” … በሁለት አካላት የተሰበሰበ ገንዘብ ስለሆነ በደንብ ማጣራት ይፈልጋል” መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ

የ2012 የውድድር ዘመን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ውድድሮች መሠረዛቸውን ተከትሎ ክለቦች እያቀረቡ ስለሚገኘው ጥያቄ ዙርያ የሊግ ኩባንያው ሰብሳቢ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ለታዛቢዋች እና ዳኞች የውሎ አበል 870,000 ብር አስቀድመን ከፍለናል፣ ይህ ክፍያ የሰላሳ ሳምንት ያካተተ ቢሆንም ቀሪ ጨዋታ ባለመከናቸውን ምክንያት የ13 ጨዋታ ታሳቢ ተደርጎ ብሩ ተመላሽ ይሁንልን።” ሲሉ ወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ድቻ በይፋ ጥያቄያቸውን ያቅርቡ እንጂ የአብዛኛዎቹ ክለቦች ጥያቄ መሆኑ ይገመታል። ይህን አስመልክቶ የፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማኅበር ዋና ሰብሳቢ የሆኑትን መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በጉዳዩ ዙርያ ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀን ይህን ብለውናል።

“በክለቦቹ በኩል ጥያቄዎቹ እየቀረቡ ናቸው። ጥያቄውን ለመመለስ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል። ምክንያቱም ይህ ሂሳብ የገባው የሊግ ኮሚቴው ሳይቋቋም በፊት ለፌዴሬሽኑ ነው። ፌዴሬሽኑ ከእኛ ጋር ቁጭ ብሎ ሂሳቡን ተሳስበን ከወጪ ቀሪ የተረፈውን ወደ አክስዮኑ ገቢ መደረግ አለበት። ይሄን እየሰራንበት እንገኛለን። ይህ ሒደት ሳያልቅ ገንዘብ መመለስ አንችልም። እንደገናም ይህን ለማድረግ ሁላችንም መሰብሰብ ይፈልጋል። ሆኖም ወቅቱ ይህን ለማድረግ አይፈቅድም። በአጠቃላይ ሁሉም ክለቦች እንደሚያውቁት ሂሳቡ በሁለት አካላት የተሰበሰበ ገንዘብ ስለሆነ በደንብ ማጣራት ይፈልጋል። ሂሳቡ ተሰርቶ እንዳለቀ እኛ ቁጭ ብለን ከተነጋግረን በኃላ የምናሳውቅ ይሆናል” ብለዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ