የዛሬ ሦስት ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየን አሰግድ ተስፋዬን አስመልክቶ በተለያዩ ፅሁፎች ስናስበው መቆየታችን ይታወሳል። በዚህ የመጨረሻ ክፍል መሰናዶም ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ሊብሮ የአሰግድ አስገራሚ ገጠመኞችን እንዲህ አጋርቶናል።
አሰግድ እና ናይጄርያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ናይጀርያ ሄዶ አሰግድ ተጠባባቂ ወንበር እንደሚቀመጥ ይነገረዋል። እንደማይገባ ያወቁት የመጀመርያ አስራ አንድ ተሰላፊ ተጫዋቾች ጨዋታው ከመጀመሩ በፊትም የአንገት ሀብል እና የተለያዩ የግል ቁሳቁሳቸውን እንዲይዝላቸው ይሰጡታል። ያው ናይጄሪያ ሌቦች አሉና ጠብቅልን ብለው መሆኑ ነው። ጨዋታው ተካሂዶ በናይጄሪያ ስድስት ለአንድ ተነሸንፍን፤ ከዛ በውጤቱ የተደሰቱት የናይጀርያ ኳስ አቀባዮች አሰግድን ተሸክመው መጨፈር ጀመሩ። ለካ ከጨዋታው መጀመር በፊት ሀብሎች ተቀብሎ በቱታው ኪስ ውስጥ ሲያስቀምጥ አይተውታል። ተሸክመውት እየጨፈሩ ኪሱ ገብተው እቃዎቹን ወሰዱበት። በኋላ ይህ የገባው አሰግድ በድንጋጤ ይጮኸል፣ ፖሊሶች በፍጥነት መጥተው አስለቅቀውት የተወሰደውንም ንብረት እንዲመለስ አድርገውለታል።
አሰግድ እና ሱዳን
የአሰግድ በብሔራዊ ቡድን የመጀመርያው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ከሱዳን ጋር ያደረገው ነው። ወደ ሱዳን ለጨዋታ ሲሄዱ እንደአጋጣሚ ሙሉጌታ ከበደ አግብቶ ሠርጉን በደምብ ሳያጣጥም ነው ወደ ሱዳን የሄዱት። ሱዳን ደግሞ በወቅቱ የነበረው ሙቀት በጣም ከፍተኛ ነበር። አንድ የማነ የሚባል ኤርትራዊ ብስክሌተኛ አሰግድን እንደሚፈልገው መልዕክት ሆቴል ይልክልታል። አሰግድም መልዕክቱን አይቶ በቀጠሮ መሠረት ቦታው ቆሞ ይጠብቀዋል። መልዕክቱም አሰግድ ወደ አዲስ አበባ የሚላክ ዕቃ እንዲያደርስለት ነበር። የሚገርመው አሰግድ ቆሞ ከሆቴላቸው ፊት ለፊት ቢጠብቀው የማነ አልመጣም። አሰግድ ተናዶ ወደ ሆቴሉ ይገባል። ለካ ያልመጣው ብስክሌተኛው በከፍተኛው ሙቀት ምክንያት ህይወቱ በማለፉ ነበር። ይህን ነገር ሙልጌታ ከበደ ይሰማና በነጋታው በነበረው ጨዋታ ሙልጌታ ሠርጌን ሳላጣጥም ልሞት ነው እንዴ ብሎ ጨዋታውን አቋርጦ ጥሎ ይወጣል። ምክንያቱም የማነ በሙቀት ምክንያት መሞቱን ስለሰማ። አሰግድም ምንም ሳይዘጋጅ ሽንቱም ሳይሸና ተቀይሮ ይገባል። ጨዋታ ውስጥ ሜዳ ላይ ሽንቱን ወጠረው፤ ለቡድን ጓደኞቹም የሆነውን ነገራቸው። እነሱም ከበውት ሜዳ ውስጥ ሽንቱን ሸንቷል። በኃላ ላይ አሰግድ ሲጠየቅ “ለመሽናት ወደ መልበሻ ክፍል ገብቼ ነበር። ሆኖም ሁሉም ፅሑፉ በአረብኛ ስለሆነ ሽንት ቤቱ አጥቼው ነው” ብሏል ።
አሰግድ እና ተቃውሞ
በ1982 ዓ.ም አሰግድ ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለ ከእርሻ ሠብል ጋር የፍፃሜ ጨዋታ ያድርጋሉ። አሰግድ ዓመቱን ሙሉ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ስለነበረ ደጋፊ አይወደውም ነበር። ጨዋታው ቀጥሎ እርሻ ሰብል እያጠቃ ጨዋታው ባዶ ለባዶ ነበር። ሊያማሙቅ ሲነሳ ደጋፊው እንዳይገባ ጮኸበት ሆኖም መንግስቱ ወርቁ ተቀይሮ እንዲገባ አድርጎት ጎል አገባ። ደጋፊዎች ተቀይሮ እንዳይገባ ጮኸውበት ግብ ያገባበት አጋጣሚ አይረሳም። ብዙም አልቆየም ጊዮርጊስን ለቆ ወደ መድን ሄደ። በሌላ አጋጣሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለ ሁሉም ተጫዋች ለአዲስ አበባ ምርጥ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው እርሱ ሳይመረጥ ቀርቶ ብቻውን ካምፕ የቀረበት አጋጣሚ የሚያስገርም ነው።
አሰግድ እና አበዳሪነት
የአሰግድ ሌላው ታሪክ ደግሞ ገንዘብ አበዳሪ ነበር። ደሞዙ ሰባ ብር ነው። የሚጠቀመው ተጠቅሞ ከዚህ ብር ላይ ተርፎትም ያበድር ነበር። በዚህ ምክንያት ብር የጨረሱ ተጫዋቾች እርሱ ጋር እየመጡ ብድር ይበደሩ ነበር። ሌላው አሰግድ የሚታወቅበት ነገር ሰው መፈንከት ነው። ድሬደዋ ላይ የዛየር ግብ ጠባቂን ፈንክቶታትል ይባላል።
አሰግድ እና መብራት ኃይል
ከድሬዳዋ እንደመጣ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሲያዩት ተክለ ሰውነቱ ደቃቃ ነው ብለው ይህማ ለ ‘ B ‘ ቡድን እንጂ ዋናው ቡድን አይጫወት ብለው የመጀመሪያው ጨዋታውን ከመብራት ኃይል ጋር አድርጓል። የሚገርመው ደግሞ ወደ ዋናው ቡድን ሲያድግም የመጀመርያ ጨዋታው ያደረገው ከመብራት ኃይል ጋር መሆኑ ግጥጥሞሹ አስገራሚ ነው።
አሰግድ እና አስረኛው የአፍሪካ ዋንጫ
አስረኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ በድሬደዋ ከተማ ሲካሄድ አሰግድ ሁለት አጋጣሚዎች ነበሩት። አንደኛው በልጅነቱ ከአንድ ልጅ ጋር በመሆን የአበባ ጉንጉን መስጠቱ እና ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በሜዳው ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ይመታ እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ