅዱስ ጊዮርጊስ እድል ማግኘት አስተዋፅኦ ያደረገ ሲሆን ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተለያይቷል። ቀጥሎም “ለትልቅ ቡድን መጫወት አልፈልግም” በማለት አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኝ ሰሚት ለሚባል ቡድን መጫወት ችሎ አንደነበር አስታውሳለው።
እግርኳስን ካቆመ በኋላ ወደ አሰልጣኝነቱ ለመግባት ቢያስብም ብዙ ገፍቶ አለመሄዱ በአሰልጣኝነቱ ሳንመለከተው ቀርተናል። በ1996 የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ለቀድሞ ተጫዋቾች አንድ ነገር ለማድረግ አስቦ ሙልጌታ ከበደ፣ ዘሪሁን ሸንገታ፣ አንተነህ፣ ፀጋዬ ባቲ እና ተስፋዬ ኡርጌቾን በተለያዩ ክልሎች በመዞር ታዳጊ ተጫዋቾችን እንዲመለምሉ ያደረገ ሲሆን መሐመድ ናስር፣ አበባው ቡጣቆ እና ሌሎቹም ታዳጊዎች ተመልምለው የመጡት በእነርሱ ነበር።
ከዚህ በኃላ አዲስ አበባ እየኖረ ወደ 2002 አካባቢ በጠና ከመታመሙም ባሻገር ትንሽ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር። ሆኖም የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በሚገባ የህክምና ወጪውን በመቻል አሳክመውታል። እንዲሁም ደጋፊዎችም አስተባብረው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል። በዚህ አጋጣሚ ሁለቱም አካላት ሊመሰገኑ ይገባል። ብዙም ሳይቆይ የጤንነቱ ሁኔታ ተስተካክሎለት የንግድ እንቅስቃሴ ቢጀምርም በኃላ ወደ አሜሪካ አቅንቶ ሰባት ዓመት አካባቢ ኖሯል። ከሦስት ወር በፊት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ነው ዛሬ ህይወቱ ማለፉ የተሰማው። እጅግ የሚያሳዝን ቢሆንም ተስፋዬ በአጠቃላይ በእግርኳስ ተጫዋችነቱ ዘመን በጣም ምርጥ አማካይ የነበረ፤ ሜዳ ላይ ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችል፤ ጨዋታ ላይ ቀልድ የማያቅ መሆኑ ያስገርመኛል። አንድም ቀን በጨዋታ ወቅት በእግር መሐል ኳስ ለማሾለክ (ሎጬ ለማግባት) የማያስብ፤ የአማካይ ተጫዋች ሊኖረው የሚገባ አቅም፣ ድሪብል፣ ፍጥነት እና ድፍረት የነበረው አማካይ ነው።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ