በሲዳማ ቡና ከ2009 እስከ 2010 በነበረበት ወቅት ብዙ ተስፋ ታይቶበት የነበረው ሙጃይድ መሐመድ ጉዳት ካስተናገደ በኃላ ያለፈውን ዓመት በምን ሁኔታ አሳለፈ?
ትውልድ እና ዕድገቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ነው፡፡ ሙጃይድ በታዳጊ ፕሮጀክት ታቅፎ በነበረበት ወቅት ባሳየው አቋም መነሻነት ከተመለመሉ ጓደኞቹ ጋር ሆኖ ወደ አሰላው አካዳሚ ተመርጦ ከ2005 እስከ 2007 እየሰለጠነ ቆይቷል፡፡ የአሰላ ከተማ አካዳሚ ቆይታው በመጠናቀቁም ከማዕከሉ ከወጣ በኃላ ወደ ደደቢት ተስፋ ቡድን አምርቶ በቡድኑ ውስጥ ከዋነኛ ቦታው የተከላካይ አማካኝነት በተጨማሪም በተከላካይ ስፍራ ላይ በመጫወት የአንድ ዓመት ቆይታን ካደረገ በኃላ በጠበቀው መልኩ በቶሎ ወደ ዋናው ቡድን የመግባት ዕቅዱ መሳካት ሳይችል ወደ ትውልድ ከተማው ተመልሶ በአሰላ ከተማ ለሚዘጋጀው የአሰላ ሊግ መጫወትን ቀጠለ፡፡ በ2008 መጨረሻም በአርባምንጭ ከተማ በተዘጋጀው የክለቦች ሻምፒዮና አሰላን ወክሎ በሚጫወትበት ወቅት የወቅቱ የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዓለማየሁ ዓባይነህ ዐይን ውስጥ በመግባቱ ለክለቡ ፊርማውን እንዲያኖር አድርገዋል፡፡ ተጫዋቹም በትልቅ ክለብ ለመጫወት የነበረው ፍላጎት ተሳክቶ በሲዳማ ቡና ለመጫወት 2009 ላይ ፊርማውን ማኖር ችሎ ነበር።
በክለቡ በነበረው የሁለት ዓመት ቆይታ በተከላካይ አማካይነትም ሆነ በመሀል ተከላካይነት በፕሪምየር ሊጉ ለክለቡ በመጫወት ተስፋ ሰጪ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ለፕሪምየር ሊጉ አዲስ የነበረው ሙጃይድ ባሳየውን ድንቅ እንቅስቃሴ መነሻነት ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ሆኖም ተጫዋቹ በ2011የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሦስተኛ የውድድር ዓመት ለሲዳማ ቡና ተሰልፎ ለመጫወት ወደ ልምምድ ከክለቡ ጋር ቢገባም በልምምድ ላይ የደረሰበት አሰቃቂ የእግር ስብራት ከሜዳ አርቆታል፡፡ ሙጃይድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙዎች ዓይን ውስጥ ከገባ በኃላ ከሜዳ ካራቀው ጉዳት አገግሞ ዳግም ወደ ሜዳ ይመለስ ይሆን ? ለሚለው ጥያቄ ይህን ምላሽ ሰጥቷል።
“2011 ላይ ነው ልምምድ ላይ እያለው ጉዳት የገጠመኝ ፤ ፕሪምየር ሊጉ ሊጀመር አንድ ሳምንት እየቀረው። ጉዳቱም በእግሬ አገዳ ላይ ፍራክቸራል እየተባለ የሚጠራ ስብራት ነበር። ጠንካራ ስለነበርኩ አሁንም መጫወትን ስለምመኝ ቀዶ ጥገና አድሬጌ ስድስት ወራትን ራሴን ሳስታምም ቆይቻለሁ። አሁን ግን በጣም ደህና ነኝ። ከሲዳማ ቡና ጋር ኮንትራት አለኝ ፤ ዘንድሮ ለመጫወት ፈልጌም ነበር። ድኜ ስመጣ ግን ከክለቡ ጋር ተጋጨን። እነሱ ‘ቴሴራ ስጠን ለሌላ ተጫዋች እንጠቀመው’ አሉኝ። እኔ ግን ‘እንቢ’ አልኩኝ። ‘በቃ ከክለቡ ተቀንሰሀል’ አሉኝ። ‘እኔ ውል አለኝ’ ብዬም ፌድሬሽን ክስ ጀመርኩ ፤ ለእኔም ተወሰነልኝ። ክለቡ ይግባኙም ጠይቆም ወደ ክለቡ መለስ የሚለው ውሳኔ ፀና። በመሀል ኮሮና ተከሰተ እንጂ እኔ አሁንም መጫወት እፈልጋለሁ። በቅርቡ ወደ ሜዳ እመለሳለሁ ፤ በግሌ እየሰራሁ ነው ጤነኛ ነኝ። ”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ