ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ አስር-ክፍል አንድ

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል።


ካቴናቺዮ

በእግርኳሱ ዓለም የ<ካቴናቺዮ>ን ያህል የጠለሸ ሥም ያተረፈ የታክቲክ አቀራረብ አልታየም፡፡ በጣልያንኛ ቋንቋ ካቴናቺዮ ለበር መዝጊያ የሚያገለግል የ”ሰንሰለት” ቁልፍን የሚወክል ተቀራራቢ ፍቺ ይሰጠዋል፡፡ ይህ የአጨዋወት ሥልት ለበርካታ ዓመታት በሃገሪቱ እግርኳስ ሌሎች የጨዋታ አቀራረብ ዘይቤዎችን በጥርጣሬ የሚመለከት፣ አሉታዊ ገጽታ የተላበሰ እና አካላዊ ጉሽሚያዎች የሚያመዝኑበት እንደሆነ አመላካች ምስል ፈጥሯል፡፡ በተለይ ደግሞ በብሪታኒያ ካቴናቺዮ እጅጉን የጎደፈ ሥም ተሰጥቶት ቆይቷል፡፡ በ1967ቱ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የጃክ ስቴይኑ ሴልቲክ የሥልቱ ዋነኛ አቀንቃኝ የነበረው የሄሌኒዮ ሄሬራ ኢንተር ሚላንን ሲረታ የያኔው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ቢል ሻንክሌይ ለጃክ ስቴይን የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ሲያስተላልፉ ድሉ ስኮትላንዳዊውን አሰልጣኝ “ህያው” እንደሚያደርገው ገልጸውለታል፡፡ ጨዋታው ከተካሄደ በኋላ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የፍጻሜው ፍልሚያ ሲካሄድ ስቴይን በኢንተር ተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ አካባቢ ሁለት የሴልቲክ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን ከሄሬራ ጀርባ አስቀምጦ ሙሉ የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ አርጀንቲናዊውን አሰልጣኝ እያዋከቡት እንዲጨርሱ አድርጓል፡፡ ሄሬራ ግን ሰዎች በአግባቡ እንዳልተረዱት ሲወተውት ኖሯል፡፡ ልክ እንደ ኸርበርት ቻፕማን ሁሉ የእርሱን ቡድን የእግርኳስ አጨዋወት ዘዴ በደረጃቸው ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ቡድኖች ተገቢ ባልሆነ መንገድ እየተገበሩት መሆኑን ሲያስረዳ ኖሯል፡፡ ይህም ስምና ዝናውን እንዳጎደፈበት ይናገራል፡፡ በእርግጥ ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ ከርሟል፡፡ ይሁን እንጂ የካቴናቺዮ ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት አደገኛ እየሆነ በሄደ ቁጥር ተቀባይነቱ እየወረደ መጥቷል፡፡

ካቴናቺዮ በካርል ራፕን አማካኝነት በሲውዘርላንድ የተጀመረ የእግርኳስ አጨዋወት ዘዴ ነው፡፡ በእርጋታ የሚናገረው፣ እምብዛም እውቅና ያልተቸረውና ባለ ግርማ ሞገሱ ራፕን የተወለደው በ1905 በቪየና ነበር፡፡ ከ1920ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ 1930ዎቹ መነሻ ዓመታት ድረስ የዘለቀው የቪየና ወርቃማ የእግርኳስ ዘመን ከራፕን የፕሮፌሽናል ተጫዋችነት ጊዜያት ጋር ተገጣጥሞለታል፡፡ ያን ወቅት ራፕን በፊት መስመር ተሰላፊነት አልፎአልፎም በማጥቃት ላይ የሚያመዝን አማካይ ሆኖ ተጫውቷል፡፡ ራፕን በቡና-መጠጫ ቤቶች እየተሰባሰቡ የልሂቃን ውይይት ከሚያደርጉት የህብረተሰብ ክፍሎች (Coffee-House Society) እንደመገኘቱ በህይወቱ የመጨረሻ ዘመናት ጄኔቫ ውስጥ ዴ-ላ ቦርዤ የተሰኘ ካፌ ከፍቶ ያስተዳድር ነበር፡፡ ራፕን በ1930 ለኦስትሪያ ብሄራዊ ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል፤ በዚሁ ዓመትም ከራፒድ ቪዬና ጋር የሊጉን ድል ተቀዳጅቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሲውዘርላንድ አምርቶ በሰርቫቴ ክለብ በተጫዋች-አሰልጣኝነት ተሾመ፡፡ ራፕን በሰርቫቴ ያገኛቸው ተጫዋቾች እግርኳስን የመሉ ጊዜ ስራቸው ያደረጉ አልነበሩም- ይልቁንም በሌላ የሙያ መሥክ ኑሯቸውን እየመሩ እግርኳስን በትርፍ ጊዜያቸው የሚጫወቱ (Semi-Professionals) ነበሩ፡፡ ስለዚህም ራፕን እነኚህን ተጫዋቾች ከሌሎቹ ፕሮፌሽናል ቡድኖች ውስጥ ከሚገኙ ተጫዋቾች ጋር ተቀራራቢ የአካል ብቃት ደረጃ ላይ ለማድረስ የስልጠና መንገዱን እንደገና ማሻሻል እንደተጠበቀበት አንጋፋው የሲውዘርላንድ ስፖርት ጸሃፊ ዋልተር ለትዝ እንዲህ ሲል ጽፏል፡፡ ” በስዊዝ ቡድኖች ታክቲክ እጅግ ወሳኝ ድርሻ አለው፤ አንድ ሲውዘርላንዳዊ ተጫዋች በተፈጥሮ የታደለው የተለየ ክህሎት ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገርግን እንቅስቃሴዎችን የሚቃኝበት ሒደት ረጋ ያለ ነው፡፡ ይህን ተጫዋች አርቆ እንዲያስብ አልያም የወደፊቱን እንዲያሰላ ለማድረግ ማሳመን ቀላል ይሆናል፡፡ አንድ ቡድን በሁለት መንገዶች ሊገነባ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው የተትረፈረፈ ተፈጥሯዊ ክህሎት እና የተናጠል ብቃት ያላቸው አስራ አንድ ተጫዋቾች ይኖሩህና ተጋጣሚዎችህን በቀላሉ እንድትረታ ይረዱሃል፤ ብራዚልን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መሃከለኛ ደረጃ የሚሰጣቸውን አስራ አንድ ተጫዋቾች ትይዝና ሁሉም ወጥ የሆነ የአጨዋወት ግንዛቤ ኖሯቸው በጥሩ ሁኔታ እንዲቀናጁ የሚያስችል ዕቅድ ታዘጋጃለህ፡፡ ትልምህ ለቡድንህ ስኬታማ መሆን ከእያንዳንዱ ተጫዋችህ ምርጡን የምታገኝበት ሊሆን ይገባል፡፡ አስቸጋሪው ነገር ተጫዋቾቹ በጥልቀት የማሰላሰል እና ያሰቡትን የመተግበር ነጻነታቸው ሳይነካ ከፍተኛውን የታክቲክ አተገባበር ሥርዓት (Absolute Tactical Discipline) እንዲያሳዩ ማስገደዱ ላይ ነው፡፡” ሲል የ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት ለ<ወርልድ ስፖርት መጽሄት> በሰጠው ብቸኛ ቃለ-ምልልሱ ላይ ተናግሯል፡፡

በአንድ ሲውዘርላንዳዊ ጋዜጠኛ <ቨሩው> ወይም “ማሰሪያ-ብሎን” የሚል ስያሜ የተሰጠው የራፕን ታክቲካዊ መፍትሄ ከጥንቱ 2-3-5 ቀጥሎ የመጣ የታክቲክ እድገት ውጤት እንደሆነ ይታሰብ ነበር፡፡ የኸርበርት ቻፕማኑ W-M (3-2-2-3 ፎርሜሽን) ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ በኋላም ቢሆን 2-3-5 በቪዬና ለረጅም ጊዜ በሰፊው የሚተገበር መደበኛ ፎርሜሽን ሆኖ ቆይቷል፡፡ ልክ በ(WM/3-2-2-3/)  እንደሚደረገው የመሃል-ተከላካይ አማካዩን (Centre-Half) ወደኋላ ስቦ በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች (Full-Backs) መካከል ከማሰለፍ ይልቅ ሁለቱ የመስመር አማካዮች (Wing- Halves) በየመስመሮቻቸው ወደኋላ ተመልሰው ቀዳሚዎቹን የመስመር ተከላካዮች (Full-Backs) ወደ መሃል (Center) በመግፋት እነርሱ (Wing-Backs) የመስመር ተከላካይ ይሆናሉ፡፡ የማጥቃት ሚናቸው እንዳለ ቢሆንም ኃላፊነታቸው በዋነኝነት የተጋጣሚን የመስመር አማካዮች/አጥቂዎችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ይሆናል፡፡ ስለዚህም ቀዳሚዎቹ የመስመር ተከላካዮች (Full-Backs) የመሃል ተከላካዮች (Centre-Backs) ሆነው በጣም በመቀራረብ መጫወት ይጀምራሉ፤ በተግባራዊ ልምምድ (Practice) አማካኝነትም ጥሩ ጥምረት እንዲፈጥሩ ይደረጋሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የተጋጣሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር በኩል ከሆነ ከሁለቱ የመሃል ተከላካዮች በስተግራ በኩል ያለው ኳሱ ወዳለበት አካባቢ ይሄዳል፤ ይኼኔ ከጎኑ (በቀኝ በኩል) ያለው ሌላኛው የመሃል ተከላካይ ሽፋን ይሰጠዋል፤ ትቶት የሄደውን ክፍተት ለመድፈን ጥረት ያደርጋል፡፡ የተጋጣሚ ቡድን ጥቃት በስተግራ ከሆነም እንዲሁ የሁለቱ የመሃል ተከላካዮች ሚና በተመሳሳይ መልኩ እየተቀያየረ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ በንድፈ-ሐሳብ (Theory) ደረጃ ይህ አይነቱ የተጫዋቾች የሚና ሽግሽግ በኋላው መስመር አንድ ትርፍ ተከላካይ ተጫዋች ያስገኛል፡፡ በዚያን ጊዜው የሲውዘርላንድ የእግርኳስ ህትመት ውጤቶች ዘንድ በሰፊዉ <Verouller/ቨሩውለር/> የተሰኘ ስያሜ የተሰጠውና ኋላ ላይ <Libero/ሊቤሮ> በሚል መጠሪያ የታወቀው ይህ ተከላካይ ከዚሁ የታክቲክ ዕድገት ጋር የመጣ ግኝት ሆኗል፡፡

የ<ቨሩው> አጨዋወት ሥልት ዋነኛው ደካማ ጎን በመሃል-ተከላካይ አማካዩ (Centre-Half) ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ነው፡፡ ፎርሜሽኑ በወረቀት ላይ አራት ተከላካዮችን መያዙ፣ የመሃል-ተከላካይ አማካዩ (Centre-Half) ወደኋላ ካፈገፈጉ ሁለት የፊት መሥመር ተሰላፊዎች (Withdrawn Inside Forwars) አልያም አማካዮች (Halves) ጀርባ መሰለፉ እና በአንድ የጎንዮሽ መስመር የተደረደሩ ሶስት አጥቂዎችን ማካተቱ ታሳቢ ሲደረግ ከዘመናዊው 4-3-3 ፎርሜሽን ጋር ተመሳስሎ ያለው ሆኖ ይታያል፡፡ ጆዜ ሞውሪንሆ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የውድድር ዘመናት የቼልሲ ቆይታቸው ይህንኑ አጨዋወት ተግብረውታል፡፡ ይሁን እንጂ በአቀራረብ ረገድ ትልቅ ልዩነት ታይቷል፡፡ የመስመር አማካዮቹ (Wingers) በሜዳው ቁመት እስከ ተጋጣሚ የመከላከያ ወረዳ ድረስ የሚሄዱበት ሁኔታ ነበር፡፡ ልክ እንደ አጥቂዎች በፊተኛው መስመር የማጥቃት ሚናቸውን ይወጣሉ፤ ኳስ በተጋጣሚ ቡድን ቁጥጥር ሥር ሲሆንም ወደኋላ ተመልሰው ለመሃል ክፍሉ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅም አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በላይኛው የማጥቃት ሲሶ ያሳልፋሉ፡፡ ይህም ቨሩው ፎርሜሽን (1-3-3-3/1-4-4-1/5-4-1) በሌሎች የተለያዩ የአጨዋወት ሥልቶች ብልጫ እንዲወሰድበት ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ቨሩውን (1-3-3-3) ከWM(3-2-2-3) አንጻር እንቃኘው፦ ሶስቱ የWM የፊት መስመር ተሰላፊዎች በተለመደው መንገድ በሶስቱ የVerrou ተከላካዮች ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡ በቨሩው ሲስተም ወደኃላ ያፈገፈጉት አማካዮችም(Inside Forwards) የWMን ሁለት የተከላካይ አማካዮች (Halves) ክትትል ያደርጉባቸዋል፡፡ ይህም በ<1-3-3-3/1-3-1-2-3> ፎርሜሽን የመሃል-ተከላካይ አማካዩን (Centre-Half) ከተጋጣሚ ሁለት አማካዮች (Inside Forwards) ጋር እንዲጋፈጥ ያደርገዋል፡፡ ትልቁ ችግር የሚፈጠረውም እዚህ ጋር ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ “ሊቤሮ”ን የሚያሰልፉ ቡድኖች በሙሉ ይገጥማቸዋል፡፡ በአንደኛው የሜዳ ጥግ አንድ ትርፍ ተጫዋች የሚያስገኝ ሲስተም በሌላኛው የሜዳ ክፍል አንድ ጉድለት መፍጠሩ አይቀሬ ነውና፡፡

ምስል፦ የራፕን “ቨሩው” ሲስተም፣ 1938

የቨሩው አጨዋወትን የሚተገብር ቡድን  2-3-5ን ከሚመርጥ ተጋጣሚ ጋር ሲገናኝ ደግሞ ይበልጡን ከባድ ሁኔታዎችን ይጋፈጣል፡፡ ምንም እንኳ 1-3-3-3 ፎርሜሽን ከ2-3-5 አንጻር በሜዳው ቁመት በታችኛው (በመከላከል-ሲሶ) እና በላይኛው (በማጥቃት-ሲሶ) ሁለት ትርፍ ተጫዋቾችን ማስገኘት ቢያስችልም የመሃል- ተከላካይ አማካዩ (Centre-Half) ግን ከተጋጣሚ ሁለት ወደኋላ ያፈገፈጉ የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) በተጨማሪ የተጋጣሚ ቡድኑን የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Centre-Half) እንዲቆጣጠር ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሌም የሚቻል አይደለም፡፡ ስለዚህ ራፕን ቡድኑ ወደኋላ በጥልቀት እንዲያፈገፍግ በማዘዝ፣ የአማካይ ክፍሉን የበላይነት ለተጋጣሚ አሳልፎ በመስጠት፣ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ እንዲሁም የማጥቃት ክፍሉን በማጠናከር የተጋጣሚ ቡድን ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር ተጫዋቾች ኳሱን ወደ መስመሮች ብቻ እያወጡ እንዲጫወቱ ማስገደድ ቻለ፡፡ የአጨዋወት ሥርዓቱ እየተለመደ ሲመጣና ቡድኖች በሰፊው እየተገበሩት ሲሄዱ ከሁለቱ አማካዮች አንደኛው ከመሃል-ተከላካይ አማካዩ ጎን መሰለፍ መረጠ፡፡ ይህም የመሃል-ተከላካይ አማካዩ ላይ የነበረውን ጫና ቀስ በቀስ ያቃልለው ጀመር፡፡ ከሁሉ በላይ እጅግ እንግዳ የሆነው ለውጥ የታየው ግን በተከላካይ መስመሩ ላይ ሆነ፡፡ ቀደም ሲል በ2-3-5 ከመስመር ተከላካይነት (Full-Backs) ወደ መሃል ተከላካይነት (Centre-Backs) ከተቀየሩት ሁለቱ ተጫዋቾች አንደኛው በቋሚነት ከሌላኛው ጀርባ በመሰለፍ የጠራጊ ተከላካይን (Orthodox Sweeper) ኃላፊነትን መወጣት ጀመረ፡፡

ካርል ራፕን ከሰርቨቴ ጋር ሁለት፥ በ1935 ማሰልጠን ከጀመረው ግራስሆፐርስ ጋር ደግሞ አምስት የሊግ ዋንጫዎችን አሸንፏል፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ ወደ እግርኳሱ ዓለም ያመጣው የአጨዋወት ሥልት ውጤታማ መሆኑ የታየለት ከሲውዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን ጋር ባሳለፋቸው ስኬታማ ቆይታዎች ነው፡፡ ራፕን በ1937 የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ፡፡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥም ሃገሪቱን ለ1938ቱ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ አበቃት፡፡ በወቅቱ ሲውዘርላንድ ከመካከለኛው የአውሮፓ ሃገራት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣት ደካማዋ የእግርኳስ ሃገር ነበረች፡፡ በዶክተር ጌሮ ዋንጫ የነበራት ሪከርድም እጅግ ዝቅተኛ ነበር፡፡ ሰላሣ ሁለት ጨዋታዎች አከናውና፥ አራቱን አሸንፋ፣ ሶስቱን አቻ ወጥታ፣ በሃያ አምስቱ የመሸነፍ ዕጣ ገጥሟታል፡፡ ራፕን ቨሩው ሲስተምን መጠቀም ከጀመረ በኋላ ግን ሃገሪቱ የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት እንግሊንን በወዳጅነት ጨዋታ 2-0 መርታት ቻለች፡፡ ቀጠለችና በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ያኔ ኦስትሪያን ጠቅልላ ይዛ የነበረችውን ጀርመን አሸነፈች፡፡ ከውድድሩ የተሰናበተችው በኃያሏ ሃንጋሪ 2-0 ከተረታች በኋላ ነበር፡፡ ቀደም ሲል ሃገሪቱ ከነበራት ዝቅተኛ የእግርኳስ ደረጃ አንጻር በሃንጋሪ 2-0 ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበት በክብር የመሸኘት ያህል ሆነላት፡፡ ይህም ቨሩው የአጨዋወት ሥልት መጠነኛ ትኩረት እንዲቸረው ገፋፋ፤ ደካማ ቡድኖች ለተጋጣሚዎቻቸው ቢያንስ አስቸጋሪ ሆነው የሚቀርቡበትን ፍንጭ አሳየ፡፡


ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡