አሴ ጎል – ታላቁ እግርኳሰኛ ሲታወስ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የድሬ ኮካ ኮላ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ቡና አጥቂ በህይወት ካጣነው ነገ ግንቦት 26 ሦስተኛ ዓመቱን ይደፍናል። ሶከር ኢትዮጵያም ይህ ድንቅ ተጫዋች በኢትዮጵያ እግርኳስ ጥሎት ያለፈውን አሻራ በተለያዩ ጥንቅሮች ለተከታታይ ቀናት ስትዘክረው ትቆያለች።

አሰግድ ተስፋዬ በድሬዳዋ ከተማ ልዩ ሥሙ ደቻቱ በተባለ አካባቢ ከአባቱ ተስፋዬ ደበላና ከእናቱ ወ/ሮ ጌጤ ደበሌ በ1962 ተወለደ። እንደማንኛውም ተጫዋች በሠፈር ውስጥ በመጫወት ጀምሮ በድሬደዋ ኮካ ኮላ ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቀለ። በመቀጠልም ለኢትዮጵያ መድን የተጫወተ ሲሆን በጊዜው የበርካቶችን ቀልብ የገዛውና በማራኪ አረንቅስቃሴው አሁን ድረስ የሚታወሰው መድን በ1985/86 ካፍ ካፕ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ባደረገው አስደናቂ ግስጋሴ ቁልፍ ከነበሩ ተጫዋቾች አንዱ ነበር። በመቀጠል የአሰግድ ማረፍያ ኢትዮጵያ ቡና ነበር። የብቃቱ ጣርያ ላይ የደረሰውና ይበልጥ በኢትዮጵያ እግርኳስ አፍቃሪያን ልብ ውስጥ የገባውም በቡና ባሳለፈው ውጤታማ ጊዜ ነበር። ከክለቡ ጋር ፕሪምየር ሊጉ ከመጀመሩ በፊት የነበረውን የመጨረሻ የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን ጨምሮ የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋጫዎችን ከማንሳቱ በተጨማሪ ክለቡ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሲሸልሱ ሰንሻይንን 8-1 ሲያሸንፍ በግሉ አምስት ጎሎች በማስቆጠር ብቸኛው ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። አል አሕሊን ጥሎ ወደ ተከታዩ ዙር እንዲያልፍ ቁልፍ ሚና ከተጫወቱ ተጫዋቾችም መካከል ነበር። በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን ለሁለት ጊዜያት ሲያሸንፍ በፕሪምየር ሊጉ እግርኳስን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት መፎካከር የቻለ ተጫዋች ነበር።

በሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ዘንድ ከቴክኒክ ብቃቱ፣ ከሰውነት አጠባበቁ፣ ልዩነት ፈጣሪነቱ እና በወጥነት በርካታ ዓመታት ከመጫወቱ ጋር በተያያዘ “ኢትዮጵያዊ ፔሌ”፣ “ሮማርዮ” እና “ዢሬስ” በሚሉ ቅጽል ስሞች የሚጠራው አሰግድ በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ካለው አመለሸጋ ባሕርይ ባሻገር ሜዳ ላይ የተቃራኒን ተከላካይ ክፍል በማሸበር እረፍት የሚነሳ አጥቂ እንደነበር ብዙሀን ይስማሙበታል። የፊት መስመሩ ፊት አውራሪ የኳስ ክህሎቱ፣ ለጎል ያለው ዓይን፣ ፍጥነቱ፣ ጉልበቱ፣ ጠንካራ የኳስ ምቱና በመሳሰሉት በኢትዮጵያ እግርኳስ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ነው።

አሰግድ ተስፋዬ ከእግር ኳስ ዘመኑ ማብቃት በኋላ በተለያዩ ዘርፎች ለሀገሪቱ እግርኳስ ዕድገት የበኩሉን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ካበረከታቸው አገልግሎቶቹ መካከል በክለብና በብሔራዊ ቡድን የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲሁም ታዳጊ ወጣቶችን በእግር ኳስ በማሠልጠን እንደሱ ውጤታማ የሚሆኑ ተጫዋቾች እንድታፈራ ሳይታክት በመልፋት ላይ ነበር። ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት የነበረው አሴ-ጎል ግንቦት 26 ቀን 2009 ረፋድ ከልምምድ መልስ በመታጠቢያ ቤት ውስጥ በድንገት በ48 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል። ሥርዓተ ቀብሩም ባረፈ በሁለተኛው ቀን በቅድስት ሳህሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

*አሰግድ ተስፋዬን የምንዘክርበት ልዩ ልዩ ጥንቅር ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ይጠብቁን።

በዝክረ አሰግድ ልዩ ዘገባ ካሰለጠኑት፣ አብረውት ከተጫወቱት እና ስለ እርሱ ከሚያውቁ ግለሰቦች ጋር ቆይታ በማድረግ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ