ዮሐንስ ሽኩር የት ይገኛል ?

ለበርካታ ክለቦች በግብ ጠባቂነት ያገለገለው እና ባሳለፍነው ዓመት ከእግር ኳስ የራቀው ዮሐንስ ሽኩር የት ይገኛል?

በእግር ኳስ ህይወቱ ለሙገር ስሚንቶ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ፋሲል ከነማ እና ወልዋሎ ተጫውቷል፤ በሁለት አጋጣሚዎችም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ደርሶታል። ባለፈው ዓመት አጋማሽ ከወልዋሎ ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እያለው በስምምነት የተለያየው ይህ ግብ ጠባቂ ከወልዋሎ ጋር ከተለያየ በኃላ ከእግር ኳስ ተለይቶ ይገኛል።

ሶከር ኢትዮጵያም የተጫዋቹን ወቅታዊ ሁኔታ አጣርታ ተጫዋቹም ከእግር ኳስ የራቀበት ምክንያት እንደሚከተለው ገልጿል።

” ከወልዋሎ ጋር ከተለያየው በኃላ ከክለብ እግር ኳስ ርቄ ነው ያለሁት ፤ ሆኖም በግሌ ልምምድ በመስራት ላይ ነኝ። ሙሉ ጤነኛ ነኝ ፤ የብቃት ችግርም የለኝም። ሆኖም በአንዳንድ ጉዳዮች ከእግር ኳሱ ለመራቅ ተገድጃለው። በሁለት አጋጣሚዎች አዲስ ክለብ ለመግባት ተቃርቤ ነበር። በተለይም የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ለሁለኛው ዙር ወደ አዲስ ክለብ ለመቀላቀል ተቃርቤ ነበር ” ብሏል።

በ2010 ወልዋሎ በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ባደረገው ተጋድሎ ካለ ተቀያሪ ግብ ጠባቂ በመሪ ተዋናይነት ትልቅ ድርሻ ከነበራቸው ተጫዋቾች ስሙ የሚጠቀሰው ይህ ተጫዋች በሙገር ፣ ንግድ ባንክ ፣ ወልዋሎ እና ፋሲል ከነማ ቆይታዎቹ ደጋፊዎች ላደረጉለት ትልቅ ድጋፍ አመስግኖ በዚህ ወቅት ከተፈጠረው ነገር በኃላ ግን ወደ እግር ኳስ እንደሚመለስ ገልጿል።

” በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉም ደጋፊዎች ትልቅ ነገር አድርገውልኛል። በሁለም ክለቦች በነበረኝ ቆይታ ደግሞ ደስተኛ ነኝ” ብሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ